ለውጡን ተከትሎ በርካታ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያ ፖለቲከኞች ወደ አገር ቤት ከገቡ በሁዋላ ዋናው ችግራቸው የዜግነት ጉዳይ እንደሆነና ኢትዮጵያ የሁለት አገር ዜግነት ልትፈቅድ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። መንግስትም ጉዳዩን ወደ ፊት እንደሚያየው በተደጋጋሚ አስታውቋል።
ይህንኑ ተከትሎ በአገሪቱ ህግ መሰረት የፖለቲካ አመራር ለመሆን በስደት ያገኙትን ዜግነት ለመመለስና በትውልድ አገራቸው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ለመጠራት የወሰኑ ስለመኖራቸው እስካሁን አልተሰማም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዛሬ የተለያዩ ሚዲያዎች ይፋ እንዳደረጉት ስድስት ፓርቲዎች ግንባር ገጥመው በመሰረቱት አዲስ ፓርቲ ውስጥ የቀድሞው የግንቦት ሰባት አመራር የሆኑት አይካተቱም። ፋና እንዲህ ዘግቦታል።
ትናንት ራሱን ያከሰመው የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እና አቶ ኤፍሬም ማዴቦ አዲስ በሚመሰረተው ፓርቲ የአመራርነት ስፍራ አይዙም።
 
የቀድሞው አርበኞች ግንቦት ሰባት የፖለቲካ ጉዳዮች ዘርፍ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት እሳቸው እና የድርጅቱ ዋና ፅሃፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ለአዲሱ ፓርቲ በአመራርነት የመመረጥ መብት አይኖራቸውም።
 
ይህም የሆነው ሁለቱ አመራሮች የውጪ ሀገር ዜግነት ስላላቸው እና የሀገሪቱ ህግ ለውጪ ሀገር ዜጎች የመመረጥ እና መምረጥ መብት ስለማይሰጥ ነው።
 
በዚህም ምክንያት አቶ ኤፍሬም እና አቶ አንድርጋቸው አርበኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ሰባት ፓርቲዎች ራሳቸውን አክስመው በሚመሰረቱት ፓርቲ የአመራርነት ሚና አይኖራቸውም ተብሏል።
 
አቶ ኤፍሬም እንደገለፁት ሁለቱ የቀድሞ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች በአዲሱ ፓርቲ የአማካሪነት እና የእገዛ ሚና ይኖራቸዋል።
 
አርበኞች ግንቦት ሰባት ትናንት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ድርጅቱ ከስሞ አርብ የሚመሰረተውን አዲስ ፓርቲ አካል እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።
 
በዳዊት መስፍን – (ኤፍ ቢ ሲ) 

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *