ዜጎች ከመነዳት ቀስ እያሉ መውጣት መጀምራቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ ነው። ቀደም ሲል በደመ ነብስ ላይክና ሼር ሲያደርጉ የነበሩ ወገኖች በሚያስገርም ሁኔታ ተቀዛቅዘዋል። ይህንን የሚከታተሉ የሼርና የላይክ ገበያ መቀዛቀዙንና በምትኩ ቀልብ የሚስቡ ተናጋሪዎች ጆሮ እያገኙ መሆኑን እየተናገሩ ነው።

” አንዱ ብቻውን ይጮሃል። ኦን ላይን አክቲቪስት መሆኑ ነው። በመንገድ ላይም ቢሆን ሆኜ ለአማራ እህዝብ እታገላለሁ። እለፈልፋለሁ። አክቲቪስትነቴን እስክሞት አልተውም … እያለ ይናገራል። የሚገርመው የሚያወራው ብቻውን ነው” ሲሉ ይህንን ዋቢ አድርገው ለጎልጉል አስተያየት የሰጡት አቶ ግዛው ዮሐንስ በብዛት እንደተከታተሉት ራሳቸውን አክቲቪስት ብለው የሰየሙ ወገኖች አሁን ወቀሳና ትችትም እየበዛባቸው ነው።

አስራት ሶራ በበኩሉ አሁን በተለያዩ ደረጃ የተጀመሩ ውይይቶችና ንግግሮች አዳዲስ ሰዎችንም እያስተዋወቀ ነው ይላል። ይህ የሚያሳየው ዝም ብለው የነበሩ መነሳታቸውን ነው። ነገሩ በዚህ ከቀጠለ ዝም ብለው ሲዘባርቁና ያለ እውቀት ሲያበላሽ የነበሩት ስለሚደነግጡ ቀስ ብለው ሌላ አማራጭይፈልጋሉ።

አስራት አክለው ስም መጥቀስ እንደማይፈልጉ በማስታወቅ እንዳሉት ከሆነ በማህበራዊ ገጽ ከሚለጥፉት ግርጌ ፈተናና ውግዘት እየበረከተባቸው ነው። ታማኝ በየነ ለምን ፋሲክ ከነማን ጎበንና ሽልማት ተሰጠው በሚል ቅሬታ ላቀረቡ ክፍሎች የተሰጠው መልስ የሚጎመዝዝና ለውጥ መኖሩን የሚያሳይ ነው።

“ታማኝ በመቀበላቸውና በመሸለማቸው ፋሲል ከተማ እግር ኳስ ቡድን  ይቅርታ ይጠይቅን” በሚል ጽፈው የለጠፉ ወገኖች ክፉኛ መሰደባቸውንና በዚህም መደናገጣቸውን የገለጸው አስራት ” የአክቲቪስትነት ትርጉሙ በአገራችን ሁኔታ ግራ ቢያጋባም በጅምላ ሲከተሉ የነበሩ ወገኖች ለውጥ ማሳየታቸውን አይቻለሁ” ብሏል።

ስመኝ በበኩልዋ በጅምላ የምንጎድ ጉዳይ ላይ ለውጥ ማየቷን፣ ነገር ግን ብዙ ሊሰራበት እንደሚገባ፣ ተናገራለች። እሷ እንደምትለው ሚዲያዎች ውይይቱንና ንግግሩን በስራው ለተሰማሩ ትተው በመረጃና በማስረጃ የተደገፈ የምርመራ ስራ ላይ እንዲያተኩሩ ትመክራለች። ይህ ሲልሆን መጋለጥ የሚገባቸው ይጋለጣሉ። ህዝብ እውነታውን ይረዳል።

አቶ ልደቱ አያሌው በቅርቡ በሰጡት አስተያየት ሚዲያው የምርመራ ስራ ላይ ማተኮር አለበት። የተነገረውን ሁሉ እየገለበተ የሚሰራ ከሆነ ዜጎች ትክክለኛ መረጃ ሊያገኙ አይችሉም ማለታቸውን ያነሳቸው ስመኝ ” የጠራ መረጃ ከሌለ አተላውን መጋት ግድ ይሆናል። አክቲቪስት ነን እያሉ የሚጮሁት አብዛኞቹ በመረጃ ተደግፎ ዶክመንታሪ ቢሰራባቸው ጥሩ ነው። ምን ያህል ህዝቡን እንዳሳቱት በገሃድ በማሳየት የሚከስሙበትና የተሻሉት ነጥረው እንዲወጡ መልካም አጋታሚ ይፈጥራል ” ባይ ናት።

Related stories   በኦሮሚያ - ለውጡን የሚጻረሩ ተልዕኮ ተቀብለው አሰቃቂ ደርጊት ሲፈጽሙ የነበሩ ተጨማሪ ችግር ሆነዋል

“የዛሬ መቶና ሁለት መቶ አመት ለነበረ ጉዳይ ዛሬ አዲስ ድንኳን ተክለው ያባሉናል” እንዳሉት ፓስተር የማህበራዊ ገጽ ቤተሰቦች ግንዛቤ መለወጡና መረጃን ወደ መመርመር መሸጋገሩ አገሪቱ የያዘችውን ለውጥ ተስፋ ሙሉ እንደሚያደርገው አብዛኞች ያምናሉ።

አክቲቪዝም ያለ እውቀት መዘላበድና የተገኘውን ሙያ ሁሉ በማግበስበስ መስራት እንዳልሆነ በርካታ ዜጎች አሁን አሁን በይፋ እየተቹ ነው። አብዛኞቹ ከራሳቸው ጉያ ስር ካለ ፍላጎትና የሌሎችን ቡድኖች ሃሳብ ተገዝተው የሚያስፈጽሙ መሆናቸውንም ህዝብ እያወቀ ነው። ከሁሉም በላይ በዘረኛ አስተሳሰብ አብረው የኖሩ ዜጎችን ለጥቅም ሲሉ በማጋጨት የተጠመዱ መሆናቸው ግልጽ እየሆነ መምጣቱ በደመ ነብስ ሲቸራቸው የነበረው ሼርና ላይክ ገበያ እንዲቀዛቀዝ ምክንያት ሆኗል። ውግዘትም እያስተናገዱ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *