አከራካሪው የእስልምና ሃይማኖት ሰባኪ ዛኪር ናዪክ ከህገወጥ ገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ በህንድ አቃቤ ህግ ክስ ተመሰረተባቸው።

በስደት የሚኖሩት ዛኪር ምንጩ ያልታወቀና በህገወጥ መንገድ የተገኘ እስከ 28 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ አንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ሲሆን የተመሰረተባቸው እሳቸው ግን ክሱን ሙሉ በሙሉ በመቃወም ክደዋል። ከዚህ በተጨማሪም ዛኪር የሽብር ጥቃትን የሚያነሳሱ የጥላቻ ንግግሮችን አስተላልፈዋል የሚል ክስም ቀርቦባቸዋል።

የ53 ዓመቱ ዛኪር ተራማጅ የእስልምና ፍልስፍና ተከታይ ሲሆኑ ‘ፒስ ቲቪ’ በተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ስብከት ያስተላልፋሉ። ጣቢያው ምንም እንኳን ህንድ ውስጥ የተከለከለ ቢሆንም እስከ 200 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች እንደሚከታተሉት ታውቋል።

ዛኪር ናዪክ ያቋቋሙትና የቴሌቪዥን ጣቢያውን ሙሉ ወጪ የሚሸፍነው ‘ኢስላሚክ ሪሰርች ፋውንዴሽን’ የተባለው ድርጅት መቀመጫው በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዱባይ ነው።

የቴሌቪዥን ጣቢያው ከህንድ በተጨማሪ በብዙ ሃገራት የተከለከለ ሲሆን ባንግላዲሽ ደግሞ ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች። በፈረንጆቹ 2016 በባንግላዲሽ ለተከሰተው የሽብር ጥቃትም መንግስት ይህንኑ ጣቢያና ዛኪር ናዪክን ተጠያቂ ያደርጋል።

ዛኪር ናዪክ ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ ወደ እንግሊዝ እንዳይገቡ የተከለከሉ ሲሆን የሚያስተላልፏቸው መልእክቶች ተገቢ ያልሆኑና ወጣቱን ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚመሩ ናቸው ብሏል የእንግሊዝ መንግስት። የተለያዩ ሃገራት እግድ የጣሉባቸው ዛኪር በአውሮፓውያኑ 2017 በጥገኝነት ወደ ማሌዢያ አቅንተዋል።

BBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *