ሶስቱ የመንግስት አካላት ስራቸውን በቅንጅት እየሰሩ ባለመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደተጋረጡበት ተመላከተ፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት በህግ አውጭ፣በህግ ተርጓሚ እና በህግ አስፈጻሚ አካላት መካከል ባለው ግንኙነት፣ ቁጥጥር፣ አተገባበር እንዲሁም በዲሞክራሲ ግንባታ ዙሪያ በሚታዩ ተስፋዎች እና ተግዳሮቶች ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ መክሯል፡፡ ለምክር ቤት አባላቱ በፓርላሜንታዊ ስርዓት የመንግስት አደረጃጀት፣ አሰራር፣ የስልጣን አካላት አወቃቀር ግንኙነት እና ሰላማዊ ሀገራዊ ለውጥ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበዋል። ተወያዮችም የአማራ ክልል ምክር ቤት የበላይ ሆኖ ሁለቱንም አካላት የመቆጣጠር ሚናው ለዲሞክራሲ የሚጠቅም አይደለም፤ በወረቀት የተሰጠው ስልጣን እና በተግባር የሚታየው ሁኔታ ተቃርኖ ይታይበታል፤ የአንድ ፓርቲ የበላይነት መኖሩ ሶስቱም አካላት ተቀናጅተው ስራቸውን እንዳይሰሩ እና ተግባራቸውን እንዳይወጡ እያደረገው ነው የሚሉ አስተያቶችን አቅርበዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የምክር ቤት ተመራጮች ከመረጣቸው ሕዝብ ይልቅ ላስመረጣቸው አካል ትኩረት እየሰጡ ነው፤ ሀገራዊ ለውጡን መሸከም የሚችል የመንግስት መዋቅር እየተገነባ አይደለም፤ ህግ አውጪው፣ህግ ተርጓሚው እና ህግ አስፈጻሚው ሶስቱ አካላት የመፈጸም አቅም ውስንነት ይታይባቸዋል ብለዋል ተወያዮቹ፡፡

የክልሉ ህገ መንግስት ከክልሉ ውጭ ስለሚኖሩ አማራዎች የሚለው ነገር የለም፤ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ብሔሮች እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መብት ሰጥቷል፤ ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ በርካታ የአማራ ተወላጆች እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ሌሎች ክልሎች እድል አልሰጧቸውም፤ ለምን? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ያለው የሕዝብ ብዛት ሲታይ የበርታ እና የአማራ ብሔሮች ቁጥር ይበልጡን ይይዛል። ይሁን እንጅ የክልሉ ህገ መንግስት የክልሉ የባለቤትነት ጉዳይ ለበርታ፣ሽናሻ ወ.ዘ.ተ. ሲሰጥ አማራዎችን የባለቤትነት መብት ነፍጓል። የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግስትም ስለ ኦሮሞ ሕዝብ እንጅ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስለሚገኙ ሌሎች ብሔሮች አይገልጽ የሚሉት ናቸው በማሳያነት የቀረቡት፡፡

Related stories   ትህነግ ከትግራይ አስተዳደር ጋር መሳሪያ አስረክቦና ጦሩን በትኖ እንዲደራደር ታስቧል፤ መንግስ የተረፈውን ሃይል ሊያጸዳ ነው

የፌደራል ስርዓቱ ለፌደራል መንግስት እና ለክልል መንግስት የሰጠው ስልጣን ቢኖርም ከመጠን በላይ የስልጣን ባለቤቶች ክልሎች መሆናቸው ለችግሮች መፈጠር ምከንያት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ መንግስት የተሰጠውን ኃላፊነት በትክክል መወጣት ባለመቻሉ የክልሉን ሕዝብ የአገልጋይነት ስሜቱ እየተዳከመ ስለመሆኑ ያቀረቡት ተወያዮቹ ሕዝቡ የመንግስት አገልግሎት እያገኘ ያለው በሙስና እና በሌሎች ትስስሮች መሆኑን በማሳያነት ተናግረዋል፡፡

የስደትና ሞት መበራከት አሳሳቢ መሆኑን ያቀረቡት ተወያዮቹ የህግ የበላይነትን ለማስፈን የክልሉ የመንግስት አካላት ውስንነት እንደሚስተዋልባቸው ተናግረዋል፡፡ የሕዝብ አገልጋይነት ስሜት ያላቸውን እና የሌላቸውን አካላት በትክክል የመለየት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡ የተረጋጋ ሰላም እንዳይኖር የሚሰሩ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ ላይ ውስንነቶች መኖራቸውም ተጠቅሷል፡፡ የፓርላመንታዊ ስርዓቱ በሀገሪቱ እየተፈጠረ ላለው አለመረጋጋት ምክንያት በመሆኑ ሊጤን እንደሚገባውም ጠይቀዋል፡፡

Related stories   ህወሓት፤ የኢትዮጵያና ኤርትራ የጋራ ጠላት!

ከተወያዮቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡ በሌላ ክልል ውስጥ የሚገኙ አማራዎች የአስተዳደር እና የዲሞክራሲ መብታቸው እንዲከበር የተነሳው ጥያቄ ተገቢ በመሆኑ ምክር ቤቱ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚያቀርብ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ‹‹ሁሉም ዜጋ ባለበት እንደ ሰው የመኖር፣ የመንቀሳቀስና ዲሞክራሲያዊ አንድነት እንዲኖር መስራትን ሁላችንም በኢትዮጵያ ካሰፈንን ችግሩን መቅረፍ እንችላለን›› ብለዋል የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅ ሰሙ ማሞ፡፡

ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ለሀገራችን ያስፈልጋል የሚለው ጉዳይ ደግሞ ሰፊ ትኩረት የሚጠይቅ በመሆኑ በቀጣይ ሕዝቡ ተወያይቶ መልስ ቢሰጥበት የተሻለ እንደሚሆን ነው ሀሳብ የተሰጠበት፡፡

ለህግ አውጭውም ሆነ ለህግ ተርጓሚው እንቅፋት እየፈጠረ ያለው በአብዛኛው አስፈጻሚው የመንግስት አካል ነው፤ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራው ነው፤ የአማራ ክልል የሰላምና ደኅንነት ስጋት መንስኤው በአብዛኛው የክልሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ነን የሚል ማብራሪያም ተሰጥቷል፡፡ በየደረጃው ያለን አስፈጻሚ አካላት ችግራችን ተነጋግረን ባለመፍታታችን ሕዝቡ ማግኘት ያለበትን ጥቅም እያገኘ አይደለም፤ በክልሉ እየታየ ካለው ወቅታዊ ለውጥ ጋር አብሮ ለመጓዝ ችግር ፈች ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለብን ብለዋል፡፡

Related stories   የኢዜማ 23 የፓርላማ እጩዎች እነማን ናቸው?

ህገ ወጥነት እየተስፋፋ፣ ስርዓት አልበኝነት እየነገሰ፣ ችግሮች ሲከሰቱ አስፈጻሚ አካላት አለመፍታታቸውም ክፍተት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡ ሶስቱ የመንግስት አካላት ስራቸውን በቅንጅት እየሰሩ ባለመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደተጋረጡበት ሀሳብ ተሰጥቷል፡፡ የክልሉ መንግስት ይህን ጉዳይ ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የፌደራል መንግስቱ በመላ ሀገሪቱ ከዜጎች ሞት እና መፈናቀል ጋር ተያይዞ የሚታዩ አሉታዊ ገጽታዎችን መፍታት እንዳለበትም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ የክልሉ መንግስት የማህበረሰቡን ሰላማዊ ሁኔታ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሲሰራ ሕዝቡም የበኩሉን እገዛ ማድረግ እንዳለበትም ተጠይቋል፡፡

የምክር ቤት አባላት እና የፓርቲ አባላት በአወቃቀር ይለያዩ እንጅ በአብዛኛው በአንድ አይነት ርዕዮት ዓለም የተጠመዱ በመሆናቸው በፓርላመንታዊ ስርዓቱ ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ በመሆኑ እልባት እንደሚያስፈልገው ተገልጧል፡፡

ህገ መንግስቱን ማሻሻል እንደሚያስፈልግና ለማሻሻል ደግሞ ኢትዮጵያውያን እንዲነጋገሩበት ማድረግ ተገቢ መሆኑም ተነስቷል፡፡ አብመድ)

ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *