ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ከተማውን ከአንድ ሚሊዮን የፕላስቲክ ጠርሙሶች ነጻ ያደረገው ጀግና!

የ36 ዓመት ወጣት ነው፤ ነዋሪነቱ በአማራ ክልል መርሳ ከተማ ነው። በጫማ ማሳመር ሙያ ተሰማርቶ ረዥም ዓመታትን አሳልፏል፤ ዘይኑ ሀሰን።

‹‹ኑሮዬን ለማሸነፍ በርካታ የሥራ ዓይነቶችን ያለመታከት እሠራለሁ›› የሚለው ዘይኑ ከዓመታት በፊት በአንዱ ቀን አካባቢውን እያፀዳ ለራሱም ገቢ የሚያገኝበት የሥራ ሐሳብ ብልጭ አለለት።

‹‹በየመንገዱ የተጣሉ ፕላስቲኮችን ለምን እየለቀምኩ አላጠራቅምም? በዚያውም ከተማዬን ከቆሻሻ የፀዳች አደርጋታለሁ ብየ አሰብኩ›› ይላል ሥራውን ስለጀመረበት አጋጣሚ ሲናገር።

‹‹ሲበዛ ጠንካራ ነኝ፤ ተስፋ አልቆርጥም፤ ብዙ ጊዜ ምን መሥራት አለብኝ? ምን ብሠራ ይሳካልኛል? ብየ አስባለሁ›› ሲል ይናገራል ዘይኑ።

በየቀኑ ጠዋት ከ12:00 እስከ ረፋድ 3:00 እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከ8:00 ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ በከተማዋ አውራ ጎዳዎች እየተዘዋወረ ያለመታከት የኘላስቲክ ለቀማውን ማከናወን ጀመረ።

ከጊዜ ወደ ጊዜ የፕላስቲክ ጠርሙሶቹ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ፕላስቲኮችን ለማከማቸት የሚሆን ቦታ ጥበት ገጠመው። ሥራውን ለማከናወን የሚሆን ቦታ እንዲመቻችለት የሚኖርበትን ቀበሌ ከዚያም የመርሳ ከተማ መዘጋጃ ቤትን ቢጠይቅም በወቅቱ መፍትሔ አላገኘም ነበር፡፡

‹‹የቦታ ጥያቄዬ ባለመመለሱ ተስፋ አልቆረጥኩም፤ እንዲውም ይበልጥ እንድጠነክር አድርጎኛል›› በማለት በወቅቱ የተሰማውን በመግለጽ ጥረቱ መቀጠሉን አስረድቷል። ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ በመጨረሻም ወይዘሮ ፋጡማ የሱፍ አህመድ የተባሉ ሴት ፕላስቲኮቹን በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ እንዲያጠራቅም ፈቀዱለት።

ይህንን ሥራ ከጀመረበት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ 400 ሺህ ፕላስቲኮችን መሰብሰብ የቻለው ዘይኑ ከሁለት ወራት በፊት ያቀደውን ቁጥር ማሳካት መቻሉን በኩራት ይናገራል። ‹‹አሁን ዕቅዴ ተሳክቷል፤ ከተማዬን ከአንድ ሚሊዮን የፕላስቲክ ጠርሙሶች ነጻ ማድረግ ችያለሁ›› ብሏል። ዘይኑ የፕላስቲክ ጠርሙሶቹ አንድ ሚሊዮን ሲደርሱ በአንድ ሚሊዮን ብር የመሸጥ ዕቅድ እንደነበረው በአንድ ወቅት ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።

ይህ ብርቱ ወጣት አሁን የፕላስቲክ ጠርሙሶቹን የሚገዛው እያፈላለገ ነው፤ የሚረዳው ድርጅት ካገኘ ደግሞ ቆሻሻውን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

ይህን ተግባር በመፈፀሙ የከተማው ንፅህና እንዲጠበቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከተም በኩራት ይናገራል።
አሁንም ሌሎች የፕላስቲክ ዓይነቶችንም እየለቀመ ማጠራቀሙን ቀጥሏል። በኢትዮጵያ ውስጥ 6 ቢሊዮን የውኃ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ከየፋብሪካዎች ታሽገው ጥቅም ላይ እንደዋሉ ሪፖርተር ጋዜጣ ባንድ ዘገባው ላይ ጠቅሶ ነበር።
ይሁን እንጅ ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋልም ሆነ ይዘትን ቀይሮ በመገልገል ደረጃ የተሳካ ሙከራ አለመደረጉን መረጃዎች ያስረዳሉ።

ጎረቤታችንን ኬንያን ጨምሮ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የፕላስቲክ ጠርሙሶችን መልሶ በመጠቀሙ በኩል አበረታች ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ። አንዳንድ ሀገራት የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ፕላስቲክ ነክ ቁሶች ጨርሶ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የሚያደርጉ ሕጎችን እስከመደንገግ የሚደርስ ቁርጠኝነት እያሳዩ መሆኑም ይታወቃል።

ወጣቱ ይህን በሚሰራበት ወቅት ስላጋጠመው ችግር ሲገልጽ ‹‹ከማጠራቀሚያ ቦታ ችግር በተጨማሪ ፕላስቲኮቹን ስለቅም ብዙ መሰናክሎች ቢገጥሙኝም ሁሉንም አልፌያቸዋለሁ። ብዙዎች ‹አበደ› ብለውም ሸሽተውኛል›› ብሏል።
አሁን ግን በርካታ የከተማው ወጣቶች ጥንካሬውንና አርዓያነቱን በስፋት እየመሠከሩለት ነው፡፡
ምንጭ፡- አረንጓዴ ሐሳቦች

(አብመድ)

Related stories   የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?