ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ትግራይ – ባለቤት ያጣች የአፈና የእስርና የጨለማ ደሴት ሆናለች (ዲያስፓራ የዓረና መድረክ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ)

ግራኝ መሐመድ መጣብህ ተነስ ተዋጋ” እያሉ በመቀስቀስ ሕብረተሰቡን ማሸበር ከጀመሩ ውለው አድሯል:: በተለይም መንግስት ያወጣቸውን የይቅርታና የምህረት አዋጆች በክልሉ ተፈፃሚነት እንዳይኖራቸው አድርጓል:: ከህወሓት የተለየ አመለካከት አላችሁ ተብለው በሰበብ አስባብ ለዓመታት የታሰሩ ዜጎችም እስካሁን ድረስ በህወሓት የጨለማ ጉድጓድ ውስጥ ታጉረው ይገኛሉ:: በቅርቡ በመቀሌ በኩይሓ በዓዲ ግራትና በሌሎች ቦታዎች እየተካሄዱ ያሉት ዜጎችን የማፈናቀል የማሰርና የመንጥር ዘመቻዎችም መነሻቸው ህዝቡ ከህወሓት ውጭ ሌላ አማራጭ ሃሳብና ግንኙነት እንዳይኖረው

ይድረስ ለኢትዮ  ያ ጠቅላይ ሚኒስቴር
ክቡር ዶክተር ዓቢይ አህመድ
አዲስ አበባ

ጉዳዩ:- በዲያስፓራ የዓረና መድረክ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር አባላት በትግራይ ክልል በወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ ስላለው አፈናና ሰብኣዊ መብት ረገጣን በማውገዝ ያወጡት የጋራ መግለጫና ውሳኔን ይመለከታል ::

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆይ !!

እኛ በውጭ ዓለም በሰሜን አሜሪካና በሌሎች ክፍላተ ዓለም በተለያዩ የማሕበረሰብ ስብስቦች ተደራጅተን በመንቀሳቀስ ላይ የምንገኘው የትግራይ ተወላጆች የተጀመረውን የለውጥ ውጋገን የሁላችንም ድምር የትግል ውጤት ስለሆነ የኢትዮ ያ ሀገራችን ትንሳኤ እውን ሊሆን ይችላል የሚል ብሩህ ተስፋ አሳድሮብን ነበር:: በተለይም ከአርባ ዓመት በላይ በህወሓት ባርነታዊ አገዛዝ ስር ወድቆ በስቃይ ላይ የሚገኘውን የትግራይ ህዝብ ከጅብ ምንጋጋ አላቆ ነፃ በማውጣት አዲስ ምዕራፍ ይከፍት ይሆናል በሚል ተስፋና እምነት የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በአወንታዊ ጎኑ በማየት ትክክለኛውን ፈር ይዞ እንዲጓዝ የበኩላችንን ድርሻ ስንወጣ ቆይተናል::

ይሁን እንጂ ዛሬ በትግራይ አካባቢ ያለው ፓለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚዊና ማሕበራዊ ገፅታ ስንመለከት ለብዙዎቻችን እንቆቁልሽ ፣ አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ ሆኖብን ይገኛል:: ጭቁኑ የትግራይ ህዝብ የለውጡን ተቋዳሽ መሆን ቀርቶ እንደ ህዝብም የኔ ወገን ነው ብሎ ከጎኑ የሚቆም ፣ አስተዋሽና ለችግሩ ደራሽ የሚሆን ባለቤት አሁንም አላገኘም:: በትግራይ ምድር ትላንትም ጨለማ ነው  ዛሬም ጨለማ ነው ያለው:: ሌላ ቀርቶ በሌሎች ክልሎች ትኩረት ተሰጥቷቸው የአመራርና የመዋቅር ለውጥ ሲደረግ እናያለን:: ይበል የሚያሰኝ ነው:: ትግራይ ግን የኢትዮ ያ ህዝብ አሽቀንጥሮ የጣላቸውን የህወሓት ወንጀለኛ መሪዎች መሸሸጊያና የቆሻሻ ስርዓትን መጣያ ሆና ትገኛለች:: በሌሎች ክልሎች በተለለይም ወጣቱ ትውልድ የመደራጀት ፣ የመናገር ፣ ሰላማዊ ስልፍ የማድረግ፣ መሪዎቹን የመተቸትና የማውረድ ነፃነት ሲያገኝና የለውጡን ፍሬ ተጠቃሚ ሲሆን እያየን ነው:: ይህም የሚያኰራና የሚያስቀና ስራ ቢሆንም በትግራይ ይባስ ብሎ ከለውጡ በፊት ከነበረው ሰቆቃና አፈና አሁን የባሰበት ሁኔታ ላይ ደርሶ ህዝቡ አቤት የሚልበት የፍትሕ ቦታና ባለቤት አጥቷል::

ከማሀል ሀገር የተባረሩትን የህወሓት መሪዎች ህዝቡን የቁጭታቸው መወጣጫ በማድረግ ሆን ብለው የለውጡን አጋርና ተጠቃሚ እንዳይሆን በመጋረድ በጅሆ (ሆስቴጅ) ይዘውት ይገኛሉ:: በእነርሱ ላይ ያነጣጠረውን የህዝብ ተቃውሞም አቅጣጫውን በመቀየር የትግራይ ህዝብን ለማጥፋት የሚደረግ ትግል አስመስለው በማቅረብ “ግራኝ መሐመድ መጣብህ ተነስ ተዋጋ” እያሉ በመቀስቀስ ሕብረተሰቡን ማሸበር ከጀመሩ ውለው አድሯል:: በተለይም መንግስት ያወጣቸውን የይቅርታና የምህረት አዋጆች በክልሉ ተፈፃሚነት እንዳይኖራቸው አድርጓል:: ከህወሓት የተለየ አመለካከት አላችሁ ተብለው በሰበብ አስባብ ለዓመታት የታሰሩ ዜጎችም እስካሁን ድረስ በህወሓት የጨለማ ጉድጓድ ውስጥ ታጉረው ይገኛሉ:: በቅርቡ በመቀሌ በኩይሓ በዓዲ ግራትና በሌሎች ቦታዎች እየተካሄዱ ያሉት ዜጎችን የማፈናቀል የማሰርና የመንጥር ዘመቻዎችም መነሻቸው ህዝቡ ከህወሓት ውጭ ሌላ አማራጭ ሃሳብና ግንኙነት እንዳይኖረው በማፈን ወደደም ጠላም የህወሓት ወንጀለኛ መሪዎችን ከለላና መሸሸጊያ ሆኖ እንዲያገለግል ለማድረግ የማይሸርቡት ሴራና የማያካሂዱት የውሸት ዘመቻ የለም:: ፍትሕ የጠየቁ ወይም ተቃውሞ ያሳዩ ዜጎች ሁሉ “ዓቢይ መጥቶ ሲያድንህ እናያለን” እየተባሉ እንደ ከሓዲና ጠላት እየታዩ ባንዳ ፣ እንክርዳድ ፣ እሾህ አሜኬላ ፣ ዓይጥ፣ ቋቁማ ፣ ወዘተ የሚሉትን አስከፊና አሳፋሪ ስማ ስሞችን እየተለጠፈባቸው በተወለዱባትና እትብታቸውን በተቀበረባት ምድር ላይ እንዲሸማቀቁና ከሕብረተሰቡ እንዲገለሉ እየተደረገ ይገኛል:: ከዚሁ አስከፊ በደልና ስነ ልቦናዊ ጥቃት ለማምለጥ ያላቸው ዕድልም ሀገራቸውን ጥለው ወደ ስደት መሄድ አሊያም ባርነትን አሜን ብለው በመቀበል እንደ ህፃን ልጅ አፍህን ያዝ እየተባሉ እየተኰረኰሙ መኖር ነው:: በቅርቡ በሀገራቸው ተሰፋ ቆርጠው እንጀራ ፍለጋ ባህር ሲሻገሩ ያለቁትን የትግራይ ተወላጆች የዚህ ሁሉ የጥቃት ሰለባ ውጤቶች ናቸው:: በዚሁ አጋጣሚም በእነዚህ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው አስደንጋጭና አሳዛኝ ሞት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እየገለፅን ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ሁሉ መፅናናትን እንመኛለን::

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆይ !!

በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃትና ሶቆቃ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሰወራል ብለን አናምንም:: እኛን እንደሚያስጨንቀን ሁሉ ለእርስዎም ሊያስጨንቅዎት እንደሚችል በሚገባ እንረዳለን:: ዛሬ ይህንን ግልፅ የሆነ የብሶት ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ዶክተር ዓቢይ አህመድ ስናቀርብም እንደ አንድ የሀገር መሪ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ወንድም ኢትዮ ያዊ ሆነው በቅርብ የሚያውቁትን

የታገሉለትንና መቀሌ ድረስም በመሄድ በአደባባይ የመሰከሩለትን ህዝብ ካለው አስከፊ ሁኔታ እንደሌላው አካባቢ ነፃ እንዲወጣ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ የሚል ተስፋና እምነት ስላለንም ጭምር ነው:: ከዚሁ ፅኑ እምነት በመነሳትም የጉዳዩን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የበኩሉን የመፈትሔ እርምጃ ይወስድ ዘንድ ያሉንን ስጋቶችና ጥያቄዎች እንደሚከተለው እናቀርባለን::

 

  1. በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል በወገኖቻችን ላይ እየተካሄደ ያለው የማሰርና የማጥቃት ተግባር የዜጎችን ሕገ መንግስታዊ፣ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የሚጥስ ሕገ ወጥ ድርጊት በመሆኑ እያወገዝን – ጥቃቱን በአስቸኳይ እንዲቆም ፣ የታሰሩትን ወገኖቻችን ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና ወንጀል ፈፃሚዎቹንም ለፍርድ እንዲቀርቡ የኢትዮ ያ ፌዴራላዊ መንግስትና ሌሎች ጉዳዩን የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል አስተዳደር አካላት ሁሉ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ የወገን አድን ጥሪያችንን እናቀርባለን::
  2. አወዛጋቢና ደም አፋሳሽ ሆኖ የቆየውን የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ጉዳይ በሚመለከት በሁለቱ አጎራባችና ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም ፣ የጋራ ጥቅምና የሀገራችንን ሉዓላዊ ክብር በሚያስጠብቅ መልኩ ለመፍታት ጉዳዩን ከህወሓት እጅ ወጥቶ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዓቢይ አህመድ መሪነት መንግስት ለመንግስት ግንኙነት መጀመሩን የሚታወስ ነው:: ይሁን እንጂ ህወሓት ዛሬም በዳር ድንበሩ ጉዳይ ላይ በጋሃድና በስውር ጣልቃ እየገባ ሆን ተብሎ ተንኳሽ ተግባራትን በመፈፀም ላይ ይገኛል:: የህዝቡን ሰላም፣ ስነ ልቦናና ቁስል ዳግም ለመጉዳትና ለመቀስቀስ ሲባል ፌዴራል መንገስት የማያውቃቸውንና በይፋ ያላፀደቃቸውን የሐሰት ካርታዎች በማውጣትና በማሰራጨት እኖሆ የአካባቢውን ህዝብ እያስጨነቀ ይገኛል:: ህወሓት ይህ ዓይነቱ ወራዳ ተግባር የሚፈፅምበት ዋና አላማም በአንድ በኩል “ዳር ድንበርን በሚመለከት ከዶክተር ዓቢይ አህመድ አስተዳደር ምንምመፍትሄ አታገኙምና እርማችሁን አውጡ” የሚል የተሳሳተና ተስፋ አስቆራጭ መልእክትን ሆን ተብሎ ለአካባቢው ህዝብ በማስተላለፍ የትግራይ ህዘብንና መንግስትን ለማጋጨት ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ በህወሓት ላይ እየተነሳ ያለውን የህዝብ ተቃውሞ መልኩንና አቅጣጫውን በመቀየር የትግራይ ህዝብ ዋናው የችግሩ ምንጭ የሆነው አፋኝ ስርዓትን ትቶ በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ተጠምዶ እየተተራመሰ እንዲኖር የሚደረግ ሴራ መሆኑን በሚገባ ተገንዝበኗል:: የሀገርን ዳር ድንበር የሚመለከት ጉዳይ የመንግስት ስራ እንጂ የአንድ የፓለቲካ ድርጅት ሃላፊነት አይደለም:: ስለሆነም ህወሓት ከዚሁ ግብረ ሽበራ ተግባሩ አደብ እንዲገዛና እጁን ከትግራይ ህዝብ ጫንቃ እንዲያነሳ እናሳስባለን:: መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አስፈላገውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን::

 

  1. በትግራይ ህዝብ ደምና ስም ለዓመታት ሲነግዱ የቆዩት የህወሓት መሪዎች ጦርነትንና ህዝብ ከህዝብ ጋር ማጋጨትን እንደ ልዩ ሙያ አድርገው በመውሰድ ዛሬም በመሬት ላይ የሌለ የጦርነት ድባብ በመፍጠር በህዝቡ ላይ እያካሄዱ ያሉት የሽብርና የስነ ልቦና ጦርነት እናወግዛለን:: እንደሚታወቀው በኢትዮ ያ አንድ መንግስት ፣ አንዲት ልዑላዊት ሀገርና አንድ መከላኪያ ሰራዊት ነው ያለው:: ይሁን እንጂ እንደ ዘመነ መሳፍንት አንድ የሽፍታ ቡድን ራሱን መንግስት ነኝ እያለ በመሰየም “ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት” እያለ ጦርነት በማወጅ ሀገርንና ህዝብን የማሸበርና የማተራመሰ መብትም ፣ ሕጋዊ መነሻንና ሕጋዊ ውክልናም የለውም:: ህወሓት ሕብረተሰቡን ነጋ ጠባ ጠላት መጣብህ እያለ ዕረፍት በማሳጣት ህዝቡ አማራጭ መንገድ አጥቶ ተስፋ በመቁረጥ ሳይወድ በግድ “የሌላ ጅብ ከሚበላኝ የወንዜን ጅብ ይብላኝ “ ብሎ እንዲወስንና ዝንተ ዓለሙን የጥቂት መሪዎች ተከላካይና አገልጋይ ሆኖ እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን በሚገባ እንገነዘባለን:: የትግራይ ህዝብ ላለፉት አርባ ዓመታት ያሳለፈውን ደማዊ የእልቂት ዘመን እንዳይበቃው ዛሬም ገና ቁስሉን ሳይሽርና ዕረፍት ሳያገኝ ለዳግም ጥፋትና መከራ ለመዳረግ አካኪ ዘራፍ እያሉ ፀረ ጥቅሙ እንዲሰለፍና ከገዛ ወገኖቹ ጋር ደም እንዲቃባ ለማድረግ እየተፈፀመ ያለው የጦርነት ቅስቀሳ አጥበቀን እናወግዛለን:: ድርጊቱም ዓለም ያወገዘውን የግብረ ሽበራ ተግባር ስለሆነ በይፋ መወገዝ ያለበት ፀረ ሰላም ስራ ነው ብለን እናምናለን::

 

  1. በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ በተወሰኑ ሰዎች ትግል ብቻ የመጣ ሳይሆን በሀገር ውስጥም ሆነ በመላ ዓለም የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችም ላለፉት በርካታ ዓመታት የህወሓት/ኢሕአዴግ ጨቋኝ ስርዓትን በመቃወም ባደረጉት ተጋድሎ ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል:: በመሆኑም የትግራይ ህዝብ የትግሉንና የለውጡን ባለቤት ለመሆን ማንም የማይቸረው ሕገ መንግስታዊ መብቱ ስለሆነ ልክ ሌሎች በትግላቸው ያገኙትን ለውጥ ያላንዳች መሸማቀቅና ስጋት ነፃ ተጠቃሚ እየሆኑ እንዳሉ ሁሉ ትግራዋይም እኩል መብት ሊኖረው ይገባል:: ህዝቡ መብቱን ለማስከበር በሚያደርገው ጥረት የትግል ድርሻውን የሚወጣበት ሁኔታና መጫወቻ ሜዳ ሊመቻችለት ይገባል:: በመሆኑም መንግስት የትግራይ ህዝብን ክብር ከአሮጌው የህወሓት ቡድን በላይ መሆኑን ተገንዝቦ ከጥቂት አፈንጋጭ መሪዎች ጋር ጊዜ ከማጥፋት ፣ ከመሻኰት፣ ከማስተመምና እሸሩሩ ከማለት ይልቅ ከብዙሃኑ ህዝብ ጋር በመወገን ሕገ ወጦች መተላለፍ የሌለባቸውን ቀይ መስመር በማስቀመጥ ሃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን::

 

  1. በትግራይ ክልል ያለውን የፓለቲካ ምሕዳር ፣ የሀብት ክፍፍል ፣ የፀጥታ ሁኔታና የሚዲያ አጠቃቀም ሲታይ ሁሉም መቶ በመቶ የአንድ ድርጅት የህወሓትን ፈላጭ ቆራጭ ስልጣን የሚጠብቁ የመጨቆኛ መሳሪያዎች ናቸው:: ይህ የተዛባ የሀብት ክፍፍል በማንኛውም እንቅስቃሴ ህወሓት የበላይነቱን ይዞ እንዲቀጥልና የፈለገውን ለማድረግ የሚያስችሉት ጡንቻዎች ናቸው:: በአንፃሩ ሕገ መንግስቱ የሰጣቸውን መብት ተጠቅመው በሕግ ተመዝግበው ሕግንና ስርዓትን አክብረው በሰላማዊ መንገድ በክልሉ

የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፓለቲካ ሐይሎች ግን ምንም ድርሻ የሌላቸው ከሁሉም ሀገራዊ ጥቅማ ጥቅም የተገለሉና የተከለከሉ ናቸው:: ተጠቃልሎ ሲታይ በትግራይ ትልቁ ዓሳ ትንሹን ዓሳ እየበላና እያሳደደ የሚኖርበት ምሕዳር ነው ያለው:: ይህ ኢፍትሓዊና ሚዛኑን ያልጠበቀ የሀብት ክፍፍል ካልተስተካከለና ስርዓት ካልያዘ ደግሞ በክልሉ የሚካሄደው የለውጥ ሂደት ዞሮ ዞሮ በጉልበተኛው እጅ መውደቁ አይቀሬ ነው:: ስለዚህ አንድ ድርጅት ሁሉም ነገር በሞኖፓ ይዞ ሌላውን በረሃብ አለንጋ እየቀጣና እየጨፈለቀ የሚኖርበት ዘመን አብቅቶ በሕግ ማዕቀፍ ላይ የተደገፈ ፍትሓዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ስርዓት እንዲኖር ማድረግ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን:: ህወሓቶች በጠራራ ፀሐይ የዘረፉትን የሀገርና የህዝብ ሃብት አልበቃ ብሏቸው በየዓመቱ በትግራይ ህዝብ ስም ለክልሉ የሚጎርፈው በጀትም ለልማት ሳይሆን የዓፋኙን ስርዓት ገደብ የለሽ ዘረፋ የሚያጠናክር ነው:: ስለሆም የሀገርና የህዝብ ሀብት የፀረ ለውጥ ሐይሉን ጡንቻ ማጠናከሪያና ለውጡን ማደናቀፊያ እንዳይሆን መንግስት የበኩሉን ጥበቃና ቁጥጥር እንዲያደርግ እንጠይቃለን::

  1. በኛ እምነት ምርጫ ማለት አንድ ህዝብ የለውጡን ባለቤትና የመንግስት ስልጣን ምንጭ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ሉዓላዊ መብት ነው ብለን እናምናለን:: በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን እየተካሄደ ያለው የለውጥ ጉዞም ዋና አላማውና ግቡ ፍትሓዊ ፣ ታኣሚኒና ሚዛናዊ የሆነ ነፃ ምርጫን በማካሄድ በህዝብ ይሁንታ የቆመ መንግስትንና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማረጋገጥ ነው:: ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሱትን መሰናክሎች ሳይወገዱ ፣ ቅድመ ሁኔታዎችን ሳይሟሉና ስርዓት ሳይዙ በክልሉ የሚካሄደው ምርጫ እንደተለመደው ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር ውጤት ይኖሯል ብለን ፍፁም አናምንም:: በመሆኑም በትግራይ የዜጎችን ነፃ እንቅስቃሴ፣ የሕግ የበላይነት ፣ የሕግ ዋስትናና ከለላ ፣ የእስረኞችን መፈታት ፣ የጠበበውን የፓለቲካ ምሕዳር፣ በዝርፊያ ላይ የተመሰረተው የሀብት ክምችትና ክፍፍል ፣ በአጠቃላይ የህዝቡን ደመ ነብስ የሆኑትን ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ ነፃነቶችን ሳይረጋገጡ ምርጫ እንዲካሄድ መፍቀድ ማለት በህዝቡ ላይ መፍረድና መቀለድ ነው ብለን እናምናለን:: ምርጫው በነበረው ሕግና ስርዓት ይቀጥል ማለት ደግሞ የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ዜጎች እስር ቤት ውስጥ ታጉረው ባለጡንቻው ህወሓት ግን ብቻውን ተወዳድሮ ብቻውን የሚያሸንፍበት ድራማ ይቀጥል ማለት ነው የሚሆነው:: ይህ ከሆነ ደግሞ መድረኩ የህወሓት መፈንጫ ነው የሚባለው እንጂ ምርጫ ነው ብለን ልንጠራው አንችልም:: ስለሆነም የትግራይ ህዝብን ለጅብ አሳልፎ በመስጠት ምን አገባኝ ተብሎ የሚተው ሳይሆን መንግስት ባለው ሃላፊነት ይህ ባለቤትና አማራጭ ያጣ ህዝብ አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት መፃኢ ዕድሉን የሚወስንበትና መብቱን የሚያስከብርበት ምቹ የትግል ሁኔታን ለመፍጠር ህዝባዊ አደራውንና ሃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን::

ክቡር ጣቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ጥያቄያችንንና የወገን አድን ጥሪያችንን ተቀብለው አሁን ያለው የሀገራችን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ችግሮችን ለመፍታት ለሚያደርጉት ጥረት በቅድሚያ እናመሰግናለን :: እኛም ከማንም ከምንም በላይ የህዝባችንን ድህንነት፣ ሰላም፣ አንድነትንና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ስለሚያንገበግበን ይህንን አስከፊ ገፅታ እስከሚለወጥ ድረስ ለለውጥ በሚደረገው የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው የትግል እንቅስቃሴ – ከህዝባችን ጎን ተሰልፈን ድርሻችንን እንደምንወጣ በዚሁ አጋጣሚ ደግመን ለመግለፅ እንወዳለን::

እግዚኣብሄር የሀገራችንና የህዝባችንን ሰላም ይጠብቅ
ኢትዮ ያ እናታችን በልጆችዋ ተከብራ ለዘላለም ትኑር

 

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝብና ታጋይ ሐይሎች በሙሉ !!

በሀገራችን በመካሄድ ላይ ስላለው የለውጥ ጉዞንና በተለይም በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ስላለው ዓፈናን አስመልክቶ ለመላ ህዝብና ታጋይ ሐይሎች ሁሉ የሚከተለውን አጭር መልእክት ለማስተላለፍ እንወዳለን:: የሩቁን ትተን የትናንትናው የሐምሳ ዓመት የትግል ታሪካችን መለስ ብለን ስንቃኝ በትክክል የሚያሳየን ስንተባበር እንደምናሸንፍ ስንበታተንና ስንለያይ ግን እንደምንሸነፍ ነው:: በሌላ አነጋገር ተባብረን ታግለን ያገኘነውን ድል ገና እግር ሳይተክልና ለፍሬ ሳይበቃ ተበታትነን ስናፈርሰው ነው የሚያሳየን:: ዛሬም ይህ አንድ ዓመት ያስቆጠረውን የለውጥ ጉዞ ተመሳሳይ ዕጣ ፋንታ እንዳይደርስበት ትልቅ ስጋት አለን:: ጨቋኝ መደቦች በተለይም ህወሓት ይህ ደካማ ጎናችንንና ሗላቀር የፓለቲካ ባህላችንን ከኛ በላይ ጠንቅቆ ስለሚረዳ እኛን መስሎ እኛን ለማጥፋት ሲጠቀምበት ቀይቷል:: ለአርባና ለሐምሳ ዓመታት ያህል በዘር በሀይማኖትና በቦታ እየተሸነሸነ ሲሰራበት የቆየውን የለያይተህ ግዛ ኢንጂነሪግ በያንዳንዳችን አእምሮ ውስጥ የጥላቻ መርዝን ተክሎ አልፏል:: በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች እእየተከሰቱ ያሉት አንዳንድ አላስፈላጊ ግጭቶችም መነሻቸው የዚሁ የጥላቻው መርዝ ውጤቶች መሆናቸውን እሙን ነው::

በህዝብ ትግል የመጣው ለውጥ ህወሓትን ከማሀል ሀገር ተባሮ ወደ ትግራይ መሄዱ ብቻ እንደ ግብ ወስደን ትግሉ ያለቀ መስሏችን የምንዝናና ጥቂቶች አይደለንም:: ነገር ግን ህወሓት ዘወር አለ እንጂ አልሸሸም:: መልኩን ፣ ስልቱንና ስትራተጂውን ቀየረ እንጂ አልጠፋም:: ህወሓት የትግራይ ህዝብን እንደምሽግ ተጠቅሞ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ አሁንም አለሁ አልሞትኩም ማለቱ አልቀረም::

በፌዴራል ደረጃም በተለያዩ የስልጣን እርከኖች ተሰግስጎ ሀገሪቱን እሱ በሚፈልገው መንገድ ለመምራት የሞት ሽረት ትግሉን እያካሄደ ይገኛል:: ችግሩ የህወሓት መኖርና አለመኖር ጉዳይ ብቻ አይደለም:: ህወሓት በአካል ገሸሽ ቢልም አመለካከቱ አሁንም ገና ከአእምሯችን አልተፋቀም:: የስለላ መረቡ ፣ ለዓመታት የዘረፈውን የኢኮኖሚ ሀብት ፣ ቁልፍ የሆኑትን የሚዲያ አውታሮች ፣ ለዓመታት የተካነው የማስመሰል ፕሮፓጋንዳና ሌሎች ስውር ደባዎችን እየተጠቀመ ከመጋረጃው በስተጀርባ ሆኖ ራሳችን ዋጋ ከፍለን ያመጣነውን ለውጥ መልሰን ራሳችን እንድናፈርሰው እንቅልፍ አጥቶ እየሰራ ያለው ህወሓት መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል:: የህወሓትን የጭቆና መረቦች ሰብሮ በአሸናፊነት ለመውጣት ደግሞ በቅድሚያ የሚከተሉትን የተዛቡ አመለካከቶች ማስተካከልና ፈር ማስያዝ የግድ ይላል::

 

  1. ችግሮችን ብልጭ ባሉ ቁጥር ከቅርጫፋቸውና ከውጤታቸው ከመታገል ይልቅ ግንዱን መገርሰስ ወይም ምንጩን ማድረቅ የትግላችን ተቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት እንላለን:: በመሆኑም የችግሩን ምንጭ ከሆነው ህወሓት ጋር ተደራድሮ በሀገራችን ምድር ላይ የተረጋጋ ሰላምና ዕድገት ይመጣል ብሎ ማሰብ የዋህንት ነው:: የህወሓት አምባገነንነት መነሻው ከራሱ ተፈጥራዊ ባህሪይ የሚመነጭ እንጂ በግምገማ ወይም በድርድር ሊስተካከል የሚችል ተራ ያስተዳደር ጉድለት አይደለም:: ስለዚህ ተበታትነን በያለንበት ጊዜያችንና ጉልበታችንን ከማባክን ይልቅ ትግላችንን በማቀናጀት ወደ አንድ የጋራ ጠላት ማነጣጠር የመስዋእትነታችንን ዋጋ የሚቀንስ ብቻ ሳይሆን የበለጠ ውጤታማም እንሆናለን:: ዋናውን ችግር ህወሓት ቁጭ ብሎ እያለ እሱን ትተን ከውጤቱና ከቅርጫፉ ጋር ብንታገል ጠላቶቻችንን መልሰው እንዲጠናከሩ ዕድል ከመስጠት አልፎ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም::

 

  1. ከድፍርስ የዳበሳ ጉዞ ወጥተን ጠላንትንና ወዳጅን የለየ የጠራ ትግል ማካሄድ በለውጥ ሐይሉና በህዝባችን መካከል አንድነትንና መተባበርን ያጠነክራል:: የአላማ ጥራት ፣ የአላማ ፅናት ፣ ድርጅታዊ ጥንካሬና የሰላ ስትራተጂ መኖር የለውጥ ባቡሩ ከሐዲዱ እንዳይወጣ የሚቆጣጠር የትግሉ ደም ስር ነው:: ይህን ሐቅ በመገንዘብ ዛሬ በሀገራችን የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በሚመለከት ከየአቅጣጫው እየተነሱ ካሉት ሃሳቦች ውስጥ ወዴት ነው እየሄድን ያለነው? ለለውጥ እንታገላለን ከተባለ ማንን ነው የምንታገለው? ከማን ጋር ሁነን ነው የምንታገለው? የትግሉና የለውጡ ባለቤትስ ማን ነው? ፀረ ለውጥ ሐይሉስ ማን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ህዝቡ እንደ ነጭና ጥቁር ቀለም ግልፅ በሆነ መልኩ ትክክለኛውን መልሰ ማገኘት ይገቧል:: ዛሬ ህወሓት የትግራይ ህዝብን ልብ ለማስሸፈት ሲባል ጠላቶቼ የሚላቸውን ባንዳ፣ እንክርዳድ ፣ ምርኰኛ፣ የደርግ ርዝራዝ ፣ ወዘተ እያለ የማጥቃት ዘመቻውን እያካሄደ ይገኛል:: በሌላው ወገን ግን ለሰላም ሲባል የህወሓትን ሰይጣናዊነትና ላለፉት ዘመናት በሀገርና በህዝብ ላይ የፈፀማቸውን የክህደትና የዓፈና ወንጀሎችን አታገልጡ እየተባለ እኖሆ ዛሬም የልብ ልብ እየተሰማው በኛ ላይ ሲፎክር፣ ጦርነት ሲያውጅ፣ ሲያሸብርና ሲያተራምስ ይገኛል:: በዚህ ምክንያት ብዙ ሰው ግራ እየተጋባና እየሰጋ ከመደመርና የለውጡን አጋር ከመሆን ይልቅ ጥጉን ይዞ ዳር ቆሞ ተመልካች መሆን እየመረጠ ይገኛል::

 

  1. ለውጡን በተፈለገው ፍጥነትና ጥራት እንዳይጓዝ እንቅፋት እየሆነ ያለው አግላይነትን ፣ ጥላቻነትንና ምንአገባኝንትን የመሳሰሉት በታኝ ፣ ሗላቀርና አፍራሽ አመለካከቶችን መታገልና ማስወገድ የግድ ይላል:: “ህወሓት ከክልላችን እንኳን ተጠራርጎ ሄደ እንጂ ስለትግራይ ህዘብ ምን አገባን እዚያው እርስ በራሳቸው ይናቆሩ” በማለት በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል በራስህ ወገን ላይ የደረሰ በደል አድርጎ አለመልከት እየተበራከተ ሄዷል:: ይህ አግላይና የምንአባገባኝነት ዝንባሌ ፀረ ለውጥ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ድህንነትና አንድነትም አደጋ ነው:: ስለሀገርና ስለለውጥ ስናስብ በቅድሚያ ሁላችንም መገንዘብ ያለብን ትልቁ ጉዳይ አንድን ህዝብ እያገለሉና እየጠሉ ፍፁም ሀገርን መውደድና የኢትዮ ያዊነት ጠበቃ መሆን አይቻልም:: አንድን ህዝብ እያገለሉና እየጠሉ ፍፁም ለመቶ ሚሊዮን ህዝብ የሚሆን ለውጥ ማምጣትና ወደፊት መራመድ አይቻልም:: አንድን ህዝብ እያገለሉና እየጠሉ ፍፁም የፍትሕና የዴሞክራሲ አራማጅ መሆን አይቻልም:: በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብን ከህወሓት ሰው በላ መሪዎች ጋር ደምሮ በጀምላ በመጥላት ሀገርን መገንባትና አንድነትዋንም መጠበቅ አይቻልም:: አንድ ሰው ጤናማ ሆኖ መንቀሳቀስ የሚችለው እኮ ሁሉም አካላቱ ጤናማ ሲሆኑ ነው:: ኢትዮ ያም ሰላሟን ጠብቃ ጤናማ ሀገር ሆና ወደፊት መራመድ የምትችለው ሞሶሶ ሆነው ያቆሟትን ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ትልቅ ትንሽ ሳይባባሉ ሁሉንም በእኩል አቅፋ ስትሄድ ብቻ ነው:: ስለሆነም መፍትሄው በሕብረተሰባችን ውስጥ ለዓመታት የተተከለውን የህወሓት የጥላቻ አሻራ ጠራርጎ በማጥፋትና በማፅዳት በምትኩ ለዘመናት ተባብረንና ተፋቅረን አብረን እንድንኖር አስተሳስረውን የቆዩትን የብሄራዊ እሴቶቻችንን ገመዶች ተመልሰው በቦታቸው እንዲተከሉና እንዲያብቡ ማድረግ የሁላችንም ሃላፊነትና ተቀዳሚ ተግባር ነው ብለን በፅኑ እናምናለን::

 

Related stories   "የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎችን ላለመላክ የወሰነው የማይታዘዝና የማያጎበድድ መንግሥት ይመጣል የሚል ስጋት ነው"አንዳርጋቸው ፅጌ

በማጠቃለል በጭቁን ህዝብ መካከል መሰረታዊ ቅራኔ የሚባል ነገር ፈፅሞ እንደሌለ እሙን ነው:: ነገር ግን ሁሉ ጊዜ የቅራኔ፣ የጥላቻ፣ የጦረነትና የእርስ በርስ መናቆር ምንጭና ተጠቃሚዎች መሪዎች ናቸው:: ህወሓትም የመቶ ሚሊዮን ኢትዮ ያውያን ጠላት እንጂ ላንዱ ህዝብ ወዳጅ ለሌላው ህዝብ ግን ጠላት ሆኖ እንደማያውቅ ያለፈውን ትተን ዛሬ በትግራይ በጠራራ ፀሐይ ላይ እያካሄደ ያለውን ዓፈና ራሱ ዋቢ የማያስፈልገው ምስክር ነው:: ህወሓት ዓይን ብሌኑ ስልጣኑንና ገንዘቡን እንጂ የትግራይ ህዝብ አይደለም:: ስለዚህ ይህ አረሜናዊ ስርዓት ከጭቁኑ የትግራይ ህዝብ ነጥሎ ከነ ግሳንግሱ ማስወገድ ለትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላ ሀገራችንም እፎይታና ሰላም የሚሰጥ ነው:: ስርዓቱን ለመጣል ደግሞ ለትግራይ ተወላጆች ብቻ የሚተው ሳይሆን ለፍትሕና ለሰብኣዊ ፍጡር ነፃነት ቁመናል የሚሉት ኢትዮ ያውያን ወገኖች ሁሉ ግዴታና ሃላፊነትም ጭምር ነው:: ስለሆነም የትግራይ ህዝብን ከህወሓት ዘመናይ

ባርነትን ነፃ ለማውጣትና ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ ኢትዮ ያዊነት ሃላፈነታችንን እንድንወጣ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን:: ካለፈው ተመኩሮዎቻችን ከስህተታችንና ከውድቀታችን መማር ብልህነት ነው:: ነገር ግን ከተመኩሯችን ሳንማር ሁሉጊዜ ተመሳሳይ ስህተት እየፈፀምን ታጥቦ ጭቃ እየሆን መኖር ግን የውርደት ውርደትና የውድቀት ውድቀት ነው የሚሆነው:: ስለዚህ አስተሳሰባችን ከ16ኛው የዘመነ መሳፍንት የተሻለ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰለጠነ አስተሳሰብ የተላበሰ ስብእና እንዲኖረን ግድ ይላል::

ጥላቻ የዕድገትና የአንድነት ነቀርሳ ነው
ፍቅር የሰላምና የመተባበር ምንጭ ነው

 

Related stories   “አቡነ ማቲያስ የሰጡት መግለጫ የግላቸው እንጂ የቅዱስ ሲኖዶስ ወይም የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ አይደለም”

የተከበርከው የትግራይ ህዝብ ሆይ

ለትግራይ ህዝብ ፣ ለትግራይ ምሁራን ፣ ለትግራይ ወጣቶችና ታጋይ ሐይሉ በሙሉ ማስተላለፍ የምንፈልገው መልእክትም አንድና አንድ ነው:: የትግራይ ህዝብን ለጥቃት ለውርደት ለስደትና ለረሃብ የዳረገው ከህወሓት በላይ ሌላ ጠላት የለውም:: ትግራዋይ ትግራዋይን ለማጥፋት እርስ በርሱ እንደጠላት እየተፈራረጀና እየተባላ እንዲኖር እያደረገ ያለው ምንጩ ህወሓት ራሱ በፈጠረው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ደማዊ ሰርዓት ውጤት እንጂ ዛሬ በኩይሓ በመቀሌ በዓዲ ግራትና በሌሎች የትግራይ ቦታዎች ዜጎችን እያሰረና እያሰቃየ ያለው ከኦሮሞ ወይም ከአማራ የመጣ ጠላት አይደለም:: በሀገሩ በማንነቱና በነፃነቱ ኰርቶ ይኖር የነበረውና የጀግንነት የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት እየተባለ ይታወቅ የነበረውን ኩሩ የትግራይ ህዝብ ዛሬ ትግራይን በጥላቻ የታጠረች የሽብር ደሴት ሆና እንድትቀር እያደረጋት ያለው ራሱ ህወሓት በፈጠረው የለያይተህ ግዛ መርዝ ያመጣው ጣጣ እንጂ ከሌላ ጎረቤት ድንበርን ተሻግሮ የመጣብን ችግር አይደለም:: ስለዚህ የችግሩ ምንጭም የችግሩ ሰለባም እዚያው በትግራይ ምድር ነው ያለው:: የችግሩን የመፍትሄ መድሃኒት ደግሞ በራሱ በትግራይ ህዝብ እጅ ነው ያለው:: አንቱ ሲባል የነበረውን ህዝብ ዛሬ ነፃነቱንና ሰብኣዊ ክብሩን ብቻ አይደለም የተነጠቀው ብሄራዊ መለያው የሆኑት ወርቃማ ታሪኩን አኩሪ ባህሉን ብሄራዊ አንድነቱንና ማንነቱን ተራክሷል ፈራርሷል ተበትኗል::

ለባዕዳን ወራሪዎችን ያልተንበረከከ ጀግና ህዝብ ዛሬ እጃቸውን በደም የተነከሩ ፣ ዓይናቸውን በፍቅረ ንዋይ የታወሩ፣ አእምሯቸውን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምትሓት የደነዘዙ የህወሓት ጉግ ማንጉግ መሪዎችን መጫወቻ ፣ ምርኮኛና የቁም እስረኛ ሆኖ ሲታይ እጅጉን ያሳዝነናል፣ ያሳፍረናል፣ ያስቆጣናልም:: ትናንት እንደነ አሉላ አባ ነጋ ፣ ዮሐንስ ፣ እንደነ ሐየሎም አርኣያና ሌሎች በሽዎች የሚቆጠሩትን ብሄራዊ ጀግኖች የተወለዱባትና የተቀበሩባት ትግራይ ዛሬ የህወሓት ፈርጣጭ መሪዎችን መሸሸጊያና መደበቂያ ሆና ሲታይ ውርደትና ሐፍረት ከመሆኑም በላይ የትግራይ ህዝብን ጨዋነትና የሞራል እሴት አይመጥንም:: ስለዚህ የትግራይ ህዝብ መድህን ህወሓት ሳይሆን መቶ ሚሊዮኑ የኢትዮ ያ ህዝብ መሆኑን ቀደም ሲል በዓድዋ በዘመናችን ደግሞ በባድመ በተግባር አስመስክሯል:: ዛሬ በህወሓት ደጋፊዎችና አባላት ዘንድ እየታየ ያለው አመለካከት ግን ይህንን እውነታ የሚቀበል አይደለም:: በአንፃሩ ህወሓትን ከሀገርና ከህዝብ በላይ አድርጎ በማየት እንደ ጣዖት የሚያመልክ አመለካከት ነው:: ይህ ዓይነቱ ጭፍንና ሗላቀር አመለካከት ደግሞ ፀረ ሕገ መንግስቱ፣ ፀረ ዴሞክራሲና ፀረ ዕድገት ከመሆኑም በላይ ውሎ አድሮ ዋጋ የሚያስከፍል የጥፋት መንገድም ነው:: ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ማለቂያ ከሌለው ጭቆና ተላቆ ዘላቂ ሰላምና እፎይታ ማግኘት የሚችለው የሁሉንም ችግሮች ምንጭ የሆኑትን የህወሓት መሪዎች ላንዴና ለመጨረሻ ከጀርባው አሽቀንጥሮ በመጣል ቦታውን ለባለተራው ለአዲሱ ታጋይ ትውልድ እንዲለቁ ሲያደርግ ብቻ መሆኑን በፅናት እናምናለን:: ስለሆነም የትግራይ ህዝብ የጎደፈውን ወርቃማ ታሪኩ ለማደስ፣ የጥላቻ አጥሩን ሰብሮ በመውጣት ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እኩል ለመራመድና ነፃነቱን መልሶ ለመቀዳጀት ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን::

ትግራይ የሐቀኛ ኢትዮ ያዊነትና ጀግንነት ተምሳሌት እንጂ
የአፈና የጥቃት የእስርና የጨለማ ስርዓት ደሴት ሆኖ አትኖርም

 

Related stories   ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ200 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