“Our true nationality is mankind.”H.G.

‹‹ይነዛ በነበረው ወሬ በመዘናጋታችን ያቀድነውን ውጤት ማምጣት አልቻልንም ››

‹‹ባለፈው ዓመት የሀሰት መልሶችን የሚሸጡ አካላት ተስተውለዋል፡፡›› የክልሉ ትምህር ቢሮ

በባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2011ዓ.ም (አብመድ) በዝግጅት ማነስ እና በተለያዩ አሉባልታዎች የሚፈጠረውን የሥነ-ልቦና ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን የትምህርት ባለሙያዎች ነግረውናል።

በፈተና ወቅት ተማሪዎች በነፃነት መፈተን እንዳለባቸው የትምህርት ባለሙያዎች መክረዋል። ተማሪ ሙሉጌታ አሰፋ በጣና ሐይቅ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኝ ነው፡፡ አሁን ላይ ለቀጣይ ዓመት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት የሚያስችለውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለመውሰድ የተለያዩ የፈተና ጥያቄዎችን እና አጋዥ መጻሕፍትን እያነበበ እንደሆነ ነው የነገረን፡፡

ተማሪ ሙሉጌታ በፈተና ወቅት የተማሪዎችን ሥነ-ልቦና የሚረብሹ የተለያዩ አሉባልታዎች መናፈስ የተለመደ እንደሆነም ነግሮናል፡፡ የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በወሰደበት ወቅት ፈተናው እንደተሰረቀና ለአንዳንድ ተማሪዎች እንደደረሰ በመወራቱ ተማሪዎች የተሳሳተ የፈተና መልስ ይዘው ገብተው ውጤታቸው እንደቀረባቸውም ነግሮናል፡፡ አሉባልታ እንደሆነ የተረዱ እና በተዘጋጁት ልክ የሠሩ ተማሪዎች ደግሞ የተሻለ ውጤት ማምጣታቸውን ነው ተማሪ ሙሉጌታ የገለጸው፡፡

ተማሪ ሙሉጌታ እንደሌሎች ተማሪዎች ተለቀቀ የተባለውን የፈተና መልስ ይዞ ቢገባም ከፈተናው ጋር የሚገናኝ ሆኖ ባለማግኘቱ በተዘጋጀው ልክ ትክክለኛውን ሀገር አቀፍ ፈተና በመፈተን ሦስት ነጥብ ማምጣት እንደቻለ አስታውሷል፡፡ ይሁን እንጅ ይነዛ በነበረው ወሬ በመዘናጋቱ ያቀደውን ውጤት ማምጣት እንዳልቻለ ነው የተናገረው፡፡ በዚህ ዓመትም የፈተናው ቀን መራዘሙን አስመልክቶ የተማሪውን ሥነ-ልቦና የሚጎዱ የተለያዩ አሉባልታዎች እየተናፈሱ በመሆኑ ተማሪዎች ተረጋግተው መዘጋጀት እና በፈተናው ወቅትም በተዘጋጁበት ልክ መሥራት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

የጣና ሐይቅ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ትምህርት ቤት የተማሪዎች የምክር እና የድጋፍ አገልግሎት ባለሙያ አቶ ማስረሻ ታደሰ እንደገለፁት ተማሪዎች በዝግጅት ችግር እና በውጭ በሚሠራጨው አሉባልታ መደናገጥ ሲስተዋልባቸው ይታያል፡፡ ተማሪዎች በተዘጋጁበት ልክ ከሠሩ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ ውስጣቸውን አሳምነው በነፃነት ፈተናውን መውሰድ እንዳለባቸውም ነው ባለሙያው የገለፁት፡፡ በፈተና ወቅት መደናገጥ፣ መጨነቅ፣ የፈተና ማቋረጥ እና በግዴለሽነት አጥቁሮ መውጣት ከዝግጅት ማነስ የሚፈጠሩ እንደሆኑ ነው ያመለከቱት። ችግሩንም ለመቅረፍ በሥነ-ልቦና ባለሙያዎች እና በመምህራን በኩል የምክር አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉን ባለሙያው ነግረውናል፡፡

የጣና ሐይቅ ትምህርት ቤት የአካዳሚክ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ተስፋ ገነት እንደተናገሩት በትምህርት ቤቱ በ2011 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ መምህራን የሚያስተምሯቸውን ትምህርቶች በወቅቱ እንዲያጠናቅቁ ተደርጓል፡፡ መልመጃዎችንና ከዚህ ቀደም የነበሩ የፈተና ጥያቄዎችን በማሠራት እና የተለያዩ ፈተናዎችን በተደጋጋሚ በመፈተን ተማሪዎች አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ተደርጓል። ከመማር ማስተማር ባለፈ ተማሪዎችን ለፈተና የሚያዘጋጁ ‹ሞዴሎችን› በማዘጋጀት እንዲፈተኑ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡ ወቅቱ ተማሪዎች የልፋት ውጤታቸውን የሚያዩበት ጊዜ በመሆኑ በሚናፈሱ አሉባልታዎች ሳይደናገሩ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ወይዘሮ ተሰፋ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ፈተናው እንደወጣ ቢናፈስም ከተማሪዎች ጋር ተቀራርቦ በመሠራቱ ትምህርት ቤቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ካመጡት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ መሆን መቻሉንም እንደ ጥሩ ተሞክሮ አንስተዋል፡፡ ‹‹በርካታ ተማሪዎች ተረጋግተው በመሥራና ውጤት በማምጣት ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መግባት ችለዋል›› ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የፈተና እና የትምህርት ምዘና ጥናት ባለሙያ አቶ ማማሩ ላቀ ደግሞ በክልሉ የክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተና የሚፈተኑ ተማሪዎች በዝግጅት ማነስ የሥነ-ልቦና ችግር እንዳይደርስባቸው ከበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ጥራት ላይ ትኩረት እንዲሰጥ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
‹‹የዝግጅት ማነስ ካለ በሚናፈስ አሉባልታ ሁሉ የመሽነፍ ነገር ስለሚኖር በቅድመ ዝግጅት ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል፡፡›› ብለዋል ባለሙያው፡፡

በባለፈው ዓመት የሀሰት መልሶችን የሚሸጡ አካላት እንደነበሩም አቶ ማማሩ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ተማሪዎች በዝግጅት ማነስ የሚደርስባቸውን የሥነ-ልቦና ችግር ለመቅረፍ ትርፍ ጊዜን ጨምሮ እንዲማሩ ተደርጓል፡፡ በፈተና ወቅትም ችግር እንዳይፈጠር ከፌደራል አስከ ትምህርት ቤቶች ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፤ ውይይትም ተደርጓል፡፡ ችግሮችም እንደተከሰቱ ሲነገር እውነት ነው ብሎ ከመቀበል ይልቅ ከትክክለኛው ምንጭ ማረጋገጥ ይገባል›› ሲሉም አቶ ማማሩ አሳስበዋል፡፡ 
ተማሪዎች ትምህርት ቢጨርሱም እስከ መጨረሻው የፈተና ጊዜ ከትምህርት ቤት አካባቢ መራቅ እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ በፈተና ወቅትም ያለምንም መደናገጥ እና ‹ኩረጃ› በተዘጋጁበት ልክ ነፃ ሁነው እንዲፈተኑ ባለሙያው አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ –

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የዘረኝነት ጥግ “እናት ነኝ የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ”
0Shares
0