ባሕር ዳር፡ ግንቦት 03/2011ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ በዓመቱ መጨረሻ የፋይናንስ ደኅንነት ተቋማት ኅብረት የሆነው የዓለም አቀፉ ‹ኢግሞንት ግሩፕ› አባል ስትሆን በውጭ አገራት በሕገ-ወጥ መንገድ የተቀመጡ ገንዘቦቿን ማስመለስ እንደምትጀምር የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል ገለጸ።

የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ እንዳለ አሰፋ እንደገለጹት አስፈላጊ ዝግጅቶች በመጠናቀቃቸው ኢትዮጵያ በዓመቱ መጨረሻ 159 አገራት የፋይናንስ ደኅንነት ተቋማትን በአባልነት የያዘው ኢግሞንት ግሩፕ አባል ትሆናለች። በመሆኑም ከኢትዮጵያ ሙስናን ጨምሮ በሕገ-ወጥ መንገድ ከአገር የወጡ ገንዘቦችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት አባል አገራቱ ሙሉ መረጃ በመስጠት እና በማስመለስ ረገድ ትብብር ያደርጋሉ።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ደኅንነት ተቋም (ኢግሞንት ግሩፕ) አባል አገራት መካከል ሙስናን ጨምሮ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን የመከላከል ግዴታ ተጥሏል።

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

በመሆኑም በውጭ አገራት ባንኮች እና በተለያዩ ቦታዎች የተከማቹ ገንዘቦች ለማስመለስ የሚያስችል አቅም ስለሚፈጠር ገንዘቡ ወደአገር እንዲመለስ ይደረጋል። በቀጣይ ዓመት ስዊዝ ባንክም ሆነ የትኛውም አገር ላይ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ከኢትዮጵያ የወጣ ገንዘብ ካለ መረጃ ተሰብስቦበት በመጀመሪያ መጠኑ እንዲታወቅ ይደረጋል። ከዚያም የማስመለስ ሥራው ከየመንግሥታቱ እና ተቋማቱ ጋር ይካሄዳል።

የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ አጠራጣሪ የሆኑ ግብይቶች እና የገንዘብ ዝውውሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደደረሱት አቶ እንዳለ ገልጸዋል። በሙስና፣ በግብር ማጭበርበር፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎችም ወንጀሎችን የያዘው ጥቆማ ዝርዝር መረጃ ተሰብስቦበታል። 52 ጉዳዮችም አስፈላጊው መረጃ ተጠናቅሮባቸው ጉዳያቸው ወደ ፖሊስ መላካቸውን ተናግረዋል።

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

እንደ አቶ እንዳለ ማብራሪያ ማዕከሉ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኙ ገንዘቦችን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን ለመከላከል በኢትዮጵያ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማትን የገንዘብ ዝውውሮች መረጃ ይተነትናል።

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጥርጣሬ የታየባቸው የስድስት ቢሊዮን ብር መጠን ያላቸውን ጉዳዮች አጣርቷል። እያንዳንዱ ባንክ፣ ኢንሹራንስ እና ቁጠባ ተቋማት በየቀኑ የሚደረገውን ከ300 ሺህ ብር በላይ የሆነ ገንዘብ ዝውውር እና ጥርጣሬ የታዬባቸውን መረጃዎች እያቀረቡ በመሆኑ የገንዘብ ዝውውሮች ከሕገ-ወጥነት ጋር እንዳይያያዙ ጥንቃቄ እየተደረገ ይገኛል።

Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

እንደ ማዕከሉ መረጃ በኢትዮጵያ የሚገኙ ባንኮች፣ ኢንሹራንስ እና ቁጠባ ተቋማት፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የተፈቀደላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች፤ በቤት ግንባታ የተሠማሩ ድርጅቶች፣ የገቢዎች እና የጉምሩክ ተቋማት ለፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል የገንዘብ ልውውጣቸውን የሚመለከት ሪፖርት የመላክ ግዴታ በሕግ ተጥሎባቸዋል። እስካሁን ግን እያንዳንዱን የሒሳብ ባለሙያ እና ኦዲተሮች መረጃ ለማዕከሉ የሚያቀርቡበት ልምድ አልተፈጠረም።

መቀመጫውን ቤልጂየም ብራሰልስ ያደረገው ዓለም አቀፉ ኢግሞንት ግሩፕ አሜሪካን ጨምሮ 159 አገራት የፋይናንስ ደኅንነት ተቋማትን በአባልነት የያዘ ተቋም ነው።

ምንጭ፡- ኢ.ፕ.ድ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *