” …መገናኛ ብዙሃንን እየመሩ መገናኛ ብዙሃኑን ላልተፈለገ ዓላማ የሚጠቀሙበት፤ ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር በማቀናጀት አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥሩ የሚችሉ ግለሰቦችና ሰብስቦችም አሉ። በተለይም በአሁኑ ወቅት በጅምላ የመፈረጅና የማጥቃት ሁኔታ ስላለ ጋዜጠኞች ወደተለያየ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመዘገብ ያስቸግራቸዋል። የደቦ ጥቃት ሊደርስባቸው ስለሚችልም ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል,,, “

የዛሬው እንግዳችን በጋዜጠኝነት ሙያ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል። በርከት ባሉ የአገራችን የግል መገናኛ ብዙሃን ውስጥም አሻራቸውን አሳርፈዋል። ጋዜጠኝነትን «ሀ» ብለው የጀመሩት በ1985 ዓ.ም «ህሊና» በምትባል መጽሔት ነው።

የ«ጦማር ጋዜጣ» መስራችና ጋዜጠኛም ነበሩ። በኢንተርፕሩነር እና በካፒታል ጋዜጦችም በመስራችነትና በጋዜጠኝነት ተሳትፈዋል። በፎርቹን ጋዜጣ በጋዜጠኝነት አገልግለዋል። ላለፉት 16 ዓመታት በሪፖርተር የእንግሊዝኛና የአማርኛ ጋዜጣ ላይ ሲሲሩ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅትም የአማርኛው ሪፖርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ሆነው እያገለገሉ ነው። ጋዜጠኛ መላኩ ደምሴ ይባላሉ።

ከአንጋፋውና የበርካታ ዓመታት ልምድ ባለቤት ከሆኑት ጋዜጠኛ መላኩ ደምሴ ጋር በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ውጣ ውረድ፤ ችግርና መፍትሄ ዙሪያ ረዘም ያለ ቃለ ምልልስ አድርገናል። ጋዜጠኛ መላኩ በልምዳቸው የቀሰሙትን መነሻ በማድረግ ስለአገራችን መገናኛ ብዙሃን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውናል። በቀጣይ የተሻለ ለማድረግ መሰራት አለባቸው ስለሚሏቸው ጉዳዮችም ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። ቆይታችንን እንደሚከተለው አቅርበነዋል። 


አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ የግል መገናኛ ብዙሃን በይፋ ነፃነቱን ያገኘው መቼና እንዴት ነበር?

አቶ መላኩ፡– የመገናኛ ብዙሃን ወደ ስራ የገቡት ህገ መንግስቱ ከመጽደቁ በፊት በሽግግር መንግስቱ ወቅት ነው። በ1983 ዓ.ም መጨረሻ የሽግግር መንግስቱ እውን ሆነ። የሽግግር መንግስቱ እውን እንደሆነ ጋዜጦች በመንገድ ላይ መታየት ጀመሩ። ህግ ከመውጣቱ በፊት የህትመት ውጤቶችን በአደባባይ መሸጥ ተጀምሮ ነበር። ይህን ተከትሎም ለአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው የፕሬስ ህግ አዋጅ ቁጥር 34/1985 ወጣ። በዚሕ አዋጅ መገናኛ ብዙሃን እየሰሩ በህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ህገ መንግስቱ ጸደቀ።

አዲስ ዘመን፡– በህገ መንግሥቱ ለመገናኛ ብዙሃን የተሰጠው ነፃነትና አተገባበሩ ላይ ያለዎ ሀሳብ ምንድን ነው?

አቶ መላኩ፡– ህገ መንግሥቱ ጥሩ ነገር ይዞ መጥቷል። በህገ መንግሥቱ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የያዘው ክፍል ነው። በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 የተደነገገው የፕሬስ ነፃነት ነው። አንቀጹ የተወሰደው የተባበሩት መንግሥታት እ.ኤ.አ በ1948 ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 19ኝን ቃል በቃል በመተርጎም ነው።

በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 የተረጋገጠው መብት ለፕሬስ ነፃነት ሙሉ እውቅና ሰጥቷል። በህገ መንግሥቱ ላይ እውቅና ቢያገኝም በተግባር ግን ብዙ መከራ አይቷል። ህገ መንግሥቱ በብዙ ቦታዎች አልተከበረም። ይህ ባለመከበሩ በሁሉም መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ችግር ሰፍኗል።

በመሆኑም፤ ራሳቸውን ከመንግሥት እኩል የሚያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ለመገናኛ ብዙሃን በጣም አስጊ ስለሆኑ የህግ የበላይነት መከበር አለበት።

አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ የግል መገናኛ ብዙሃን የውድቀታቸው አስኳል መንስዔ ምንድን ነው ይላሉ?

አቶ መላኩ፡– የግል መገናኛ ብዙሃን ችግር የሚጀመርው ገና ከመጀመሪያ ነው። ከ1985 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ክሶች፤ ማሳደዶች፤ እያነቁ እስር ቤት መክተት፣ ለተወሰኑ ቀናት ደብዛን ማጥፋት ነበር። በቤተሰብ ብዙ ፍለጋ ተሯሩጦ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደርጎ በዋስ ሲፈቱም፤ በድጋሚ ከመንገድ ላይ አፍሶ ሌላ ቦታ መሸሸግ መንግሥት ያደርግ ነበር። በዚህ ሁኔታ እየተሰራ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ተከሰተ።

አዲስ ዘመን፡– በኢትዮኤርትራ ጦርነት የግል መገናኛ ብዙሃን ሚና ምን ነበር?

አቶ መላኩ፡– በጦርነቱ ወቅት የግል መገናኛ ብዙሃን ሉዓላዊነትን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ቁጥር አንድ ተሟጋችና ቀስቃሽ ሆኖ ሰርቷል። ጦርነቱ እንደተጠናቀቀ ህዝባዊ ውያነ ሓርነት ትግራይ (ህውሓት) ለሁለት ተሰነጠቀ። አንደኛው አሸናፊ ሆኖ ወጣ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከ 1997 ዓ.ም ለግል መገናኛ ብዙሃን በአንፃራዊነት ምቹ ጊዜ ነበር። ችግር አልነበረም ማለት ግን አይደለም። ክስና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩም በርካታ የግል መገናኛ ብዙሃን በሥራ ላይ ነበሩ። ምርጫው ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ አገር ጤና፤ ሁሉም ደህና ሆኖ የግል መገናኛ ብዙሃን ሥራ እየሰሩ ነበር። ምርጫው የተካሄደ ዕለት ማታ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ ብዙ ትርምስ ተፈጠረ።

…የመንግሥት አፋኝነት ቢቆምም ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተዋንያንና መገናኛ ብዙሃኑን በቀጥታና በተዘዋዋሪ በማስፈራራት ለመጠምዘዝ ጥረት የሚያደርጉ ማፊያ መሰል ኃይሎች አሉ። እነዚህ ጽንፈኛ ቡድኖችና ግለሰቦች ለጋዜጠኞች ስጋት ናቸው።

አዲስ ዘመን፡– ምን ተፈጠረ?

አቶ መላኩ፡– የግል መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞች ወደ እስር ቤት ገቡ። የተቀሩትም ከአገር ተሰደዱ፤ ሌሎችም ሥራቸውን አቆሙ። የመገናኛ ብዙሃን ፍቃድ አወጣጥም ራሱን የቻለ መከራ ሆነ። የ97ቱን ምርጫ ተከትሎም ሦስት አደገኛ አዋጆች ወጡ።

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

የመጀመሪያው፤ የመገናኛ ብዙኃንንና የመረጃ ነፃነትን የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 590/2000 ዓ.ም ሲሆን፤ ይህም አዋጅ ቁጥር 34/1985ን የሚተካ ነው። ገና ህጉን በማርቀቁ ሂደት የሀሳብ ጦርነት ተጀምሮ ነበር። ’አፋኝ ነው፤ አያሰራንም፤ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 የተረጋገጠውን የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት አይወክልም፤’ ብንልም ማንም ሊሰማን አልቻለም፤ አዋጁ ጸደቀ። ሁለተኛው የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ ጸደቀ። እነዚህ አዋጆች የሥነ ምግባር ተቋማትን አሽመደመዷቸው።

ከዚያም ቀጥሎ የመጨረሻው አፋኝ ህግ የሆነው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ወጣ። እነዚህ ህጎች የመገናኛ ብዙሃንን ብቻ ሳይሆን ሀሳብን የመገልጽ ነፃነትን ሙሉ ለሙሉ አፈር ድሜ አብልተው እንዳይሆን አደረጉት። በህገ መንግሥቱ የተቀመጠው ሰፊ ነፃነት ብንሰራበት ብዙ ልናተርፍ የሚያስችል ቢሆንም፤ ተልኮስኩሶ ተግባራዊ ሳይሆን ቀረ።

አሁን ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግሥት ከምንም በፊት ቅድሚያ ሰጥቶ ባለሙያዎችን ሰብስቦ እያስተካከለ ያለው ይህንን ነው። ይህም የሚያሳየው እነዚህ ሦስት ህጎች ከ1997 ዓ.ም በኋላ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ችግር መፍጠራቸውን ነው።

አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ የግል መገናኛ ብዙሃን ሙያውን አክብረው ከመስራት ይልቅ በአካል ጦርነት የተሸነፉ አካላት መዋጊያ እንደሆኑ፤የችግራቸው መንስዔውም ይህ እንደሆነ ይነሳል። እርሰዎ ስለዚህ ምን ይላሉ?

አቶ መላኩ፡– ይህ የሰዎች አስተያየት ነው። እያንዳንዱ ሰውም ለሚሰጠው አስተያየት ኃላፊነት አለበት። በእኔ ግምገማ በግል መገናኛ ብዙሃን ውስጥ በርካታ ሰዎች ገብተዋል። እንደተባለው በደርግ ጊዜ በጋዜጠኝነትና በተለያየ ሙያ ይሰሩ የነበሩ ወደ ዘርፉ ገብተዋል። ከዚያም ውጭ ከተለያየ የሥራ መስክና ትምህርት ቤትም የመጡ ሰዎች ተቀላቅለዋል።

መንግሥት በጅምላ ለፕሮፓጋንዳ እንዲመቸው ያለፈው ሥርዓት ርዝራዦች ገብተውበት ነው ዘርፉ የተበላሸው ሲል ይሰማል። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልገነባ ነው ያለ መንግሥት የተለየ ሀሳብ በሚያራምድ ወገን ላይ አደጋ የሚያደርስ ነው የሆነው፤ የመንግሥት ባለስልጣናት በየአደባባዩ የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች… ምናምን እያሉ ሲዘልፉ ነበር። በዴሞክራሲዊ ስርዓት ውስጥ መብታችንን በዚህ መንገድ እንገልፃለን የሚሉ ሰዎችን ማስተናገድ ነው የሚገባው፤ መንግሥት ይህን ማድረግ አልቻለም። ቦልቴየር የተባለ ፈላስፋ ዴሞክራሲን ሲገልጽ «የምትለውን ነገር ሁሉ ባይስማማኝም የፈለግኸውን በአደባባይ እንድትገልጽ መቃብር እስክገባ ድረስ እደግፍሀለሁ» ነው ያለው፤ የኢትዮጵያ የግል መገናኛ ብዙሃን ከመጀመሪያው ጀምሮ ነው መስመሩን መሳት ይታይበት ነበር።

መንግሥት ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ ነው የጠላት ምሽግ አድርጎ የሳላቸው። በፖሊሲ፣ በስልጠና በምክር አያግዛቸውም። የፀረ ሰላምና የፀረ ህዝብ ኃይሎች መሰባሰቢያ ምሽግ አድርጎ ነው የሚያስባቸው፤ የግሉ ፕሬስ እንደሌላው ዘርፍ በመሳሪያና በታክስ እገዛ ለማድረግ ዞር ብሎ አያያቸውም ነበር። እጅግ ከተወሰኑ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውጭ መረጃ ሲጠይቅም ይከለክሉ ነበር።

ከዚያም አልፎ ፍርድ ቤት ተከስሰው ሲሄዱ እጽ አዘዋዋሪዎች በሚከሰሱበት 15ኛ ወንጀል ችሎት ነበር የግል መገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎች ችሎት የሚቀርቡት፤ ይህ የግል መገናኛ ብዙሃንን ልክ እንደ ዕጽ አደገኛ አድርጎ እንዲታዩ የማድረግ ሥራ ነበር የሚሰራው፤ በዚህ ሁኔታም አግላይና ጥላቻ ከባቢ ተፈጠረ። የመደብ ትግል የሚካሄድበት ዓይነት ሁኔታም ተፈጠረ።

…የመገናኛ ብዙሃን ምህዳሩ እየሰፋ ነው፤ አገሪቱ ተረጋግታ ወደ ትክክለኛው የዴሞክራሲ ስርዓት መሸጋገር ከቻለችና ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነ መልካም አጋጣሚ ነው።

በዚህ መሀል እንደምንም ተፍጨርጭረው አምስት ስድስት የሚሆኑ ሙያውን ተከትለው ለመስራት ቢሞክሩም ተደማጭነት አላገኙም። በዚህ ሁኔታ አንሰራም ያሉም ተሰደዱ። አሁን ላይ በውጭ አገር በሬዲዮ፤ በኢንተርኔትና በሳተላይት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዘርግተው ሲታገሉ ቆይተው አሁን ወደ አገር ቤት ገቡ። መንግሥት ከመጀመሪያው ክፋትና ጥላቻ አንጸባርቆ አፋኝ ህግ ማውጣቱ ነው ትልቅ በሽታ የሆነው፤

ከዚህ በተጨማሪ የግል መገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የአቅም፤ የገንዘብ፤ የሰው ኃይል ችግር ነበረበት። አንዳንድ ጊዜ አንድ ጋዜጣ ሁለትና ሦስት ሰዎች ያዘጋጁት ነበር። ስነ ምግባሩን ባልጠበቀ መልኩ አሉባልታ የሚራገብባቸውም ነበሩ። በስሜት የሚጽፉ፤ ሚዛናዊነትንና ሀቅን የመፈለግ ችግርም ነበር። ወገናዊነትም ይታይ ነበር። 40 እና 50 ጋዜጦችም ቢኖሩ በዚህ ችግራቸው ገበያው የሚተፋቸውና ተቀባይነት የሌላቸውም ነበሩ። በአጠቃላይ ከመንግሥት ተጽዕኖ በተጨማሪ ብዙ ውጥንቅጥ ችግር ነበረባቸው። አሁንም ችግሮቹ ቀጥለዋል።

አዲስ ዘመን፡– 97 ምርጫ በኋላ እንደ ሪፖርተር ያሉ መገናኛ ብዙሃን ሲቀጥሉ አብዛኞቹ ጠፍተዋል። ይህን ጊዜ ከግል መገናኛ ብዙሃንአንጻር እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ መላኩ፡– ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ አብዛኛዎቹ ሲጠፉ የተቀረነው እየተፍጨረጨርን እስከተቻለን እንሄድ በማለት መታገል ቀጠልን። በትግሉም ብዙ መከራ ደርሶብናል። መንግሥት የግል መገናኛ ብዙሃን ከተጠናከሩ ትልቅ ችግር ይሆናሉ ብሎ ስለሚያስብ ለማቀጨጭ የተለያየ ሥራ ሰርቷል። የህትመት ዋጋ በየጊዜው መቆለል፤ ህትመቱን ማዘግየት፤ ከዚያም አልፎ ስልታዊ በሆነ መንገድ ማዳከም ነበር። የእራሳቸውን ማተሚያ ቤት እንዳይከፍቱ በማሳደድ ማዳከምም ነበር። ጋዜጣ ያለው መጽሄት እንዳይኖረው ይደረግ ነበር።

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

ይህን ሁሉ ችግር ተቋቁመን እዚህ የደረስን መገናኛ ብዙሃን አለን። የንግድ ስልታችንን አስተካክለን፤ የሙያውን ሥነ ምግባር ሙሉ ለሙሉ ለመጠበቅ ባንችል እንኳን በተቻለ መጠን በዚያች መስመር ለመራመድ ጥረት በማድረግ እየተንገዳገድን እዚህ ደርሰናል። ይህ ግን በቂ ነው ወይ? ብትለኝ አይደለም።

አገሪቱ በመገናኛ ብዙሃን በብዙ ርቀት ወደኋላ ቀርታለችል። ጎረቤቶቻችንን ብትመለከት በመገናኛ ብዙሃን ዕድገት ሚዛን አንገናኝም። የመረጃ ነፃነት ማግኘት፤ የመንግሥት ጣለቃ ገብነት መቀነስ ጎረቤቶቻችንን ብዙ አራምዷቸዋል። በእኛ አገር አሁን የብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ሲመጡ ባለሃብቶችን መሳብ ጀመረ እንጂ፤ ባለሃብት የህትመቱን ሚዲያ አይጠጋውም ነበር። ይፈራ ነበር። ምክንያቱም ከመንግሥት ጋር መነካካት አልፈልግም በማለት፤

ግል መገናኛ ብዙሃኑን እንደዕጽ አዘዋዋሪ ነበር የሚመለከተው፤ ንግድና ኢንቨስትመንት መሳብ ካልቻልክ፤ እንደሌሎቹ ዘርፎች የታክስና ሌሎች ማበረታቻ ማግኘት ካልቻልክ ማንም አይጠጋህም። በዚህ የተነሳ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው የምንገኘው፤ ከእጅ ወደ አፍ ዓይነት ኑሮ፤ ብዙ ሰዎች «የኢትዮጵያን መገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪ» እያሉ ሲያወሩ ትሰማለህ። ማን ኢንዱስትሪ አደረገው? ገና በጉልት ንግድ ደረጃ ያለ ነው። ከጉልትና ከጀብሎ ንግድ ደረጃ አልወጣም።

አዲስ ዘመን፡– አሁን ላይ የመሻሻልና የማደግ አዝማሚያ አይታይባቸው?

አቶ መላኩ – ወደፊት ሊያድጉ ይችላሉ። አሁን እርግጥ ጋዜጦችና መጽሄቶች እየመጡ ነው። ግን በሚመጡበት ጊዜ እንዴት እየሰሩ ነው? ምን አይነት የንግድ ተሞክሮ ይዘው እየመጡ ነው? የሚለው በደንብ መታየት አለበት። ኢትዮጵያም ትኩረት እያገኘች ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት በአገራችን ይከበራል።

አዲስ ዘመን፡– አሁን ላይ በመገናኛ ብዙሃን መንግሥት የሚያደርሰው ችግር ምንድን ነው?

አቶ መላኩ፡– የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መንግሥት ስልጣን ከያዘ አንድ ዓመቱ ነው። በሽግግርም ላይ ነው። ብዙ ፈተናዎችም እንዳሉበት የማንክደው ሀቅ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጥተው ሲናገሩ የገባቸው ይመስለኛል። ግን በመገናኛ ብዙሃን ላይ ያለው አስተሳሰብ እስከታች ድረስ ለውጥ ማምጣት አልቻለም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መገናኛ ብዙሃን በነፃነት መረጃ ማግኘት እንዳለባቸውና በነፃነት መስራት እንዳለባቸው ይናገራሉ። ከዚያ በታች ያሉት ካቢኔውና ሌሎች የመንግሥት አካላት መገናኛ ብዙሃንን እንደ አራተኛ የመንግሥት አካል እያዩ አይደለም። አሁንም የመገናኛ ብዙሃን ዓላማ ምንድን ነው? ከበስተጀርባው ምንድነው ያለው? የሚለውን መተው አልቻሉም። የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ኤዲቶሪያል ነፃነቱ ተከብሮ ከተላላኪነትና ከአሽከርነት እንዲወጣ አላደረጉም። የግል መገናኛ ብዙሃን በነፃነት ይስራ። ሲያጠፋ እንደማንኛው ሰው በህግ ፊት ያለምንም ልዩነት በእኩልነት በህግ ስርዓት ይጠየቅ የሚለው አስተሳሰብ አልመጣም።

አንዱ የመንግሥት ባለስልጣን ያለምንም ማስረጃ ይነሳና ይህ መገናኛ ብዙሃን የነፍጠኛ አስተሳሰብ አለው ይላል። ባለስልጣኖቹ ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት አልቻሉም። መገናኛ ብዙሃንን አንድ ችግር ሲያይ እንደሚያጋልጥ አካል መመልከት ገና አልተጀመረም። በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 መንግሥት በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ ገብቶ እንዳይነካካና እንዳያማስል ክልከላ ጥሎበታል። ይህን የመንግሥት አካል ከላይ እስከታች ተረድቶ በአግባቡ የመወጣት ችግር አለ።

መገናኛ ብዙሃን የራሳቸው ሥነ ምግባር አላቸው። ፍትሃዊና ሚዛናዊ እንዲሆኑ ይጠበቃል። ማድረግ የሚገባቸውንም በዝርዝር ያስቀምጣል። አንዱ እየበደለህ ሌላውን አታሳጠ ነው የሚለው። ይህን መሰረት አድርገን በነፃነት እንድንሰራ ይደረግልን። ሰዎች እንደመሆናችን መጠን በስሜት ብናጠፋ በህግ እንጠየቅ። መንግሥት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማዕከላዊነት የታሰረ ጭንቅላቱን ይፍታ። እኔ ሊበራል ነኝ ስል፤ እናንተ ሊበራሎች ፀረ ህዝብ ኃይሎች ናችሁ እንባላለን። ለምን እንደዚያ እባላለሁ? እኔ አብዮታዊ ዴሞክራሲን መስማት አልፈልግም። እኔ ሊበራል ነኝ ካልኩ ለምን አልክ ማለት የለበትም። ምክንያቱም መብቴ ነዋ!

መገናኛ ብዙሃን የሃሳብ ማንሸራሸሪያ ሜዳ ናቸው። አንድ የምትባል ነጠላ ዜማ አለች። ማስተማርና ማዝናናት የሚባል፤ መገናኛ ብዙሃን ማስተማር፤ ማዝናናት አንችልም። እኛ የሚያዝናኑትና የሚያስተምሩትን የማስተናገጃ ሜዳ ነን። ከዚህ ባለፈ መረጃን ፈልፍለን በሀቀኝነት ለሚፈልግ መስጠት ነው ኃላፊነታችን፤ መረጃውን በተቻለ መጠን ሚዛናዊና ትክክለኛ ማድረግ ነው ግዴታችን፤ ይህ እንዲሆን ደግሞ መታገዝ አለብን። ምክንያቱን አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብምና።

አዲስ ዘመን፡– መገናኛ ብዙሃን የሚታገዙት ምንድነው?

አቶ መላኩ፡- በመጀመሪያ መንግሥት ማስተካከል ያለበት አስተሳሰቡን ነው። መገናኛ ብዙሃን የተለያየ ማለያ እናለብሰዋለን። በአዲስ ዘመንና በሪፖርተር የሚሰሩት ጋዜጠኞች የሚዲያ ሰዎች ናቸው። የተለያየ አተያይ ሊኖረን ይችላል። ወደ ሙያው ስንመጣ ግን ምልክታችን አንድ ዓይነት ነው።

ምክንያቱም የምናነበው ከአንድ ምንጭ ነው። የሙያ ሥነ ምግባር መመሪያው ተመሳሳይ ነው። ግን እዚያ ላይ ቢጫ፣ ሰማያዊና ቀይ ያለብሱንና የፓርቲ፤ የመንግሥት እና የምናምን እያሉ ይከፋፍሉናል። ይህ ዓይነት ሁኔታ አይሰራም። መንግሥት ለመገናኛ ብዙሃን እውቅና ሰጥቶ፤ ሜዳውንም ፈረሱንም አመቻችቶ ሥራበት፤ ህግ ግን አክበር ማለት ይገባዋል።

አዲስ ዘመን-በኢትዮጵያ ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ባለቤቶች በሙያው ላይ እጀ ረጅምነት ሌላው ችግር ነው። ይህ እንዲስተካከል ምንመሰራት አለበት?

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

አቶ መላኩ፡– በየትኛውም ዓለም የመገናኛ ብዙሃን ባለቤትነት ይኖራል። የባለቤቶቹ እጀ-ረጅምነት መገናኛ ብዙሃንን እንደሚያቀጭጭ የዓለም ተሞክሮ ያሳያል። ይህን ችግር ያለፉትን አገራት ተሞክሮ ቀስሞ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል። የባለቤቱና የመገናኛ ብዙሃኑ ድንበር መበጀትም አለበት። የመገናኛ ብዙሃን ኤዲቶሪያልም ከጣልቃ ገብነት ነፃ መሆን አለበት።

ይህ ሲሆን መገናኛ ብዙሃኑ ትርፋማ ስለሚሆን ትርፉን በተገቢው መልኩ ያገኛል። እየመጣ እጁን የሚከትት ከሆነ ግን ጊዜ ጥሎት ይሄዳል። ይህን ማድረግ ነው የሚበጀን፤ ከውጭ አገር የምናመጣውን ልምድ ግን ከአገራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ማስኬድ ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡– የሙያ ሥነ ምግባሩ እንዲከበር ተጽዕኖ ከማድረግ አንፃር ባለሙያዎች ተደራጅተው ምን መስራት አለባቸው ይላሉ?

አቶ መላኩ፡– እያንዳንዱ መገናኛ ብዙሃን በተቋማቸው ውስጥ የራሳቸውን ኤዲቶሪያልና ደንብ በማዘጋጀት በቅድሚያ መጠናከር መጀመር አለባቸው። ይህን ማድረግ ሲጀመር ወደ ባለሙያነት ያድጋል። ሙያዊ እያደገ ሲመጣ ህብረት ለመፍጠር ምክንያት አይደረድርም። የተለያዩ ማህበራትን በመቀላቀል አንድ ጠንካራ ሙያዊ ማህበር መፍጠር ይቻላል። ራስን በራስ የሚቆጣጠር ስርዓት መዘርጋትም ይቻላል። የኤዲተሮች ፎረምና ሌሎች አሰራሮችንም መዘርጋት ይቻላል። ይህን ለማድረግ ግን በመጀመሪያ በእያንዳንዱ ተቋም በሙያዊ መደራጀት ይገባል። ይህ ከሆነ የጋራ ሙያዊ ነገር ስለሚኖር ስለጋራ ጉዳይ አብረን እንሰራለን።

አዲስ ዘመን፡– ይህን የመደራጀቱን ሥራ ማን ይጀምረው ይላሉ?

አቶ መላኩ፡– አሁን ላይ አንዳንድ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። የፕሬስ ካውንስል ለማጠናከር እየተሰራ ነው። ያገባናል የሚሉ እየገቡበት ነው። የኤዲተርስ ፎርም የመመስረት እንቅስቃሴ እየተጀመረ ነው። የፕሬስ ህጉም ሲረቀቅ ባለሙያዎች ይገናኛሉ፤ ይወያያሉ። አንድ የሚያስተዳድረን ህግ ሲወጣ ቁጭ ብለን መነጋገር ስላለብን፤ በእነዚህ ሂደቶች ሁሉም ዓይኑን እየገለጠ ይሄዳል። ወሬውም እየሰከነ ሲሄድ እንነጋገራለን። ካልተነጋገርንና ካልተባበርን ስለምንወድቅ ወደ ትብብር እንመጣለን።

አዲስ ዘመን፡– ለመገናኛ ብዙሃን መዳከም ሌላው ችግር የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቶች ጥራት ያላቸው ባለሙያዎች አለማፍራታቸው ነውይባላል። ስለዚህ ምን ይላሉ?

አቶ መላኩ፡– የትምህርት ተቋሞቻችን ሁሉም የጋዜጠኝነት ሙያ ለማሰልጠን ከፍተዋል። አንዳቸውም ግን ብቁ ባለሙያ አያፈሩም። በፉክክር ሁሉም ከሚከፍቱ አንድ ጠንካራ ተቋም ከፍተው ከመገናኛ ብዙሃን ጋር አገናኝተው ባለሙዎችን ቢያፈሩ ይሻል ነበር።

 

ሁሉም አይቅርብኝ ብለው ከፍተው ተማሪዎቹ ጋዜጣ አያነቡም ትምህርት ቤታቸው ውስጥ ጋዜጣ አይሰሩም። እህ ሲባል፤ በጀት የለም ይላሉ። በጀት የሌለው ትምህርት ክፍል ከፍተው ልጆቹን መከራ እያሳዩአቸው ነው። ከትምህርት ቤት ሲወጡም ጋዜጠኛ ሳይሆን የህዝብ ግንኙነትና ሽያጭ ባለሙያ ነው የሚሆኑት፤ ይህ መስተካከል አለበት።

አዲስ ዘመን:- በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለውን ለውጥ እንዴት ያዩታልበቀጣይስ በመገናኛ ብዙኃን ዙሪያ ፈታኝ የሚሏቸው ጉዳዮች ካሉቢገልጹልኝ?

አቶ መላኩ:- መንግሥት ባለፈው አንድ ዓመት የታሰሩ ጋዜጠኞችን በመልቀቁና የሀሳብ ነፃነት በተግባር በመፍቀዱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ 40 ደረጃዎችን አሻሽላለች። ጋዜጠኛ ያልተሰረባት ብቸኛ አገርም ሆናለች። በዚህም የተነሳ የዓለምን የፕሬስ ቀን ለማክበር ተመርጣ እየተዘጋጀች ነው።

የመገናኛ ብዙሃን ምህዳሩ እየሰፋ ነው፤ አገሪቱ ተረጋግታ ወደ ትክክለኛው የዴሞክራሲ ስርዓት መሸጋገር ከቻለችና ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነ መልካም አጋጣሚ ነው። አሳሪ የነበረው ህግ እየተሻሻለ ነው። በነፃነት እንድንዘግብም እየተደረገ ነው። ጥሩ ነገር እንዳለ ያስታውቃል። አሁንም የመረጃ ሰጪ እጥረት ቢኖርም እንኳን ብዙ ነገሮች ተሻሽለዋል።

ይሁን እንጂ፤ የመንግሥት አፋኝነት ቢቆምም ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተዋንያንና መገናኛ ብዙሃኑን በቀጥታና በተዘዋዋሪ በማስፈራራት ለመጠምዘዝ ጥረት የሚያደርጉ ማፊያ መሰል ኃይሎች አሉ። እነዚህ ጽንፈኛ ቡድኖችና ግለሰቦች ለጋዜጠኞች ስጋት ናቸው።

መገናኛ ብዙሃንን እየመሩ መገናኛ ብዙሃኑን ላልተፈለገ ዓላማ የሚጠቀሙበት፤ ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር በማቀናጀት አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥሩ የሚችሉ ግለሰቦችና ሰብስቦችም አሉ። በተለይም በአሁኑ ወቅት በጅምላ የመፈረጅና የማጥቃት ሁኔታ ስላለ ጋዜጠኞች ወደተለያየ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመዘገብ ያስቸግራቸዋል። የደቦ ጥቃት ሊደርስባቸው ስለሚችልም ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል።

በመሆኑም፤ ራሳቸውን ከመንግሥት እኩል የሚያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ለመገናኛ ብዙሃን በጣም አስጊ ስለሆኑ የህግ የበላይነት መከበር አለበት። መንግሥትም ነጻነት ፈቅጃለሁ ብሎ እያስጨበጨበ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ የለበትም። ጥቅማቸውንና ዝናችን ይነካል ብለው የሚያስቡ ግለሰቦችና ስብስቦች በጋዜጠኞች ላይ ግብ አድርገው ጉዳት እንዳያደሩሱባቸው ጥበቃ ማድረግ ይገባዋል። ጋዜጠኞችም ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።

ዝግጅት ክፍሉ – አዲስ ዘመን የመረጠው ዋና ርዕስ ከቃለ ምልልሱ ውስጥ ቃል በቃል በተወሰደ ሃረግ ተለውጧል። ሃሳቡ እንዲጎላ በመፈለጉ የተደረገ ለውጥ መሆኑንን ማስታወስ እንወዳለን።

ዋናውን ቃለ ምልልስ አዲስ ዘመን ላይ ይመልከቱ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *