የብቀላ ጥቃት ከጥቂት ህፃናትና በጣት ከሚቆጠሩ አዛውንቶች በስተቀር ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃና ቁጥሩን ለመግለፅ በሚያስቸግር መልኩ በርካታ እናቶች፣ ህፃናትና ጎልማሶች ጅምላ ግድያ የተፈፀመባቸው መሆኑን በግምገማችን ለይተናል፡፡ይህ ድርጊት በእጅጉ የሚያሳዝንና በህዝቦች አብሮነትና በሀገር አንድነት ላይ የተቃጣ፣ በንፁሃን ወገኖች እልቂት ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚፈልጉ ቡድኖች፣ ፅንፈኛ ብሔርተኞችና ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አክቲቪስት ነን ባዮች ሴራ እንደሆነ በጥልቀት ተረድተናል፡፡

ከቤጉህዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ክልላዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በክልሉ ርዕሰ-መዲና አሶሳ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ በወቅታዊ ክልላዊ ሁኔታዎች ላይ በጥልቀት በመወያየት ባለ 9 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡

የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በተለይም ከውህደት ማግሥት ጀምሮ በየዘርፉ የተከናወኑ ዓበይት ተግባራትንና የተመዘገቡ ለውጦችን በወፍ በረር የቃኘ ሲሆን በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደ ክልል ያጋጠመውን የሠላም መደፍረስና ግጭት በጥልቀት ገምግሟል፡፡

የኢፌዴሪን መንግሥት በይፋ ከመሠረቱ ሉዐላዊ ክልሎች አንዱ ሆኖ በሕገ-መንግሥቱ የተደራጀው የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት የህዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተጠቅሞ ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት መብት ከማረጋገጥ አንስቶ የኗሪውን ህዝብ የልማት፣ የሠላም፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተጠቃሚነት በአንፃራዊነት ከፍ ያደረጉ ውጤቶች መመዝገባቸውን በግምገማው አስታውሷል፡፡

በክልሉ የሚኖሩ የሁሉንም ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ከመስጠት ጎን ለጎን በክልሉ ውስጥ ለበርካታ ዘመናት አብረው የሚኖሩ ብሔር ብሄረሰቦችን ጥያቄ ለመመለስ ባደረጋቸው ጥረቶች በተለይም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አበረታች ለውጦች መታየታቸውን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ መላው የክልሉ ኗሪ ህዝብ የመንግሥት ሥራዎችን በባለቤትነት ለመፈፀምና ለመደገፍ እያሳየ ያለው ተነሳሽነትም ቢሆን በእጅጉ የሚበረታታ መሆኑን አስምሮበታል፡፡

በዚህ ረገድ በተለይም በፐብሊክ ሰርቪሱ ውስጥ ከ80% በላይ የሚሆነውን ድርሻ የሚዙት የክልሉ መስራች ከሆኑት አምስቱ ብሄረሰቦች ጋር አብረው የሚኖሩ በርካታ ብሔረሰብ ተወላጆች የሆኑ ባለሙያዎችና በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች እያከናወኑ ያሉት ተግባር በክልሉ መንግሥት በኩል ዕውቅና የሚሰጠውና የሚመሰገን ስለመሆኑ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡

በክልሉ ህዝቦች መካከል ለዘመናት ጸንቶ የቆውን ወንድማማቻዊ አንድነት ለማጎልበትና አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በጋራ ውይይት ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረት ያደነቀው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በአንፃሩ ከዚህ በተለየ ሁኔታ በህዝቦች መካከል እርስ በእርስ መጠራጠር እንዲነግሥና ግጭት እንዲፈጠር የሚጥሩ ኃይሎችን የጥፋት እንቅስቃሴ በአንድ ድምፅ አውግዟል፡፡

በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የማኦ-ኮሞ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በሦስቱም የክልሉ ዞኖች የበርካታ ዜጎችን ህይወት የቀጠፉ፣ አካል ያጎደሉ፣ ንብረት ያወደሙና በርካቶችን ከመኖሪያ ቀያቸው ያፈናቀሉ ግጭቶችን ለመቅረፍ ርብርብ እየተደረገ ባለበት ወቅት ሚያዝያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ አይሲካ ቀበሌ በትራንስፖርት ታሪፍ ውዝግብ መነሻነት ተስፋፍቶ የብሔር መልክ በመያዝ ለበርካታ ንፁሃን ዜጎች መቀጠፍ ምክንያት የሆነውን ግጭት በዝርዝር የገመገመው የቤጉህዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በግምገማው ማጠቃለያ የሚከተለውን ባለ 9 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡

1. ከዚህ በፊት በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልልና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት መከሰቱና በሁለቱ አጎራባች ክልሎች ጥምረትና በፌዴራል መንግሥት እገዛ ግጭቱን የማብረድ ሥራ እየተሰራ በመሆኑ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ነባር ቀበሌያቸው መመለስ መጀመራቸውን በዝርዝር ገምግመናል፡፡ 
ይህ ሥራ በተለያዩ ምክንያቶች እንዳይደናቀፍ ከማድረግ ጎን ለጎን የተፈናቀሉ ወገኖች ሙሉ በሙሉ ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ ከኢፌዴሪ እና ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር የጀመርነውን ጥረት ይበልጥ አጠናክረን የምናስቀጥል ይሆናል፡፡

2. ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ አይሲካ በምትባል ቀበሌ በትራንስፖርት ታሪፍ ውዝግብ ሁለት ግለሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ጉዳዩን ለማብረድ በሚል በአካባቢው በነበረ የፌዴራል ፖሊስ አባል በተተኮሰ ጥይት የአንድ ሰው ህይወት በመጥፋቱ ምክንያት ጉዳዩ ብሔረሰባዊ መልክ ይዞ ለበርካታ ንፁሃን ሰዎች ህልፈት ምክንያት እስከመሆን መድረሱን በጥልቀት ተገንዝበናል፡፡ በጠፋው የሰው ህይወትና በደረሰው ውድመት እጅግ ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶናል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለተጎጅ ቤተሰቦች በሙሉ ዳግም መፅናነትን እየተመኘን በዚህ ድርጊት ውስጥ እጃቸው አለበት በሚል እስካሁን የተለዩ 55 ግለሰቦችን ጨምሮ ሌሎች አካላትንም በማጣራት ለህግ ለማቅረብ የጀመርነውን ጥረት ይበልጥ አጠናክረን የምናስቀጥል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

3. በዳንጉርና በማንዱራ ወረዳዎች የተከሰተውን ችግር አሳሳቢነት የተገነዘበው የክልላችን መንግሥት በወቅቱ ከፍተኛ አመራሮችን ወደ ቦታው በመላክ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አቻዎቻቸው፣ ከመከላከያ ሠራዊትና ከሁለቱም ክልል የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ግጭቱን ለማብረድና ወደሌሎች አካባቢዎችም እንዳይስፋፋ በተደረገ ጥረት አንጻራዊ መረጋጋት ለመፍጠር ተችሎ እንደነበር ተገንዝበናል፡፡

በአንፃሩ ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ በሦስት አካባቢዎች በሚኖሩ የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ላይ በተሰነዘረ ብሔር-ተኮር የብቀላ ጥቃት ከጥቂት ህፃናትና በጣት ከሚቆጠሩ አዛውንቶች በስተቀር ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃና ቁጥሩን ለመግለፅ በሚያስቸግር መልኩ በርካታ እናቶች፣ ህፃናትና ጎልማሶች ጅምላ ግድያ የተፈፀመባቸው መሆኑን በግምገማችን ለይተናል፡፡

ይህ ድርጊት በእጅጉ የሚያሳዝንና በህዝቦች አብሮነትና በሀገር አንድነት ላይ የተቃጣ፣ በንፁሃን ወገኖች እልቂት ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚፈልጉ ቡድኖች፣ ፅንፈኛ ብሔርተኞችና ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አክቲቪስት ነን ባዮች ሴራ እንደሆነ በጥልቀት ተረድተናል፡፡

በመሆኑም በዚህ የተቀነባበረ ወንጀል ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸው ያለበትን ቡድኖች፣ ግለሰቦችና በማህበራዊ ሚዲያ ሳይቀር ቅስቀሳ ያደረጉ አክቲቪስቶች ጭምር ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አጥብቀን እንደምንሠራ እናረጋግጣለን፡፡

4. አካባቢውን ለማረጋጋት፣ በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስና ለማቋቋም ከሁለቱ ክልል መንግሥታት፣ ከመከላከያ ሠራዊትና ከፌዴራል መንግሥት ጋር የተጀመረው የጋራ ጥረት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እንወጣለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ህብረተሰቡ በአንዳንድ አካባቢዎች በሚስተዋሉ ትንኮሳዎች ሳይደናገጥ ወደ ቀየው እንዲመለስ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

5. የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለሀገራዊ ጥንካሬያችንም ሆነ ለጋራ ዕድገታችንና ተጠቃሚነታችን መረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ በሚገባ እንገነዘባለን፡፡ 
በመሆኑም በህዝቦች መካከል ለዘመናት ፀንቶ የቆየው ወንድማማቻዊ ግንኙነትና አንድነት በየትኛውም ዓይነት ምክንያት እንዳይሻክር ይልቁንም በላቀ መተሳሰብና መከባበር ይበልጥ እንዲጎለብት የበኩላችንን ኃላፊነት ለመወጣት ያለንን ዝግጁነት እናረጋግጣለን፡፡

6. በየአስተዳደር ወሰኑ በተደራጀና ባልተደራጀ መንገድ በጦር መሣሪያ የታገዘ ወንጀል የሚፈፅሙ አካላት እየተበራከቱ መምጣታቸውን በግምገማችን በዝርዝር አስተውለናል፡፡ 
ይህ ዓይነቱ ተግባር በአፋጣኝ እንዲቆም እስካልተደረገና በወንጀል ፈፃሚዎችና በተባባሪ ኃይሎቻቸው ላይ ሕጋዊ እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ ወደ ባሰ ችግር ውስጥ ልንገባ የምንችልበት አጋጣሚ ሰፊ ሊሆን እንደሚችልም ተገንዝበናል፡፡ በመሆኑም በአስተዳደር ወሰኖች አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ወንጀል ፈፃሚዎችንና ተባባሪዎቻቸውን ለህግ ለማቅረብ ተግተን የምንሠራ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

7. አሁን የምንገኝበት የፌዴራል ሥርዓትም ሆነ የጀመርነው የለውጥ ጉዞ በበርካታ የህዝብ ልጆች ክቡር መስዋዕትነት የተገኘ እንደሆነ እጅግ አጥብቀን እናምናለን፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱ ላይም ሆነ በለውጥ ጉዟችን ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም አፍራሽና አደናቃፊ ሙከራዎች በላቀ ቁርጠኝነት ታግለን መቀልበስ የሚገባን መሆኑን ከልብ እንገነዘባለን፡፡
በዚህ ረገድ በተለይም “መተከል የእኛ ነው” በሚል መፈክር በጥቂት አክቲቪስቶችና ደጋፊዎቻቸው የሚራመደው ሃሳብ የፌዴራል ሥርዓቱን የሚቃረንና የለውጥ ጉዟችንን ለማደናቀፍ የተጠነሰሰ ሴራ እንጅ በየትኛውም ዓይነት መስፈርት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

8. ክልላችን በበርካታ ተፈጥሯዊ ገፀ-በረከቶች የተባረከች፣ ከልብ ተግተን ከሠራን በቀላሉ ለማደግና ለመለወጥ የምንችልባት የሁላችንም የጋራ መኖሪያ መሆኗን እጅግ አጥብቀን እንገነዘባለን፡፡ በመሆኑም መላ የክልላችን ኗሪዎች ወንድማማች አንድነችንን ይበልጥ አፅንተን፣ በመካከላችን ጥርጣሬ ለመፍጠርና ግጭት ለመቀስቀስ የሚጥሩ ኃሎችን አፍራሽ እንቅስቃሴ በጋራ ትግል መክተን አሁን የተፈጠረውን አንፃራዊ ሠላምና መረጋጋት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ለጋራ አገራችን እድገትና ብልፅግና በአንድነት እንደምንረባረብ ቃል እንገባለን!!

9. በየአካባቢዎቹ በተከሰቱ ግጭቶችና በደረሱ ጥፋቶች አጅግ ያዘነው መላው የክልላችን ኗሪ ህዝብ ላሳየው እጅግ ብስለት፣ ጨዋነትና ሃገራዊ ኃላፊነት የሞላበት ትዕግሥት ያለንን ታላቅ አድናቆትና አክብሮት እየገለፅን ለህዝቦች አንድነትና ለጋራ ሠላም ያሳየውን ይህን ድንቅ ተግባር በሌሎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ዘርፎችም ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል በትውልድ የሚዘከር መልካም ታሪክ እንድንሠራ በዚህ አጋጣሚ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የቤጉህዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ  

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት

ግንቦት 01/2011 ዓ.ም 
አሶሳ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አፍሪካ ህብረት ቁርጠኛነቱን አሳይቷል፤ አውሮፓ ህብረት ምርጫ አልታዘብም አለ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *