ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

አጫጭር የውጭ ዜናዎች

የቻይና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዩ በአሜሪካ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

የቻይና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዩ በአሜሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፊታችን ሃሙስ  ጀምሮ በአሜሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት የሚያደርጉ መሆኑን የቻይና ንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሊዩ ጉብኙቱን የሚያደርጉትም በአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት ነው ተብሏል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዩ በአሜሪካ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝትም በሀገራቱ  መካከል ባለው የንግድ ግንኙነት ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይሁን እንጂ በውይይቱ ላይ ሊነሱ ስለሚችሉ ዝርዝር ነጥቦችን  የተባለ ነገር የለም። የሊዩ  ጉብኝትም  አሜሪካና ቻይና የገቡበትን የንግድ ጦርነት ለማርገብ በር ሊከፍት እንደሚችል ታምኖበታል።

ኢራን አሜሪካ የጦር መሳሪያ የጫኑ መርከቦችን ወደ ባህረ ሰላጤው ሀገራት መላኳን አጣጣለች 

አሜሪካ  በትናንትናው ዕለት ኢራን በአሜሪካ ላይ ለምታደርገው ትንኮሳ አፀፋዊ ምለሽ መስጠት የሚያስችል የጦር መሳሪያ እና ወታደሮችን የጫኑ መርከቦች ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መላኳን  የፕሬዚዳንት ትራምፕ የደህንነት አማካሪው ጆን ቦልተን አስታውቀዋል።

ይህን ተከትሎም የኢራን ብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ኬይቫን ኮህስራቪ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አሜሪካ ኢራንን በስነ ልቦና ጦርነት ለማንበርከክ የምታደርገው እንቅስቀሴ ከንቱ ድካምና ጊዜው ያለፈበት ነው በማለት  አጣጥለውታል።

ኬይቫን አክለውም የደህንነት አማካሪው ጆን ቦልተን ጉዳዩን አስመልክተው የሰጡት መግለጫ ኢራን የደረሰችበትን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበና የወቅቱን የስነ ልቦና ጦርነት የማይመጥን ነው ብለዋል።

ቦልተን የወታደራዊ ደህንነት ዕውቀትና ቴክኒክ ይጎድላቸዋል ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ጉዳዩን በተመለከተ የሰጡት መግለጫም  በሌሎች ዘንድ ትኩረትን ለማገኝት ያደረጉት ሙከራ ነው ብለዋል።

አሜሪካ አሁን በባህረ ሰላጤው አሰማራኋቸው ያለቻቸውን የጦር መርከቦችም ከ21 ቀናት በፊት ወደ ሜዲትራንያን ባህር ሲገቡ መመልከታቸውን ቃል አቀባዩን ጠቅሶ ተሰኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።

አሜሪካና ኢራን በኒውክሌር  ስምምነት ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት በሀገራቱ መካከል ውጥረት መንገሱ ይታወሳል። በዚህም አሜሪካ በኢራን ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን በመጣል ኢኮኖሚዋ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ላይ መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ።

ከዚህ ባለፈም በቅርቡ አሜሪካ የኢራን አብዮት ዘብ ጠባቂ ወታደሮችን በአሸባሪነት የፈረጀች ሲሆን፥በተመሳሳይ ኢራንም አሜሪካ በመካከለኛው መስራቅ ሀገራት ያሰማራቻቸውን የሰላም አስከባሪ ወታደሮች በአሸባሪነት ፈርጃለች። ይህም በሀገራቱ መካካል ነግሶ የቆየውን አለመግባባት ከፍ ወዳ አለ ደረጃ ማሳደጉ ነው የተነገረው ።

በማይናማር በእስር ላይ የቆዩት ሁለት የሬውተርስ ጋዜጠኞች ከእስር ተፈቱ።

ጋዜጠኞቹ ከ500 ቀናት በላይ የሃገሪቱን ህግ ተላልፈዋል በሚል በእስር ላይ መቆየታቸው ይታወሳል። ዋ ሎን እና ያው ሶይ ኦ የተሰኙት ጋዜጠኞች የሃገሪቱ መንግስት አዲስ አመትን አስመልክቶ በሰጠው ምህረት ከበርካታ እስረኞች ጋር መፈታታቸው ነው የተነገረው።

በማይናማር በሮሂንጊያ ሙስሊሞች ላይ የሚፈጸመውን አፈና እና ግድያ የተመለከቱ መረጃዎችን ይዘዋል በሚል በፈረንጆቹ 2017 በቁጥጥር ስር መዋላቸው የሚታወስ ነው።

በወቅቱ በሃገሪቱ ጦር ተፈጽሟል ያሉትን ግድያ የተመለከቱ መረጃዎችን በመሰብሰብ ጉዳዩ ለሚዲያ ሳይውል ነበር በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ሁለቱ ጋዜጠኞች ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በተከበረው አለም አቀፉ የፕረስ ነጻነት ቀን ላይ ተሸላሚ መሆናቸው ይታወሳል።

ፈረንሳይ አሜሪካና ቻይና የንግድ ፍጥጫቸውን ሊያስወግዱ እንደሚገባ አሳሰበች

ፈረንሳይ አሜሪካና ቻይና የንግድ ፍጥጫቸውን ሊያስወግዱ እንደሚገባ አሳሰበች። የፈረንሳይ የገንዘብ ሚኒስትር ብሩኖ ለ ሜር ሁለቱ ሃገራት አሁን እያደረጉት ባለው የንግድ ድርድር ውስጥ ፍጥጫን ማስወገድ እንደሚገባቸው ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ ዋሽንግተን እና ቤጂንግ የንግድ ፍጥጫውን በማስወገድ የዓለም ኢኮኖሚ እድገት እንዳይገታ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።

ሃገራቱ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ድርድር ማድረግ ይገባቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ፥ የዓለም ኢኮኖሚ እድገትን የሚጎትት እና የሚጎዳ ውሳኔን ሊያስወግዱ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። አሜሪካና ቻይና አንዳቸው በአንዳቸው ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ በመጣል የንግድ ፍጥጫ ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል።

ይህን ፍጥጫ ለማለዘብም ባለፉት ሳምንታት በሃገራቱ መካከል ድርድሮች ሲደረጉ ቢቆዩም አንዳች የውሳኔ ሃሳብ ላይ መድረስ አልቻሉም። ይህን ተከትሎም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቻይና ድርድሩን ጊዜ ለመግዛት ብቻ እየተጠቀመችበት ነው በሚል አካሄዱን ተችተዋል። በዚህ ሳምንትም አሜሪካ 200 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ባላቸው የቻይና ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ ትጥላለች ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም በቅርቡ ከፍ ያለ የገንዘብ ተመን ባላቸው የቻይና ምርቶች ላይ ቀረጥ ለመጣል ማቀዳቸውንም ሲናገሩ ተደምጠዋል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ቻይና ያለችው ነገር ባይኖርም የሃገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኡ ሂ ከነገ በስቲያ ወደ ዋሽንግተን እንሚያመሩ ታውቋል።

FANA B,

Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0
Read previous post:
በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ሰራተኞችና ነጋዴዎች ክስ ተመሰረተባቸው

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ሰራተኞችና ነጋዴዎች ላይ ክስ መመስረቱን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ...

Close