ፍርድ ቤቱ በአቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ክስ የተመሰረተባቸውና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ አራት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጠ።

የፌዴራል ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ 26 በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ተከሳሾችን ጉዳይ ዛሬ ከሰዓት ተመልክቷል።

በዚህ መሰረትም በአቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ክስ ከተመሰረተባቸው ተከሳሾች ውስጥ ከ20 እስከ 26 ተራ ቁጥር ላሉት ተከሳሾች ክሳቸው በንባብ ቀርቧል።

ተከሳሾቹ የተነበበላቸውን ወንጀል እንዳልፈፀሙ ክድው ተከራክረዋል።

የተከሳሽ ተከላካይ ጠበቆች የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲጠበቅላቸውና ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

አቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሾች የፈፀሙት ወንጀል የዋስትና መብት የማያሰጥ በመሆኑና ተከሳሾች የዋስትና መብታቸው ቢከበርም መረጃ ያሸሹብኛል ብሏል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ የተከላካይ ጠበቆች የክስ መቃወሚያ ይዘው ያልቀረቡ በመሆኑና የዋስትና መብት ተገቢነትን መመርመር አስፈላጊ ሆኖ በማግኘቱ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ለፌዴራል ፖሊስ አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በሌሉበት ክሳቸው እየታየ ያሉ አራት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በትናንትናው ዕለት ክስ ከተመሰረተባቸው 26 ተከሳሾች ውስጥ ከ1ኛ እስከ 19 ላሉት ተከሳሶች ክሳቸውን በንባብ ማቅረቡ ይታወሳል።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *