ብሩክ አብዱ ሪፖርተር

በቀጣይ ዓመት ሊደረግ የታቀደውን ጠቅላላ ምርጫ በወቅቱ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ዝግጅቱን እያፋጠነ እንደሚገኝ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ስብሳቢዋ ይኼንን ያሉት ሐሙስ ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ለጉብኝት ከመጡት የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄረሚ ሀንት ጋር በእንግሊዝ ኤምባሲ ከተወያዩ በኋላ ነው፡፡

ወ/ሪት ብርቱካን ምርጫ ቦርድ የ2012 ምርጫን በወቅቱ ለማድረግ ዝግጅቱን እያፋጠነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ለምርጫው በዝግጅት ሒደት ላይ ነው ያለነው፡፡ አሁንም ቢሆን ምርጫውን በተፋጠነ ሒደት በተያዘለት ጊዜ ለማድረግ ነው የእኔ ተቋም እየሠራ ያለው፡፡ ግን ዝግጅቱ በጣም በርካታ መልኮች ያሉት ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ገና ጅማሮ ላይ ነው ያለነው፡፡ በነገራችን ላይ ቦርድ እንኳን አልተሟላም፡፡ በሚቀጥሉት ሳምንታት በተጨማሪ የቦርድ አባልነት አራት ሰዎች ፓርላማ ቀርበው ይሾማሉ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

‹‹የምርጫውን ሒደት በፍጥነት ለማድረግ እንሞክራለን በሒደቱ ላይ ግን የሚያጋጥም ችግርና ደንቃራ ካለ ያንን በተጨባጭ እያየን እንወስናለን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄረሚ ሀንት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት የአፍሪካ አገሮች ባደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያን ቀጣይ ምርጫ ለመደገፍ መንግሥት የ15.5 ሚሊዮን ፓውንድ ወይም የ582 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ያለችበትን የለውጥ ጊዜ ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

የእንግሊዝ  መንግሥት ይኼንን ድጋፍ የሚያደርገውም በኢትዮጵያ ታሪክ እየተከሰተ ያለው አስደሳች ለውጥን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ በመግለጽ፣ ይኼም የሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ደፋርነት ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉትን መንግሥት ለመምረጥና የማይፈልጉትን ለመጣል ዕድል ያገኛሉ ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ይኼ ድጋፍ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) አማካይነት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድ ቀጣዩን ምርጫ በብቃት፣ በገለልተኝነትና በታማኝነት እንዲያከናውን ለማገዝ፣ ለሕዝቡ በየወቅቱ አስፈላጊ መረጃዎችን በፍጥነት ለማዳረስ የኮሙዩኒኬሽን ድጋፍ ለማድረግ፣ ከምርጫ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ግጭቶችን ለመፍታትና ሥጋቶችን በመለየት እንዲሠራ ለማገዝ ይውላል ሲሉ፣ የዩኤንዲፒ የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ ሉዊስ ቻምበርሌይን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

‹‹ምርጫን ተከትለው የሚመጡ ግጭቶች ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ ከዋና ዋና የፍትሕ ተቋማት ጋር በመተባበር እንሠራለን፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የእንግሊዝ መንግሥት ያደረገውን ድጋፍ ያደነቁት ወ/ሪት ብርቱካን፣ ድጋፉ ትርጉም ያለው ነው ሲሉም አወድሰዋል፡፡

‹‹የእንግሊዝ መንግሥት የፖለቲካና የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ እንደፈለገ ገልጸውልናል፡፡ ይኼ በጣም መልካም ነገር ነው፡፡ በእኛ በኩል እስካሁን ከነበሩት የተለየ ምርጫ ለማድረግ ቁርጠኝነቱ አለ፡፡ ይህ ግን በቁርጠኝነት ብቻ የሚመጣ አይደለም፡፡ በተለይ የገንዘብ ወጪው መንግሥት ከሚችለውም በላይ ስለሆነ ከአጋሮቻችን ድጋፍ እንፈልጋለን፤›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *