ማስታወሻ – እንደመግቢያ

የዛሬ ሰላሳ ዓመት ከሰዓት በኋላ ግንቦት 8 ቀን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊ ጄቶችና ሔሊኮፕተሮች በአዲስ አበባ አየር ላይ ባለተለመደ ዝቅታ በአስደንጋጭ ድምጽ ሲያፈተልኩና ሲያንዣብቡ ገና የሐያ ዓመት ወጣት ነበርኩ፡፡

ማንም ሳይነግረኝ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየተደረገ መሆኑን በመገመት ወደ ቤት አመራሁ፡፡ብዙም ሳይቆይ የአባቴ አጃቢ የነበሩ ወታደሮች ከሌሎች ሁለት ወታደሮች ጋር በመሆን ቤታችን ፊት ለፊት እነሱን ለማውረድ ከቆመው የከባድ የጪነት መኪና ወርደው የግቢውን በር አንኳኳኩ፡፡ የጭነቱ መኪና ፊቱን ወደመጣበት፣ የቦሌ መንገድ እዙሮ ከጀርባ የታጨቁትን ወታደሮች ይዞ መንገዱን ጀመረ።

ከጭነት መኪናው ለወረዱት ወታደሮች በሩን የከፈትኩላቸው እኔ ነበርኩ፡፡ ሙሉ ትጥቅ ታጥቀዋል። የአባቴ አጃቢ ከነበረው የአስር አለቃ ጌታቸው ጋር ሰላምታ ተለዋውጠን፣ ወደ ውስጥ እንዲገቡ ጋብዝኳቸው፡፡ከአስመራ በአውሮፕላን ከብዙ ወታደሮች ጋር እንደመጡና እኛ ቤት ወርደው ጥበቃ እንዲያደርጉ በአባቴ መታዘዛቸውን ነገረኝ፡፡

ከእርሱ ጋር ያሉት የማላውቃቸው ሁለቱ ወታደሮች የጄኔራል ሁሴን አህመድ አጃቢዎች አንደሆኑና እነሱም እንዲሁ እኛ ቤት እንዲቆዩ መታዛዛቸውን አስረዳኝ፡፡ አውሮፕላን ወስጥ እያሉ ጄኔራል ቁምላቸው መንግስቱ ኃይለማርያም ተገድሎ ከስልጣን እንደ ወረደ የሚገልጽ ወረቀት ማደላቸውን ሲነግረኝ የገመትነው ዕውነት መሆኑን አራጋገጥን፡፡

ሁኔታው እስኪጣራ ድረስ እቤት ከመቀመጥ ወደ ማይጠረጠር ወዳጅ ቤት መሄድን መርጠን እቤት የነበረውን መሣሪያ ተከፋፍለን ቤታችንን ለቀን ወጣን፡፡ ትላቅ ወንድሜ ዮናስ ብሄራዊ ውትድርና አንደኛ ዙር ሄዶ ለሁለት እመት ተኩል ያገለገለ ነበር። ስለመሳሪያ አጠቃቀም ያውቃል። እኔ ደግሞ አባቴ በሚመራው የጦር ሰፈር በየመሳሪያ ግምጃ ቤቱ ጥይት በካርታ እንደጨዋታ ስሞላ፣ ክላሽንኮቭ መትረየስ እየፈታሁ እየገጠምኩ ስላደኩ የደረሰኝ ለአባቴ በስጦታ የተሰጠ የጀርመን ሉጋር ሽጉጥ ቢያንስ አነጣጥሬ መተኮስ እንደምችል አልተጠራጠርኩም። የመፈንቀለ መንግስቱ ሙከራ ከመጀመሩ መክሸፉን ማታ ብንሰማም ከአስመራ የሚተላለፈው ዜና ደግሞ ሙከራው እየቀጠለ መሆኑን ነበር የሚገልጸው፡፡ አባቴ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ የሚመራውን የሁለተኛ አብዮታዊ ሠራዊት አስፈላጊ ከሆነ አዲስ አበባ ድረስ በከፊል በማምጣት ሙከራውን እስከመጨረሻው እንደሚገፋበት በአስመራ ሬዲዮ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልዕክት አስተላለፈ፡፡

