ለውጡ ነጻ ያወጣው ፕሬስ ሙያዊ ግዴታውን እያዳበረ ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ሰፊ ሚና ይጫወታል የሚል ተስፋ ቢኖርም ተስፋው አሁን አሁን አሳሳቢ ሆኗል። ዓለም ኢትዮጵያ ላይ ስለ ፕሬስ ነጻነት ሲመክርና ፌስት ሲያደርግ የመንጋ መሪዎች የህ ዓለም ያከበረውን ለውጥና የፕሬስ ነጻነት ወደ መቃብር እየሰደዱት፣ የጥላቻ ዘምቻቸውን እያራገቡበት፣ በንጹሃን ደም የስልጣንና የነዋይ ጥማታቸውን ለማሳካት እየተጠቀሙበት ነው። መንጋዎችና የመንጋው መሪዎች ገና ብዙ ያደርጋል። ምክንያቱም አብዛኞች ዝም ብለዋቸዋል፣ ይህ ብቅ ጥልቅ የሚለው ገጀራ ነገ ወደ ቤታቸው እንደሚገባ የዘነጉ ይመስል።

ቀደም ሲል ” ፕሬሱን ነጻ ልቀቁ” የሚል ትግልና ትንቅንቅ ነበር። ዛሬ ዓለም እኛ ዘንድ መጥቶ የነጻ ፕሬስ ልደቱን ሲያከብር፣ እነዚህ የሚንጫና የደም አራራ የተጠናወታቸው ወገኖች ፕሬሱን አንቀው ይዘውታል። መጠቀሚያቸው አድርገውታል። በወረቀት፣ በአየርና በሞገድ ፣ በማህበራዊ ሚዲያ፣ ተረባርበውበታል። ከዚያም በላይ መንጎቻቸውን በሳንቲም እየደለሉ ሌሎችን ያፍኑበታል።

በኢትዮጵያ እያደር የሚሰማው ጉዳይ እጅግ ዘግናኝ ነው። ምን እየሆነ እንዳለ ሁሉ ለመገመት የሚይዳግት ነው። ትናንሽ መንግስታት መንጋ እየነዱ ከህግና ከስርዓት በላይ ሆነዋል። ሰው ዘቅዝቆ መስቀል፣ ለስራ ጉዳይ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን መደብደብና መግደል፣ በፈላ ውሃ ማቃጠል፣ በስለት መጉዳት፣ ማሰር፣ ማሳደድ የእለት ተዕለት ተግባር ሆኗል።

የጋዜጠኛነት ሙያ በራሱ ያለበት የጨዋነትና የገለልተኛነት ችግር እንዳለ ሆኖ፣ በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች ለስራ የሚሰማሩ ዘጋቢዎች በብሄራቸው፣ በሚሰሩበት ሚዲያና በሚናገሩት ቋንቋ ሳቢያ፣ ከሁሉም በላይ ጎሳን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ያጋልጣሉ በሚል የሚደርስባቸው ችግር አሳሳቢ ነው።

Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

መንግስት ፕሬሱን ከአፈና ሲፈታው የጎበዝ አለቆችና የመንጋ መሪዎች መልሰው ተከርቸም ከተውታል። ፕሬሱን በጎሳ ላይ ተክለውት፣ ባለሙያዎቹን በጎሳና በክልል ከፋፍለው እጅግ የሚያሳዝን በድልና ግፍ በውክልና እያከናወኑ ይገኛሉ። በልገጣፎ የሕዝብን ድምጽ ለማሰማት በስፍራው የተገኙ ተደብድበዋል። በአማራ ክልል በተመሳሳይ መልኩ አስነዋሪ ተግባር ተፈጽሟል። ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሌሎች አካባቢ የሆኑ ባለሙያዎች የመዘገባቸው ጉዳይ የነብስ ውሳኔ እስከመሆን ደርሷል። በኮንሶ እንዲህ ሆኗል

በኮንሶ ከተማ የደረሰብኝ ዝርፊያ፣ ድብደባ፣ እስርና እንግልት በአጭሩ ይህን ይመስላል! By Dawit Wasihun Kassa

በአኪያ ሚዲያ/ፕሮሞሽንና ኢንተርቴይመንት በሰላም ጉዳይ ለምንሰራው ዘገባና ዶክመንተሪ ፊልም ቀረፃ ለማካሄድ ትላንት ወድያ ዕለተ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ለኮንሶ ዞኑ ጉዳዩን የሚያሳውቅና ፈቃድ መጠየቅያ ደብዳቤና አስፈላጊ ማቴሪያሎችን ይዤ ኮንሶ ገባሁ።

ሞተር ተከራይቼ ወደ ዞኑ አስተዳደር በመሄድ የስራውን ሁኔታ የሚገልፅ ደብዳቤ በመስጠትና ስለስራው ከዞኑ ኮሚኒኬሽን ሃላፊ ጋዜጠኛ ሰራዊት ከተባለ የተረጋጋና አሪፍ ሰው ጋር ተነጋግረን ፈቅዶልኝ፣ አንድ የዞን ከፍተኛ ባለሞያ መድቦልኝና ለመንቀሳቀሻ የሚሆን ሞተር ሳይክል ሰጥቶን ወጣን።

የዞኑ መንግስትን አሳውቄና ባለሞያ ተመድቦልኝ ቀረፃ አካሄድን። የጎሳ መሪ የሆነው አቶ ገዛኸኝን ኢንተርቪው ስለምናደርገው ወደ መኖሪያ ቤቱ ሄደን ስላጣነው ለአርብ ጠዋት ተቀጣጥረን ተመለስን።

አርብ ጠዋት የተመደበልኝ ባለሞያ እስኪመጣ ካደርኩበት ፔንሲዮን ወጥቼ ቁርስ ልበላ በሞተር ሲሄድ ነው ካሜራ ያዩ ወጣቶች ያስቆሙን።

ወጣቶች አስቁመው “ለምንድነው የምትቀርፅው?” አሉኝ። እኔ ሁኔታውን በርጋታ አስረዳኋቸው። ያኔ ነው ወጣቶቹ መሳደብና መዛት ጀመሩ፤ እየበዙም ሆነ። “እኛ ስንበደል በነበር ሰዓት የት ነበራችሁ? ማነው እኛን አድትሰልል የላከህ?” እያሉ ከበው ሊደበድቡኝ ሲቃረቡ አንድ የፖሊስ አባልና ትራፊክ ፖሊስ ደርሰው ወደ ድርጅት ቢሮ ይዘውኝ ሄዱ።

ቢሮ እንደገባን የፈቀዱልኝን የዞኑን ሰዎች ጠራሁ፣ ስለሁኔታ ተነጋገርን። ዞኑ ፈቅዶልኝ እንደሆነ ተማመን። ያኔ እኛ ቢሮ ውስጥ ስናወራ የስራ ሃላፊዎችና ወጣቶች ቢሮን ሞልተውት ነበር። ለዕርድ እንደተዘጋጀ በግ ነበር ያስቀመጡኝ።

“ይህማ የኮንሶን ህዝብ ሊሰልል ነው የመጣው” እያሉ ግርግር ፈጠሩ። የድርጅት ሃፃፊውና አንድ ፖሊስ “ላንተ ደህንነት ሲባል ቶሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንውሰድህ” አሉኝ። ፖሊስ ሁኔታውን እኪያመቻች ቢሮ ውስጥ እየገቡ ይሰድቡኝና ይመቱኝ ጀመሩ።

እኔን ለመደብደብ/ለመግደል ከተሰበሰቡት በግምት ወደ 200 የሚሆኑ ወጣቶን በፖሊስ መኪና ታጅቤ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄድን። እዛ ስደርስ ቢሮ አስቀምጠውኝ ወጣቱን ሊያረጋጉና የስራ ሃላፊዎች በእኔ ጉዳይ ስብሰባ ሊያደርጉ ሄዱ።

የፖሊስ አዛዡና የመንግስት ሃላፊዎች አድርሰውኝ እንደሄዱ ነው በሌሎች ፖሊሶች ወደ ጣቢያው ታሳሪ ማቆያ ወስደው ድብደባ የፈፀሙብኝና የያዝኩትን ገንዘብ የዘረፉኝ። “አንተ የኮንሶን ህዝብ ልትሰልል የተላክ ነህ” ይሉ ነበር። ሶስት ፖሊሶችና አንድ የደንብ ብልስ ያለበሰ የትራፊክ ፖሊስ አባል ነበሩ የደበደቡኝና የዘረፉኝ።

ደብድበው አልበቃ ሲላቸው ፀጉሬን በመቀስ መሃል ለመሃል አድርገው ቆረጡት። በህይወት ከዛ ቦታ እንደማልወጣ ሲዚቱ ነበር።

Image may contain: one or more people and closeup

በጣም ያሳዘነኝ አንዱ ደብዳቢ ፖሊስ ለታሳሪዎች በኮንስኛ (አንዱ መልካም ሰው እንደተረጎመልኝ) “ ቀጥቅጣችሁ_ግደሉት የኮንሶ ጠላት ነው” ብሎ አሳልፎ ለታሳሪዎች ሰጠኝ። በጣቢያው ያሉት ታሳሪዎች ብዛት ያስፈራ ነበር (በግምት 250 ይሆናሉ)። ያ ሁሉ ይቅርና ለአምስት ሆነው ቢደበድቡኝ ይገሉኝ ነበር።

በሚገርም ሁኔታ አምላክ ትረፍ ሲለኝ አንድ መልካም ሰው በመካከላቸው አለ። እኔን ለድብደባ ወደ ሽንት ቤት አጠገብ እንደሰዱኝ ይህ መልካም ሰው ይመጣና በኮንስኛ ብዙ ከተነጋገራቸው በኋላ ሊደበድቡኝ የነበሩት ሁሉም ትተውኝ ሄዱ። አንዳንዶችም ያፅናኑኝ ጀመሩ።

እንዳልደበደብ ያደረገው መልካም ሰው አጠገቤ ተቀምጦ ምን እንዳደረኩ ጠይቆ ተረዳ። እኔም ምን ብለሃቸው ነው የተውኝ ስለው “ፖሊሱ ደብድባችሁ ግደሉት” እንዳላቸው እና እሱ ደግሞ “እንዳይደበድቡኝ እንዳሳመናቸው” ነገረኝ።

ቀኑን ሙሉ እዛው ዋልኩ። 10 ሰዓት ሲል የስራ ሃላፊዎችና የፖሊስ አዛዡ መጡና እኔን ከቢሮ ሲያጡኝ ከታሳሪዎች መካከል ይመጡና አገኙን። ተደብድቤ ፀጉሬ ተቆርጦ ሲመለከቱ ደነገጡ። የደበደቡኝንና የዘረፉኝን ፖሊሶች አሳይቼ እንድፈታ አደረጉኝ።

ከተፈታው በኋላም “ወጣቶች ካገኙህ ይገድሉሃልና መኪና ፈልገን ከዚህ ከተማ እንድትወጣ እናደርጋለን” አሉና መኪና ተፈልጎልኝ በህይወት ተርፌ ወጣሁ።

ሶስት የመንግስት ሃላፊዎችና አራት የፖሊስ አባላት እንዲሁ ከታሳሪዎች መካከል ያን መልካም ሰው አምላክ ባያስቀምጥልኝ በህይወት ተርፌ አልወጣም ነበር። አምላክ ይመስገን! የረዳችሁኝ መልካም ሰዎች ከልብ አመሰግናለው!

የሀገሬን ነባራዊ ሁኔታ ጠንቅቄ ባውቅም ትላንት የተፈጠረብኝ ነገር ለሀገሬ የማበረክተውን መልካም አስተዋፆ አጠናክሬ እንድቀጥል ያደረገኝ መጥፎ ግን አስተማሪ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

በፖሊስ ጣብያ በነበረኝ ቆይታ የታዘብኩትንና የተነገረኝን አሰቃቂ ግፎች የምፅፍ ይሆናል።

የሚደወልልኝ ስልክና ቴክስት በመብዛቱ መመለስ ባልችልም ለተጨነቃችሁልኝ በሙሉ አመሰግናለው! አምላክ ያክብርልኝ!

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *