የአፋር ሕዝብ ፓርቲ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ከአራት ዓመታት በፊት የተፈረመውን ስምምነት በመሻር ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲያጤን ጥሪ አቀረበ። ገርብ ኢሳ፣ እንዱፎ እና አደይቱ የተባሉት ቀበሌዎች በታኅሳስ 2007 ዓ.ም ለአፋር ክልል እንዲሰጡ የተላለፈውን ውሳኔ የሶማሌ ክልል ሕገ–መንግሥታዊ አይደለም ብሏል ። የሶማሌ ክልል ስምምነቱ ህጋዊ አይደለም ብሏል
የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ሶስት የገጠር ቀበሌዎች ከአራት አመታት በፊት ወደ አፋር ክልል እንዲተላለፉ የተደረሰውን ውሳኔ መሻሩ አካባቢውን ወደ ቀውስ ሊመራው እንደሚችል የአፋር ሕዝብ ፓርቲ አስጠነቀቀ። ፓርቲው ውሳኔው እንደገና ሊጤን ይገባል ብሏል።
የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ሶስት የገጠር ቀበሌዎች ወደ አፋር ክልል እንዲተላለፉ ከአመታት በፊት የተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ ያደረገው በትናንትናው ዕለት ነበር።
የክልሉ መንግሥት ካቢኔ ገርብ ኢሳ፣ እንዱፎ እና አደይቱ የተባሉት ቀበሌዎች ክልሎቹን የሚያስተዳድሩ ባለሥልጣናት በታኅሳስ 2007 ዓ.ም. በደረሱበት ስምምነት መሰረት በአፋር ክልል ስር እንዲካተቱ የተደረገው ስምምነት ከሕገ–መንግሥቱ ጋር ይቃረናል ብሏል።
ውሳኔውን በሚመለከት የክልሉን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱላሂ መሀመድ “ቀበሌዎቹ በሕዝበ–ውሳኔ ወደዚያ የሔዱ” ባለመሆናቸው እና የአፋር ክልላዊ መንግሥት በቀበሌዎቹ የሚኖሩ ዜጎችን ሰላም እና መብት ማስከበር ስላልቻለ “ቀበሌዎቹ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሶማሌ ክልል እንዲሆኑ” ተወስኗል ሲሉ ተናግረዋል።
ውሳኔው የአካባቢውን የጸጥታ ሁኔታ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ የተጠየቁት አቶ አብዱላሂ “መጀመሪያም በሕገ–መንግሥቱ አግባብ አይደለም የተካሔደው። አንድ ነገር ሲደረግ በሕግ መሰረት መሆን አለበት። ያኔ ለወንበራቸው ጥቅም ሲሉ ነው የወሰኑት” ሲሉ መልሰዋል።
በአካባቢው የሚኖሩት አፋር እና ሶማሌ የግጦሽ መሬት ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ፉክክር ግንኙነታቸው ለዓመታት ሻክሮ ቆይቷል። ይሁንና የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት በተለይ ከአፋር እና ከሶማሌ ክልሎች ምሥረታ በኋላ ለግጦሽ ሳር ያደርጉት የነበረው ፉክክር ወደ ድንበር ይገባኛል ውዝግብ እና ግጭት አድጓል።
የሶማሌ ክልል ካሳለፈው ውሳኔ በኋላ የፌድራል መንግሥቱም ይሁን የአፋር ክልል በይፋ እስካሁን ያሉት ነገር የለም። የአፋር ሕዝብ ፓርቲ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ግን ውሳኔው “ኃላፊነት የጎደልው ብቻ ሳይሆ ችግሩን አርግቦ ለሰላም ከመስራት ይልቅ በእብሪተኝነት የተሞላና ጠብ አጫሪ” ነው ሲል ወቅሷል።
“በ2007 ዓ.ም. በሁለቱ ክልሎች መካከል የተደረገውን ስምምነት ውድቅ በማድረግ የሶማሌ ክልል የልዩ ኃይል አባላት ወደ ሶስቱ ከተሞች ለማሰማራት የወሰነው ውሳኔ ሁለቱን ክልሎች ወደ ለየለት ግጭት ሊያመራ” ይችላል ሲል ያስጠነቀቀው
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ውሳኔው “በአፋር እና በኢሳ ማኅበረሰብ መካከል ካላፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ የተከሰተውን ግጭት የሚያባብስ እና አካባቢውን ወደ ከባድ ቀውስ የሚመራ በመሆኑ የሶማሌ ክልላዊ መንግስ ወሳኔው እንደገና እንዲያጤን” ጥሪ አቅርቧል።
መሀል ሀገርን ከጅቡቲ በሚያገናኘው ዋና መንገድ ላይ መገኘታቸው ጠቃሚ ያደርጋቸዋል የሚባሉት ገርበ ኢሴ ፣እንዱፎ እና አዳይቱ ቀበሌዎች ባለፈ ግጭት በተከሰትበት መይደኔ በተባለ አካባቢ ከትናንት በስትያ በአፋር ልዩ ኃይል ተወሰደ በተባለው እርምጃ አስራ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን በሶማሌ ክልል የሲቲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዑመር አብዲ ለDW በስልክ አስታውቀዋል።
በሁለቱ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጋር በተያያዘ በሰው ህይወት ላይ ደረሰ የተባለውን ጉዳይ በሚመለከት የአፋር ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ካሎይታ ክልሉ ስለጉዳዩ ምንም የሚያውቀው ነገር አለመኖሩን አስረድተዋል።
በሁለቱ ክልሎች ለንትርክ መንስዔ ሆነው የቆዩትን የገጠር ቀበሌዎች ለአፋር የተሰጡበት ውሳኔ ተገቢ አይደለም በሚል የክልሉ ካቤኔ ውሳኔውን መሻሩን በመደገፍና በመይደኔ በአፋር ክልል ልዩ ኃይል ደረሰ የተባለውን ድርጊት በመቃወም ዛሬ በሲቲ ዞን ወረዳዎች እና በድሬደዋ ህዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል ፡፡
መሳይ ተክሉ – እሸቴ በቀለ
የሶማሌ ክልል መንግስት ካቢኔ ዛሬ ከሰዓት ባካሄደውሶማሌ የሚበዛባቸው ሶስቱን አወዛጋቢ ቀበሌዎች ወደሶማሌ ክልል እንዲዛወሩ ወስኗል::
ካቢኔው ማምሻውን ባወጣው ባለ8 ነጥብ መግለጫ በ2004ዓም ሶስቱ ቀበሌዎች ማለትም ገርበኢሴ; አዳይቱና ኡንዱፎ አብዛኛው ነዋሪያቸው ሶማሌ ሆኖ እያለ ወደአፋር ክልል እንዲካለሉ በወቅቱ የነበሩ አመራሮች የወሰኑት ውሳኔ የሀገሪቱን ህጎች የጣሰ በመሆኑ ከአሁን በሁዋላ እንደማይቀበለው አስታውቋል::
የአፋር ክልል የእነኚህን ቀበሌዎች ነዋሪዎች ፍላጎት ማሟላት አልቻለም ያለው መግለጫው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የፌደራል መንግስት የነዋሪዎችን መሰረታዊ ፍላጎቶች በማሟላት ረገድ የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጠይቋል::
ሶስቱን ቀበሌዎች የሶማሌ ክልል የፀጥታ ሃይል ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር ፀጥታቸውን እንዲያስከብር ያዘዘው መግለጫው የክልሉ የፀጥታ ሃይሎች ከክልሉ ወሰን ሳይወጡ ድንበር አካባቢ ያለውን ፀጥታ እንዲያጠናክሩም አዟል::
ስለመግለጫው ያላቸውን አስተያዬት የጠቅኳቸው የአፋር ክልል የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊው አቶ አህመድ ካሎይታ ስለመግለጫም ምንም መረጃ አንደሌላቸውና ክልሉ ወደፊት አቋሙን እንደሚያሳውቅ ገልፀውልናል::