“እናንተ ባትመርጡኝ እንኳን አካባቢው ከዳስ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እስኪወጣ አምባሳደራችሁ ሆኜ እሰራለሁ፡፡” አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ

‹‹ገንዘብህን ብቻ ልከህ ትምህርት ቤቱን ማሰራት እንደምትችል ብናውቅም መምጣትህ ብቻ ለዋግ ህዝብ ዜና ነው፡፡›› የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች፡፡

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ሰቆጣ ገብቷል፤ የሚያስገነባውን ትምህርት ቤት የመሠረት ድንጋይም ዛሬ ያስቀምጣል።

በዓለም የአትሌቲክስ ውድድሮች እያሸነፈ ሰንደቁን ከፍ አድርጎ ኢትዮጵያውያንን የደስታ እንባ ያራጨ፤ በደስታ ያስፈነደቀ፡፡ የሌላ ፕላኔት ፍጡር እስከመባል የደረሰ፡፡ ማሸነፉ ሳይሆን መሸነፉ ለዓለም ጆሮ ዜና ይሆን ዘንድ የተናፈቀለት፡፡ ከማሸነፉ በፊት የማይናገር፡፡ በውድድር ላይ በቡጢ ተነርቶ ሁሉ በፍቅር ያቀፈ የተግባር ሰው፡፡ ኢትዮጵያን በዓለም መድረኮች ከፍ አድርገው ካሳዩዋት ኢትዮጵያውያን መካከል ተጠቃሽ ነው፤ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ።

Related stories   Egypt-Sudan alliance shifting in row with Ethiopia over Nile dam

የሁለት ጊዜ የ10 ሺህ ሜትር የኦሎምፒክ ውድድር እና የአራት ጊዜ የርቀቱ የዓለም ሻምፒዮን አሸናፊም ነው፡፡ ከ1 ሺህ 500 ሜትር እስከ ማራቶን ከስቶትጋርት እስከ አትላንታ፣ ከሲድኒ እስከ ዙሪክ፣ ከሎንዶን እስከ አቴንስ፣ ከቤጂንግ እስከ በርሊን እያቀያየረ አሸንፎ ያላጠለቀው ሜዳሊያ፣ ያልበጠሰው ሪቫን፣ ያልሰባበረው ክብረ ወሰን እና ያላሻሻለው ሰዓት የለም፡፡ 27 ጊዜ በአትሌቲክሱ ዓለም ክብረ ወሰኖችን በመሰባበር ዓለምን ያስደመመው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ፡፡

አሁን ደግሞ በሌላ የህዝብ ፍቅር እና እምባ ታጅቦ በዋግ ሹሞች መናገሻ ሰቆጣ ትናንት ማምሻውን ገብቷል፡፡ ተማሪዎች ኃይሌ ኃይሌ እያሉ የከተማዋን መንገዶች በፍቅር ዞሩ፡፡ ወጣቶች በአካባቢው የባህል ልብስ ተውበው በጀግና አቀባበል ተቀበሉት፡፡

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

የአባቶች ምርቃት የኦሎፒክ መልስ ትዝታውን ቀሰቀሱት እና አይኖቹ እምባ አቀረሩ፡፡ ኃይሌ ትናንት ማምሻውን ሰቆጣ ከተማ ሲገባ ልዩ አቀባበል እና ስጦታዎች ተበረከቱለት እና ብዙ መናገርን በማይሻው አንደበቱ ይህችን ብቻ ተናገረ ‹‹እናንተ ባትመርጡኝ እንኳን አካባቢው ከዳስ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እስኪወጣ አምባሳደራችሁ ሆኜ እሰራለሁ፡፡›› ተባብረን ያሁኑን ታሪክ በመቀየር ወደ ቀደመ ዝናችን መመለስ ‹‹ይቻላል›› ስለዚህ ሁላችሁም በየድርሻችሁ የተግባር ሰው ሁኑ፡፡

አክብረኸን ስለመጣህ፣ ድምፃችንን ስለሰማህ እና ዛሬም እንደ ትናንቱ አርአያችን ስለሆንክ እናመሰግንሃለን ያሉት ዋጎች ቀጥለውም እንዲህ አሉ ‹‹ገንዘብህን ብቻ ልከህ ትምህርት ቤቱን ማሰራት እንደምትችል ብናውቅም መምጣትህ ብቻ ለዋግ ህዝብ ዜና ነው፡፡››

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ዛሬ ከሰቆጣ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት አካባቢ በምትገኘው የፃግብጅ ወረዳ በገልኩ አንደኛ ደረጃ የዳስ ትምህርት ቤት በመገኘት ትምህርት ቤቷን ደረጃዋን ጠብቆ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ትምህርት ቤቱን በቶሎ አስገንብቶ ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ለማድረስ ኃይሌ ቃል መግባቱ ይታወሳል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስድስት መደበኛ ትምህርት ቤቶች የዳስ ናቸው፡፡ በብሄረሰብ አስተዳደሩ በተለያዩ አከባቢዎች ደግሞ 324 የዳስ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ በሳተላይት ትምህርት ቤቶችም 550 የዳስ መማርያ ክፍሎች እንደሚገኙ የብሔረሰብ አስተዳደሩን ትምህርት መምሪያ ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከሰቆጣ Amara mass media

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *