ሩስያ በኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫው ዘርፍ ለመሰማራት ትልቅ ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ የሩስያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ኢቪገን ቸርኪሂን ተናገሩ።

አምባሳደር ኢቪገን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ከአሁን በፊት ኢትዮጵያ እና ሩስያ የተፈራረሙት ለሰላማዊ ጥቅም የሚውልን የኒውክሌር ኃይል ስምምነት በፍጥነት ወደ ተግባር ለማስገባት ሞስኮ እየተንቀሳቀሰች መሆኗንም ተናግረዋል።

ከሶስት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ኢቪገን ቸርኪሂን የኢትዮጵያና ሩስያ ግንኙነትን ከ3 መቶ ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ እና ሩስያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንዳላቸው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ምጣኔ ሀብት ትስስር ለማሸጋገር የተለያዩ መንገዶችን እየተጠቀሙ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ የምጣኔ ሀብት መንገድ መካከል አንዱ የኒውክሌር የሃይል ማመንጫ እና በሌሎች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ሞስኮ ትልቅ ፍላጎት ማሳየቷ ነው።

የኒውክሌር ሃይል ማመንጫው በቅርቡ ወደ ትግበራ እንዲገባ እየሰራን ነው ያሉት አምባሳደር ኢቭገን፥ የሩስያ ኩባንያዎች በሌሎች የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫዎች ላይ የመሳተፍ ፍላጎታቸውም ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ እስካሁን ባለው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ውስጥም ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ሩስያ ለኢትዮጵያውያን የምትሰጠው ነፃ የትምህርት እድል መሆኑ ይታወቃል።

አምባሳደር ኢቪገን ታዲያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታም በቀጣይ ይህ ዘርፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

አምባሳደር ኢቭገን ቸርኪሂን አዲስ አበባ እና ሞስኮ ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ በቀጠናዊ ጉዳዮችም በቅርበት በትብብር እየሰሩ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና ሩስያን የግንኙነት መስመር ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገው የሁለቱ ሀገራት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባም በየጊዜው የሚካሄድ መሆኑ የሚታወስ ነው። አምባሳደሩ ሩስያ በአፍሪካ የዲፕሎማሲው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥም ተናግረዋል።

እንዲሁም በታሪክ ወደኋላ በመሄድም የአዲስ አበባ እና ሞስኮ የግንኙነት መስመር  ደምቆ የወጣው ጣሊያን በቅኝ ግዛት መንፈስ ተነሳስታ ኢትዮጵያን ለመውረር ባደረገችው ዘመቻ ሩስያ ለኢትዮጵያ ተጋድሎ ድጋፍ ካደረገች ጀምሮ መሆኑን ያስታውሳሉ።

ከዚያም የኢትዮጵያውያን የአንድነት እና የትብብር ደማቅ ታሪክ እና ምዕራፍ ከሆነው የአድዋ ድል ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያ በሩስያ ዜጎች ፊት ታላቅ ተቀባይነት እና ክብር ማግኘቷን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እና የሩስያ ግንኙነት የችግር ጊዜ ብቻ አይደለም ያሉት አምባሳደሩ፥ ሁለቱ ሀገራት በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መንገድም አብረው ብዙ ጊዜ መጓዛቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዲፕሎማሲ ጎዳና የተሰሚነቱን ካባ የደረበች ሲሏት፥ ሩስያ ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ካላቸው አምስት ሀገራት አንዷ መሆኗን ያነሳሉ።

ሁለቱም ሀገራት በሰው ሀገር ፖለቲካ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባትን አካሄድ በፅኑ ይቃወማሉ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውም ለዚህ አካሄድ ዋጋ አይሰጡትም ብለዋል።

አምባሳደር ኢቭገን ቸርኪህን  ለአብነት ያህል ባለፉት ሁለት ዓመታት አዲስ አበባ እና ሞስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፖለቲካው መስክ የተጓዙበትን የትብብር መድረክ አንስተዋል።

ኢትዮዽያ ቀደምት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከፈጠረችባቸው ሀገራት መካከል ሩስያ አንዷ መሆኗም ይታወቃል።

በሁለቱ ሀገራት መካከልም መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከተደረገ ከ1 መቶ 20 ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህንን ረጅም ዓመታት ያስቆጠረውን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገርም ለሰላማዊ ጥቅም የሚውልን የኒውክሌር ኃይል ስምምነት በፍጥነት ወደ ተግባር ለማስገባት ሞስኮ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን አምባሳደር ኢቭገን ቸርኪህን ተናግረዋል።

በስላባት ማናዬ – (ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *