“Our true nationality is mankind.”H.G.

ቂምና በቀልን የሚሽር መፍትሔ

አገራችን ካሏት አኩሪ እሴቶች መካከል አንዱ ሽምግልና ነው፡፡ ከሰሞኑ በመተከል ዞን ተከስቶ የነበረውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታትና የህዝቡን ሰላም ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ እየተሠራ ይገኛል፡፡ የሠላሙ ሂደት የሕዝቦችን ተቻችሎ የመኖር እሴት በሚያጠናክር፣ ቂምና በቀልን በዘላቂነት በሚሽር ደረጃ መሆን እንደሚገባውም የሀገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡

በዞኑ የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት እንዳብራሩት የዘመናት አብሮነት ያላቸው ሕዝቦች ተጋብተው፣ ተዋልደው፣ ተዋደውና በአንድነት በኖሩበት መተከል ዞን በቅርቡ የተከሰቱት ውጥረቶች፣ ግጭቶችና የንጹሐን ሕይወት መጥፋት ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍና ለበቀል ሲባል የተደረጉ መሆናቸው ያሳዝናል፡፡ በሁለቱ ክልሎች ወንድማማች ህዝቦች እና በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ ብሔሮችን በማጋጨት፣ በማለያየትና በማጋደል የተለየ ትርፍ ለማግኘት መጣር ከንቱነት ነው፡ ፡

የአማራና የጉሙዝ ብሔረሰቦችም ሆኑ ሌሎች የክልሉ ነዋሪዎች አብሮነት በቀላሉ የሚፈርሱ አለመሆናቸውን ነው የሃገር ሽማግሌዎች የሚያመላክቱት፡፡ ይህንን የቆየ ተቻችሎ የመኖር የህዝቦች እሴት ለማጠልሸት የሚሯሯጡ የፖለቲካ ሰዎች መኖራቸውን በተመሳሳይ አቋማቸው የሚጠ ቁሙት የሃገር ሽማግሌዎች “በሕዝቦች መካከል ችግሮች የተፈጠሩ በማስመሰል በንጹሐን ደም የሚቀልዱና ግጭቶችን የሚያባብሱ አካላት በሁለቱም ክልሎች ሊኖር አይገባም፤ መታረም አለባቸው፤ በሕግ ሊጠየቁም ይገባልም” ይላሉ፡፡

በዚህ ረገድ ‹‹የተፈጠሩ ችግሮች ወደ ሌሎች አካባቢዎች በሰሚ ሰሚ እየተወሩ በሕዝቦች መካከል መለያየትን እንዳያስከትሉ እየሠራን ነው” የሚሉት በመተከል ዞን የቡለን ወረዳ ነዋሪ የሀገር ሽማግሌ አቶ እጀታ አዊ ናቸው፡፡ የሺናሻ ማህበረሰብ አካል የሆኑት አቶ እጀታ እንደሚሉት የመተከል ዞን አማራ፣ ሺናሻ፣ ጉሙዝ፣ አገው እና ሌሎችም ሕዝቦች ተዋደው በአንድነት የሚኖሩበት ነው፡፡ በጋብቻ ከመተሳሰራቸውም በላይ በደስታና በሐዘን የማይነጣጠል ቁርኝት የፈጠሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡

በሰው ሠራሽ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችንም በጋራ መክተው መፍትሔ እያስቀመጡ እዚህ የደረሱ በመሆናቸው መነጣጠል የማይታሰብ ነገር ነው ይላሉ፡፡ “በዳንጉር የተፈጠረው ችግርም በሕዝቦች መካከል ይምሰል እንጂ መልኩ ሌላ ነው” የሚሉት አቶ እጀታ በቡለን አካባቢ እስከአሁን የተፈጠረ የጸጥታ ችግር ባይኖርም ወጣቶች አንዱ በሌላው ላይ ቂምና ጥላቻን እንዳያሳድሩ በመምከር ላይ መሆናቸውን እኚህ አባት ያመላክታሉ፡፡ ወጣቱም ምክራቸውን እንደሚሰማ ርግጠኛ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው አባባል ማሕበረሰቡም ያለውን ለራበው የሚያበላ፣ ለተጠማው የሚያጠጣ እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ነው፡፡

ለዚህም በቅርቡ ከሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ አማራና ሌሎች ብሔሮችን ተቀብሎ አብልቶ፣ አጠጥቶ፣ አልብሶና አሳፍሮ በሰላም መሸኘቱን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ነዋሪና የጉሙዝ ማህበረሰብ አባል የሆኑት አቶ በግዚ ሰኚ በበኩላቸው እንደተናገሩት በቡለን አካባቢ ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር የለም፡፡ “ማህበረሰቡን በሰፊው እያስተማርንና እየመከርን ነው፡፡ በጃዊ በጉሙዝ ብሔረሰብ ላይ የተፈጸመው የበቀል ጭፍጨፋ በእውነቱ አሳዛኝ ነው፡፡

ስለሆነም አጥፊዎቹ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ቂምና በቀል ግን በዚህ የይቅርታ ዘመን አስፈላጊ አይደለም›› ነው የሚሉት አቶ በግዚ፡፡ በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ማምቡክ ከተማ ነዋሪና የአማራ ብሄር አካል የሆኑት የአገር ሽማግሌ አቶ አግረው ወርቁ በበኩላቸው ‹‹በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነት ጥፋት መፈጸም ያስነውራል፡፡ ጥፋት በጥፋት አይጸዳም፤ አይሽርምም፡፡ አሁን የአገር ሽማግሌዎች ማህበረሰቡ ተረጋግቶ ወደ ዕለት ሥራው መመለስ እንዲችል ጥረት እያደረግን ነው” ይላሉ፡፡

ቂምና በቀል እንዳይኖር በማድረግ በመቀራረብና በመነጋገር ወደ እርቅ መሄድ እንዲቻል የአገር ሽማግሌዎች ተመርጠው እየሠሩ መሆናቸውንም ያመላክታሉ፡፡ ፈጣሪ እንዲታከልበት የሁሉም ጥረትና ጸሎት አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ አቶ አግረው እንደሚሉት አሁን በርካታ ሰው ከቀየው ርቋል፡፡ እየኖረ ያለው በሥጋት ነው፡፡ የነበረውን አንድነት በመመለስ አብሮ መሥራትና አብሮ መብላት እንዲቻል፤ ሕፃናት፣ ሴቶች እና አጠቃላይ ማህበረሰቡ እንደገና አብሮነቱን ማስቀጠል አስፈላጊ ነው፡፡ ሰላም መፈጠር አለበት፡፡ ወጣቱ ለሥራ እንጂ አስፈላጊ ላልሆነ ነገር ጊዜውንም፣ ገንዘቡንም ማዋል የለበትም፡፡

ሕይወቱንስ ለምን በከንቱ ያጣል፡፡ መንግሥት ከሕብረተሰቡ ጋር ሆኖ አጥፊዎችን በሕግ መጠየቅ አለበት፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መሀመድ ሀምደኒል የዞኑን የጸጥታ ሁኔታ አስመለክቶ ማክሰኞ ረፋድ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት በዞኑ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማረጋጋት በጋራ እየተሠራ ነው፡፡ ህብረተሰቡን አሳታፊ በማረድረግ እየተሠራ ባለው የማረጋጋት ሥራ በአካባቢዎቹ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ከሦስት ቀናት በፊት ጀምሮ ሠላማዊ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

እንደ ኮሚሽነር መሀመድ ገለጻ እየተደረጉ ባሉ ውይይቶች የግጭቱ መነሻ ግለሰቦች መሆናቸው እየታወቀ ሠላምን የማይፈልጉ አካላት በፈጠሩት የማባባስ ሥራ የደረሰውን ጉዳት ህብረተሰቡ እያወገዘ ይገኛል፡፡ ሠላምን ለማረጋገጥና የግጭቱን ተሳታፊዎች ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ህብረተሰቡ እንዲያግዝ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አዲስ ዘመን ግንቦ

በሙሐመድ ሁሴን

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣
0Shares
0