“Our true nationality is mankind.”H.G.

የባህር ዳር ነዋሪዎች ” አደራጁን አካቢያችንን እንጥብቅ፤ ኮሽ የሚል ነገር አይሰማም” አሉ፤

‹‹ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባሕር ዳር ድንገት ባደረግነው አሰሳ በሕገ ወጥ ሥራ የተሠማሩ 89 ተሸከርካሪዎችን እና ሕገ-ወጦችን በቁጥጥር ስር አውለናል፡፡ አማራን ለማፍረስ ያልተሠራ ስለሌለ ችግሮቹ ብዙ ናቸው››  ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው 

በአማራ ክልል ከኃላፊነት የተነሱና አስቀድመው ‹ኔትወርክ› የዘረጉ አካላት ለክልሉ ፀጥታ ችግር መሆናቸውን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች መናገራቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን አስታወቀ።

በባሕር ዳር ድንገት በተደረገ የአንድ ቀን አሰሳ በሕገ ወጥ ሥራ የተሠማሩ 89 ተሸከርካሪዎች እና ሕገ-ወጦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ታውቋል፡፡

ይህ የተገለጸው የባሕር ዳር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ከርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን እና ሌሎችም የክልልና የከተማ አስተዳደሩ መሪዎች ጋር ሲወያዩ ነው፡፡ በውይይቱ ተሳታፊዎቹ በየአካባቢው እና በየቀጠናው አደረጃጀት ተፈጥሮ ባለመሠራቱ መፈናቀሎች መከሰታቸውን፤ መሪዎችን የመቀየር ጉዳዩ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ እንዲደረግበት እና አዴፓ ውስጡን መፈትሽ እንዳለበት አንስተዋል፡፡ በአግባቡ ቢሠራ ኖሮ መፈናቀል ላይፈጠር ይችል እንደነበርም አመልክተዋል፡፡

ፀጥታውን በተመለከተ ሕዝቡ ይቆጣጠራል፤ በትክክል ሕዝቡን በየቀበሌው አደራጅቶ መሥራት ከተቻለ መፈናቀል ቀርቶ ኮሽታም እንኳን አይኖርም ነበር ብለዋል፡፡ ሕዝቡን በማደራጀት፣ መሪዎቹን ተጠያቂ በማድረግና አሉባልታዎችን በመቅረፍ የፀጥታ ችሮችን መፍታት እንደሚቻልም አመልክተዋል፡፡

‹‹የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ማስተዋላችን ላይ ችግር እየፈጠሩ ነው›› ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች ችግሮቻችንን በመሣሪያ አፈሙዝ ሳይሆን በድርድር እና በመግባባት ልንፈታ ይገባል፤ በጅምላ መወንጀል አለ፤ ተለይቶ የችግሩ ፈጣሪዎች መጠየቅ አለባቸው፤ መንግሥትም ችግር ከመፈጠሩ ቀድሞ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡

ጎጠኞችና ከስልጣን የተገለሉ ሰዎች የራሳቸውን ‹ኔትወርክ› ዘርግተው ለክልሉ ሠላምና መረጋጋት እንቅፋት እየሆኑ እንዳስቸገሩ በመጠቆምም መፍትሔ እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡

አዴፓ በክልሉ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከአማራ ጥቅም ባለፈ በክልሉ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን አቅፈው እንዲታገሉ ለማድረግ አቀራርቦ ቢሠራ ጥሩ መሆኑን ያመለከቱት ተሳታፊዎቹ ‹‹አሁን ያለው ሕገ-መንግሥት በድርድር እና በመነጋገር እንዲቀየር ብትሰሩ ጥሩ ነው፤ የአማራ ክልል ሕዝብን ጥቅም እናስጠብቃለን ከሚሉ ኃይሎች ጋር ተቀራርባችሁ እንድትሠሩ ኅብረተሰቡ ይፈልጋል›› ብለዋል፡፡ ኢኮኖሚው እንዳልተነቃቃና በግብርናው ዘርፍ ከዚህ በፊት ተፈጥሮ የነበረው መነቃቃት መደብዘዙንም አንስተዋል፡፡

መደገፍና መንቀፍ በምክንያት መሆን እንዳለበት ያመለከቱት ተሳታፊዎቹ ‹‹ክልል የሚለው ጉዳይ ቢጠፋ ደስተኞች ነን፤ ለውጡ ሲመጣ ይህ ጉዳይ ይጠፋል የሚል እምነት ነበረን፤ ሲሆን ግን አላየንም፤ እንዲያውም ባሰበት፤ ጎጠኝነትና በዘር ማሰብ ቢቀር መልካም ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹በአማራ ክልል ውስጥ አንዳንድ ግለሰቦችን የፌደራል አካል በተልኮ ለማስያዝ ሲሞክር ለምን ፈቀዳችሁ?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ 
‹‹በመንግሥት ሥራ ላይ ያሉ ባለሙያዎች በሙስና ተተብትበው ኅብረተሰቡን እያንገላቱ ነው፡፡ ለውጡ፣ ለውጥ እንዲሆን አዳዲስ አሠራሮች መኖር ይገባቸዋል፤ ተዘዋዋሪ ፈንድ ላይ እየተሠራ ያለው ጥሩ ቢሆንም አሁንም መመሪያዎቹ መሻሻል አለባቸው›› የሚሉ ሐሳቦችንም አንስተዋል፡፡

መሪዎች ከአንድ አካባቢ ሲጠሉ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር እንዲቀር፣ ከክልሉ ውጭ ያሉ አማራዎች ሠላምና ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ፤ ክልሉን ሲበድሉ የነበሩ አካላት ከአዴፓ እንዲወጡ፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ችግሮችን የሚያጋልጡና ለአማራ ህዝብ የቆሙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ማዋከብም እንዲቆም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡

የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ተጠናክሮና መሠረተ ልማት ተሟልቶለት ወደ ሥራ እንዲገባ፣ የከተማ አስተዳደሩ የሚያመነጨውን ገቢ እንዲጠቀም፣ የከተማዋ መሪ ዕቅድ (ማስተር ፕላን) በፍጥነት ተከልሶ ወደ ሥራ እንዲገባና ሕገ-ወጥ ግንባታ እንዲቆምም ተወያዮቹ አሳስበዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙሉቀን አየሁ በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩን መሪዎች እንደገና ማደራጀት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ያሉት መሪዎች አዲስ ናቸው፤ ነገር ግን አንዳንዶች አሁንም የሚፈጥሩት ችግር ቅሬታ እየፈጠረ ነው›› ብለዋል፡፡ ከንቲባ ሙሉቀን እንደተናገሩት ‹‹አኩራፊ ኃይሎች›› ሥራዎችን እያሠሯቸው አይደለም፤ ለመወሰን ያስቸገሯቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ 
‹‹ከክልሉ እገዛ ቢደረግልን ችግሮችን እንፈታለን፤ ከዚህ በፊት የነበሩ አመራሮች ያልሰሯቸው ሥራዎች አሉ፡፡ እነዚህንም እንደየደረጃዎቹ እየለዬን እንፈታለን፤ የማኅበራትን ጥያቄዎችም እየፈታን ነው›› ብለዋል ከንቲባው በማብራሪያቸው፡፡ በዚህ ወቅት በአጭር ጊዜ 9 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ መሠራቱን ያመለከቱት ከንቲባው ይህም ከቀደሙት ጊዜያት የተሻለ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ 
ባሕር ዳር እንድታድግ ከተፈለገ እጅን ማጥራት፣ ወጣቶችን አለመከፋፈል እንደሚገባ የጠቆሙት ከንቲባ ሙሉቀን ለዚህም ሕዝቡ ማገዝ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ‹‹ለከተማው ሕዝብ ሲባል ከሕግ የሚወጡት ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንወስዳለን፤ የባሕር ዳር የፀጥታ ጉዳይን ለማስተካከል ከክልሉ ጋር እየሠራን ነው›› ብለዋል፡፡

ሕገ-ወጥ የቤቶች ግንባታን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡም ‹‹በሕገ ወጥ እየተሠሩ በደቦ አጽድቅልን እየተባለ እየተመጣ ነው፤ አልሆን ሲል ስም ወደ ማጥፋት ዘመቻ እየተገባ ነው፤ የራስን መሥራት ሲያቅት እየተዞረ ማሳመጽ ተጀምሯል፡፡ ባሕር ዳር የክልሉ ከተማ ብትሆንም በጀት ስለሌላት ዕድገቷ ተገትቷል፡፡ የባሕር ዳር የኢንዱስትሪ ፓርክም የሼድ ግንባታው እንደ ሌሎች አይደለም›› ነው ያሉት ከንቲባ ሙሉቀን በማብራሪያቸው፡፡ የከተማዋን ማስተር ፕላን በተመለከተም ‹‹በጀት መድቦ የሚሠራው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ነው፤ በፍጥነት እንዲጠናቅቅም እየጣርን ነው›› ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ሠላም እና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ ‹‹የአማራ ጥያቄ የዲሞክራሲ እና የኅልውና ነው፡፡ አማራ በክልሉም ውስጥ ሆኖ የኅልውና ችግሮች አሉበት›› ብለዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሉ የአማራን ሕዝብ በሚመጥን አግባብ መደራጀት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ ‹‹ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባሕር ዳር ድንገት ባደረግነው አሰሳ በሕገ ወጥ ሥራ የተሠማሩ 89 ተሸከርካሪዎችን እና ሕገ-ወጦችን በቁጥጥር ስር አውለናል፡፡ አማራን ለማፍረስ ያልተሠራ ስለሌለ ችግሮቹ ብዙ ናቸው›› ሲሉም ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ተናግረዋል፡፡

የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ‹‹ገፊዎች መሆን አንፈልግም፤ ወደፊትም ሌሎችን አንጋፋም፤ ለመጋፋትም ፍላጎትም የለንም፡፡ በፓርቲው ውስጥ የነቀዘውን ለማስወገድ ቆርጠን ተነስተን እየሠራን ነው›› ሲሉ ፓርቲው በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡

በየከተሞቹ የሚፈጠሩት የፀጥታ ችግሮች መልሰው ሕዝቡን እየጎዱ መሆናቸውንም አቶ ዮሐንስ ጠቁመዋል፡፡

አዴፓ ከአማራ ጥቅም ውጭ የሚቆምለት ዓለማ እንደሌለው ያስታወቁት አቶ ዮሐንስ ‹‹በዚህ አትጠራጠሩን፤ ከሌሎች ድርጅቶች ጋርም አብረን እንሥራ ብለናል፡፡ በሁሉም መልኩ እመኑን ዝግጁ ነን፤ ግን ደግሞ እጅ በመጠምዘዝ አይሆንም›› ብለዋል፡፡ አዴፓ በማኅበራዊ ሚዲያ ተሸብቦና ተዋክቦ ወደኋላ እንደማይመለስ ያስገነዘቡት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ‹‹መሪዎችን ማጥራትና ማስተካከል ይኖርብናል፤ ሁሉም ማኅበረሰብ በጥርጣሬ ወሬ መነዳት ግን የለበትም፡፡ መሪዎቹን የምታስፈራሯቸው ከሆነ ሊሠሩ አይችሉም፤ የሚለቁትንም አክብረን ሲቀላቀሉም ታግዘው ሳይዋከቡ መሆን ይገበዋል›› ነው ያሉት፡፡ 
የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ሕገ-መንግሥቱ ላይ ያሉ ጉዳዮች መሻሻላቸው እንደማይቀርም አቶ ዮሐንስ ለተወያዮቹ አብራርተዋል፡፡ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ወደ ልማት መግባት እንዳባቸው የቀረበውን ሐሳብም ትክክል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ደግሞ ‹‹እኛ የአማራ መሪ ነን ብለን እስከተቀመጥን ድረስ በሕዝቡ መመከር አለብን፤ ወደ ውይይቱ ስንመጣም አክብረን ነው፡፡ የሕዝቡን ጩኸት መስማት አለብን፤ ሁሉም ሐሳብ ወጥቷል ባይባልም ሕዝቡ መመሪያ ሰጥቶናል›› ብለዋል፡፡

ወጣቱን መገንባት ካልተቻለ የወደፊቱን አማራ ክልል እና ኢትዮጵያን መምራት እንደማይቻል ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳደሩ ‹‹የልማት ሥራውን አንዱ ላይ ስናተኩር ሌላው እንዳይቀር እየሠራን ነው፤ የአስተዳር እና ፀጥታ ጉዳይን በተመለከተ የመንግሥት የመጀመሪያ ሥራ በመሆኑ ይህን እየሠራን ነው›› ብለዋል፡፡

ባለሀብቶች ተረጋግተው እንዲያለሙና የፀጥታ ሥራው በተለያዩ አካባቢዎች እየተሠራ እንደሆነ ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ ሕዝቡ አብሮ እንዲሠራና የአካባቢውን ፀጥታ እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡ ችግር የሚፈጥሩትን መንግሥት መስመር እንደሚያስይዝም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በፌዴራል አካላት ሊታፈኑ ነበር የተባሉ ግለሰቦችን በተመለከተም ‹‹የተሰራጨው ወሬ ውሸት ነው፤ ያለክልሉ ፈቃድ ማንም ሰው በመከላከያ ኃይል ሊወሰድ አይችልም፡፡ የምንመራው ሀገር በመሆኑ ከሌሎች ክልሎች ጋር አብረን እንሠራለን፤ ግን ደግሞ የክልሉን ሕዝብ የሚነካ ጉዳይ ያንገበግበናል›› ነው ያሉት፡፡ 
በጎጥ መከፋፈልን በማስወገድ ‹‹ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሸዋ…›› ከሚሉ ከፋፋዮች አጀንዳ ወጥቶ ጠንካራ አማራ መገንባት ላይ ማተኮር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ውስጥን አጠናክሮ ሌሎች ጉዳዮችን መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ‹‹ከተባበርን ኃይል ይኖረናል፤ ካልተባበርን ግን ተጠላልፈን እንወድቃለን›› ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡ 
የሊዝ አዋጅ መሻሻሉን፣ የሥራ ፈጠራ ሥራው አዝጋሚ መሆኑን፣ ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል የሚገባው መሆኑንና ለወሰንና ለማንነት ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ ፎቶ፡- አስማማው በቀለ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የመ/ሰራዊትን መለያ ለብሶ ከሱዳን ወደ ወልቃይት ሊገባ የነበረ የትህነግ የሽብር ሃይል ተደመሰሰ፤
0Shares
0