ከለውጡ ወዲህ በአማራ ክልል ስላለው ወቅታዊ እና ነባራዊ ሁኔታ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ከአብመድ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ለለውጡ ከፍተኛ መስዋትነት የከፈለና በተለየ መልኩ ለውጡን በደስታ አምኖ የተቀበለ ሕዝብ እንደሆነ ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ ‹‹ለውጡ ቀደም ብሎ ከነበረው ብልሹ አሠራር እፎይ የሚባልበትና ሕዝቡም ሠላሙን የሚያገኝበት አጋጣሚ ነው ተብሎ ቢታሰብም የለውጥ ጉዞው በደጋፊና ነቃፊ ኃይሎች ወደተለያዬ አቅጣጫ በመወጠሩ ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የእርስ በርስ ግጭት እንዲስፋፋ፣ ሞት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት እንዲፈጠር አድርጓል›› ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ባልተለመደ መልኩ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ መድረሱ ታሪክ የማይዘነጋው የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ በማዕከላዊ እና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በሰሜን ሸዋ ዞን እና ሌሎች አጎራባች ክልሎች በአማራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረው የሠላም መደፍረስ አንገት የሚያስደፋ አሳዛኝ ሰብዓዊ ቀውስ እንደነበር ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹እኛም ልክ እንደ ሕዝቡ ከለውጡ የምንጠብቀው ሠላማዊ እንቅስቃሴ በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ ይሰፍናል ብለን እንጂ እንዲህ እልቂት ይደርስብናል ብለን አላሰብንም›› ነው ያሉት፡፡ ይሁን እንጂ አብረው የኖሩ ወንድማማች ሕዝቦችን ለማጋጨት ለረጅም ዘመናት ሲሠራበት የነበረ ጫፍ የረገጠ የብሔርተኝነት ቅስቀሳ እና የፖለቲካ ሴራ እየፈነዳ ባለባቸው አካባቢዎች ለፍቶና አምርቶ የሚተዳደረውን ሠላማዊ ሕዝብ ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉን አብራርተዋል፡፡ ‹‹ስውር የፖለቲካ ፍላጎትና የግል ጥቅማቸውን የሚያካብቱ ኃይሎች ባልተጠበቀ ጊዜ የፈጠሩት ችግር የአማራውንም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባሕል፣ ሥነ-ልቦና እና ወግ የጎዳ ነው፡፡ ይህ ቀውስ ጫፍ የረገጡ የአክራሪ ብሔርተኞች ሴራ ውጤት ነው›› ብለዋል፡፡ የሁለት ግለሰቦች ግጭት ዓድማሱ እየሰፋ የብሔር ግጭት እንደተፈጠረ ለማስመሰል ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት መሰል ድርጊቶች እንዳይደገሙ ሰከን አድርጎ ነገሮችን ከዘረኝነት በጸዳ መልኩ ማየት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

መንግሥት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስቀድሞ ተንብዮ ባለመከላከሉ በተፈጠረ የሠላም መደፍረስ ብዙ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሷል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት ይህ የሆነበት ምክንያት የፀጥታ ኃይሉ መረጃ የማግኘት ክፍተት ስለነበረበት እና በኅብረተሰቡ ጥቆማ የተገኙ መረጃዎችንም በሚገባ ተንትኖ ከጥፋት ሊታደግ የሚችል ስምሪት ባለመደረጉ ነው፡፡ በተለይም የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች በተደጋጋሚ የፀጥታ ስጋት እንዳለባቸው ቀደም ብለው ተናገረው የነበረ ቢሆንም የክልሉ መንግሥት በነዚህ መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ መሥመራት ባለመቻሉ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡ 
‹‹ግጭት በተከሰተበት ቦታ በጉዳዩ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች በሕግ ጥላ ስር ውለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የግጭቱን መሪ ተዋናዮች አድኖ ለሕግ ከማቅረብ አንጻር ድክመት መኖሩ በግምገማ ተረጋግጦ ስምሪት የተሰጠው የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ልዩ ኃይል ጥፋተኞችን ለሕግ እንዲያቀርቡም ድጋሜ ስምሪት ተሰጥቷል፡፡ ወንጀለኞችን በፍጥነት ወደ ሕግ ለማቅረብ የክልሉ መንግሥት አቅም አጥቶ ሳይሆን አንድም ሰው ሳይሞት ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ፍላጎት ስላለው ነው›› ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

ለጊዜው ማረጋገጫ ባይኖረውም የክልሉ መንግሥት የለየው እና በልዩ ሁኔታ የማጣራት ሥራ እየተሠራበት ያለ ኃይል መኖሩንም አመላክተዋል፡፡ ‹‹በተወሰነ መልኩ ይህንን ተግባር የሚያጋልጡ መረጃዎች ስላሉ በሕግ አግባብ ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ መሆን ይኖርበታል›› ብለዋል፡፡ በወንጀል የተጠረጠሩ አካላት ምሕረት እንዲደረግላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ዶክተር አምባቸው ጥያቄያቸው ተቀባይነት የሚኖረው በቅድሚያ እጃቸውን ለሕግ ሰጥተው በተገቢው መንገድ መጠየቅ ሲችሉ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ምንም እንኳን በሠላም መደፍረስ የደረው ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳይ አንገት የሚያስደፋ ቢሆንም ድጋሚ ሕዝቡ ለከፋ ቀውስ እንዳይጋለጥ ካለፈው ስህተት ትምህርት መውሰድና በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ በሠላም ወጥቶ እንዲመለስ እና በየትኛውም አካባቢ በነጻነት ተንቀሳቅሶ የሚኖርበትን አስተማማኝ ሠላም ለማስፈን ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የሠላም ማስከበር ስምሪት ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ችግርን አስቀድሞ መከላከል እንዲቻል ኅብረተሰቡ የመረጃ ምንጭ እንዲሆን፣ እራሱን እንዲያስከብርና አካባቢውን እንዲጠብቅ ብቁ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ የፀጥታ አካላትም በተልዕኳቸው የመቀዛቀዝ ባሕሪ እያሳዩ በመሆኑ የተለመደውን መደበኛ የሠላም ማስከበር በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የመንግሥት የመጀመሪያው ተግባሩ ሕግና ሥርዓትን አስከብሮ ለዜጎች ሠላም እና ደኅንነት ዋስትና መቆም በመሆኑ የሠላም ጉዳይ ከሌሎች ተግባራት ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሠራበት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ክልሉ ሙሉ ሠላሙ የተረጋገጠ እንዲሆን፣ ችግር የተፈጠረባቸው አካባቢዎችም ሕዝባዊ ውይይትና እርቀ ሠላም እየወረደ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ወደ ፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ተቻችለው እና ሠላም አግኝተው የሚኖሩባቸው መንገዶች እንዲኖሩ እየተሠራ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ውስጥም ሆነ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን በደል እና መፈናቀል በዘላቂነት ለማስቆም ኅብረተሰቡ እራሱ ለሠላም መቆም እንዳለበት፤ መንግሥትም ከየክልሉ አመራሮች ጋር እየተወያዩ መፍትሔ እንደሚያፈላልግ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹አንድም ሰው በቆንጨራ፣ በቀስትም ሆነ በጥይት መሞት የለበትም›› ያሉት ዶክተር አምባቸው ነገሮችን በንግግር የመፍታት ባሕል ማዳበር እና ግጭትን ማስቆም እንደሚገባ ነው ያሰመሩበት፡፡

ከሌሎች ክልሎች ጋርም የሚኖረን መልካም ግንኙነት ለዜጎች ሠላማዊ ሕይወት አስተዋጽዖ ሊኖረው ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ያለው ነባራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ እና ውስብስብ ነው›› ያሉት ዶክተር አምባቸው ‹‹ምንም እንኳን ባልተጠበቀ መልኩ በተፈጠረ ግጭት ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስም ከክልሉ ውጭ ያሉ የአማራ ብሔር ተወላጆችን የሚከታተል አካል አለ፤ በክልሉም ውስጥ በተፈጠረው ግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን የሚያወያይ እንዲሁም በድርጊቱ የተሳተፉትን ከሕግ አግባብ የሚያጣራ ግብረ ኃይል አለ፤ እየሠራም ነው›› ብለዋል፡፡

ጠንካራ መሠረት ያላት ሀገር ለመገንባትም መንግሥትና ሕዝብ አብሮ መሥራት እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች መንስኤያቸው ምን እንደሆነ በመለየት ዘላቂ መፍትሔ መስጠትም እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስትም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በሌሎችም ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሰጧቸውን ማብራሪያዎች በተከታታይ እናቀርባለን፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ – ፎቶ ፡-በሀይሉ ማሞ  ባሕር ዳር፡ ግንቦት 03/2011ዓ.ም (አብመድ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *