በምስራቅ ጎጃም ዞን የምትገኘው የእነጋትራ ሐና ገዳም አስተዳዳሪ መነኩሴ ከስድስት ክላሽንኮቭና ከአንድ ሽጉጥ ጋር በቁጥጥር ስር ዋሉ። መነኩሴው ከስድስት ክላሽንኮቭና ከአንድ ሽጉጥ ጋር በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ግጭት መፍጠራቸውን ተከትሎ መሆኑን የወረዳው አስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ይሄነው አበባው እንደገለጹት በቁጥጥር ስር የዋሉት አባ ገብረ ስላሴ ሳሙኤል የተባሉ ተጠርጣሪ በምስራቅ ጎጃም ዞን አዋበል ወረዳ በምትገኘው ጥንታዊቷ የእነጋትራ ሐና ገዳምን ከ28 ዓመታት በላይ አስተዳድረዋል።
ተጠርጣሪው መነኩሴ ከሃይማኖታዊ አገልግሎትና የገዳም መሬት ጋር በተያያዘ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ለረጂም ጊዜ የቆየ አለመግባባት ነበራቸው። ህበረተሰቡም በአስተዳዳሪው ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታ ለሚመለከተው አካል ሲያቀርብ መቆየቱን አቶ ይሄነው አስታውሰዋል። በትናትናው ዕለት ሚያዝያ 28 ቀን 2011 ዓ.ም ግን አባ ገብረ ስላሴ ጭቅጭቅ በሚነሳበት መሬት ላይ እርሻ ማረስ ሲጀምሩ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ በነቂስ ወጥቶ ግጭት መቀስቀሱን ነው የተናገሩት። በግጭቱም አስር ክፍሎች ያሉት ቤት መቃጠሉን፣ በገዳሙ አስተዳዳሪ ግብረ አበሮቻቸው በተተኮሰ ጥይት በአንድ ሰው ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን ተናግረዋል። #ENA