ለሶስት ቀናት የተለያዩ ክፍሎች ሙከራውን እንዲደግፉ ለማስተባበር ሞከረ፡፡ አስመራ የተደራጀ የአየር ሃይልና የኢትዮጵየ አየር መንገድ አውሮፕላኖች የሚገኙበት ስለነበረ ሁኔታው ካልተሳካ አገሩን ለቆ ይሄዳል የሚል ተስፋ ነበረን፡፡ የቤተሰብ ተስፋ፡፡ አባቴ ግን ያስተባበራቸውን የጦር ጓዶቹንና የሚወደውን አገሩን ጥሎ እንደማይሄድ ልባችን ያውቅ ነበር፡፡ እጁን አንደማይሰጥ ደግሞ ግልጽ ነበር፡፡ “አንድ የጦር መኮንን የጄኔራል ማዕረግ ከደረሰ እጁን ለጠላት መስጠት አገር መማዋረድ ነው ፣ ከቻለ ራሱን ማጥፋት አለበት ይል ነበር፡፡”

ይህን ደግሞ ብዙ የቀድሞ የጦር መኮንኖች የሚያምኑበት ነው፡፡ ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ፣ ጄኔራል አምሐ ደስታ በመፈንቅለ መንግስቱ በአዲስ አበባ ራሳቸውን በመሰዋት፣ ጄኔራል ለገሠ አበጀ በትግራይ ፣ኮሎኔል ካሳ ገብረማርያም በናቅፋ፣ ጀ/ል ተሾመ ተሰማ በምጽዋ ራሳቸውን መስዋእት በማድረገ ያለፉትን ነፍሳቸው ያለችበት ቦታ ስትሄዱ ጠይቁ፡፡

ስለ መፈንቅለ መንግስት ሙከራው “አባቴ ያችን ሰዓት” በተሰኘው መጽሃፌ ዝርዝሩን ስለጻፍኩ እዚህ መድገም አልፈልግም፡፡ ከሰላሳ አመት በኋላ ማስታወስ ያለብን ሙከራውን ብቻ ሳይሆን በዛ ሙከራ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ የጦር መሪዎች ለአገራቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ የከፈለኡትን መስዋእትነትና ከእነሱ ህይወት ይህ ትውልድ ሊቀስም የሚችለውን ትምህርት ነው። የመፈንቅለ መንግስቱን ሙከራ ከሰላሳ አመታት በኋ ሳስበው ጊዜው ምን ያህል እንደተቀየረና አገራችን ምን ያህል እንደተለወጠች አስተዋልኩ፡፡ አባቴና ጓደኞቹን የሚያስተሳስራቸው ለአገራቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የነበራቸው ፍቅር ነበር፡፡

መንግስቱ ኃይለ ማርያም በፍርሐት ከመኮብለሉ ሁለት አመት በፊት ጀምሮ ከዛም በኋላ ለ27 አመት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ስላደረጉት የጦር መሪዎች የተለያዬ ውሸቶ ተነግሯል፡፡ ተጽፏልም፡፡ ዕውነቱን የሚያውቀው ብዙ ስለነበር ታሪካቸው አንዳንዶች እንደተፈለገው አልጎደፈም፡፡የመንግስቱ ኃይለማርያም ደጋፊና ተቆርቋሪ የሆኑ አንዳንድ ካድሬዎችና የወታደራዊ ደሕንነት አባላት ይህን ነው ለማድረግ የሞከሩት። ሁሉም አይደሉም ከመካከላቸው ዕውነቱን የጻፉ አሉ። “ትውልድ ያናወጠ ጦርነት “ እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል፡፡

እነዚህን አንጋፋ የጦር መሪዎች እንደ ግል ጥቅም ወይም ስልጣን ፈላጊ ከዛም አልፎ አልፎ አሻጥር እየሰሩ ጦሩን ሲያስጨርሱ እንደነበር አድርገው ሲጽፉ። ሌት ተቀን ስለ አገሩ ሲጨነቅና ሲቆረቆር ቢበዛ 4 ወይም 5 ሰዓት ብቻ እየተኛ ሌሊት ተነስቶ ወደ ተረኛ መኮንኖች ጋር እየደወለ የሰጠው ትዕዛዝ መፈጸሙን ሲከታተል የሚያነጋ ፣ ጦሩ ድል ሲያደርግ በደስታ የሚሞላ። ጦሩ ችግር ሲገጥመውና ጓዶቹ ሲሰዉ በሐዘን የሚዘፈቀውን አባቴን እያስታወስኩ የእነዚያን ጀግኖች ታሪክ በወረፋ ዕጃቸውን ለወያኔዎ እየሰጡ ህይወታቸውን ባተረፉ ሰዎች እጅ ሲጎድፍ ሳይ ከማዘንም አልፎ ያበሳጨኛል።

የኔ አባት ለ 38 አመታት አገሩን አገልግሏል፡፡ ኮርያ ዘምቷል፡፡ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ አየር ወለድ ጦር ካቋቋሙት ጥቂት መኮንኖች አንዱ ነው፡፡ ገና በአጼ ሃይለ ስላሴ ዘመን ሶማሊያ ኢትዮጵያን ስትወር በመጀመሪያው የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት፣ በቶጎ ውጫሌ ጦርነት የአየር ወለዱን ጦር መርቶ ድል አድርጓል፡፡ ከዚያ በባሌ ዘመቻ በሌ/ጄነራል ጃጋማ ኬሎ ስር የአየር ወለድ ጦር መርቶ ተዋግቷል፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የወታደራዊ ትምሕርት ዳሬክተር ሆኖ በታወቀው የሐረር ጦር አካዳሚ ብዙ ምርጥ መኮንኖችን አፍርቷል፡፡ በ1970 የሶማሌ ጦር አዋሳ ለመድረስ 60 ኪሎሜትር ሲቀረው የደቡብ ዕዝ አዛዥ ሆኖ እንደ አንድ የመስመር ጦር መሪ ከጦሩ ጋር አብሮ እየተዋጋ የሶማሌ ጦር ከኢትዮጵያ ምድር እስከሚወጣ ድረስ ጦሩን መርቷል፡፡ የአባቴን የግል ማህደር እልፎ አልፎ እያነሳሁ አነባለሁ። በየቀኑ የሚያደርገውን ይጽፍ ነበር። ለ 1000 ገጽ በላይ የሚሆን ማህደሩን በኮምፒውተር ስካን አሰደርጌ አስቀምጫለሁ። ለምሳሌ በኤርትራ ስለተደረገው የባህረ ነጋሽ ዘምቻ የጻፈውን ከመጽሃፌ ግርጌ አስገብቼ ነበር።

ከታች የተቀመጠው በደቡብ ኢትዮጵያ ፊሉቱና ዶሎን ለማስለቀቅ የተደረገውን የሶስት ቀን ጦርነት የሚገልጽ ነው። የጀግናው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ጄት አብራሪ የጀ/ል ለገሰ ተፈራ ጄት ተመቶ የወደቀው በዚህ ጦርነት ላይ ነበር። የግል ማህደሩ ከ400 በላይ ጸረ ታንክና ጸረ ሰው ፈንጂ እያነሱ ወደፊት ተጉዘው የሶማሊያን ወራሪ ጦር እንደደመሰሱ ያሳያል።

ከሁሉ የገረመኝ ጽሁፉ ይህኛው ነው። “በ 3/7/70 0800 ሰአት ከዶሎ 17 ኪ/ሜትር ላይ ዋናው ጦር እንዲቆም ተደርጎ በአንድ ሻምበል ጦር (ወደ 400 የሰው ሃይል) ወደ ዶሎ ተነቃንቄ ዶሎ ከተማ ስንደርስ የሶማሌ ወታደር ከቀድሞው የጦር ሰፈራችን በመኪና ለማምለጥ ሲበር ተከታትለን ከነመኪናው ማረክን ሌሎችም 5 ወታደሮች ተታኩሰው ወደ ጫካ ስለገቡ መደምሰስ አልተቻለም።”

General Demissie Bulto's note.

ከዚያም ወደ ሐረር የምስራቅ ዕዝ አዛዥ ሆኖ በመሄድ የሶማሌን ጦር ከኢትዮጵያ ምድር በጠቅላላ ያስወጣውን ዘመቻ መርቶ ድልን ተጎናጽፏል፡፡

በመጨረሻም በኤርትራ ከረን ሊያዝ ሲል በአዛዥነት ተመድቦ የኢትዮጵያ ጦር ከረንን ተከላክሎ መልሶ በማጥቃት ወደ አፋ ቤት እንዲያመራ በማድረግ የነበረውን ሁኔታ ለመቀየር ችሎ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሁለት የተቀነባበሩ ዘመቻዎችን ከሐረር በጊዜያዊ ምድባ ወደ ኤርትራ ተጉዞ በዘመቻ መሪነት አገልግሏል ፡፡ እነዚህ ሁለት ዘመቻዎች የቀይ ባሕርና የባሕረ ነጋሽ ዘመቻ የሚባሉ ባሬንቱን ከማስለቀቅ ባሻገር ናቅፋን ለመያዝ የተቃረቡበት ዘመቻዎች ነበሩ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አገሪቱ የነበረችበት አዘቅት በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ፖሊሲ ምክንያት የተፈጠሩ ብዙ ችግሮች በጣም ያሳስቡትና ያስጨንቁት ነበር፡፡ የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ በተደጋጋሚ የሚቻለውን አድርጓል፡፡ ከቅርብ ጓደኛውና ከትግል አጋሩ ከጄኔራል መርዕድ ንጉሴ ጋር ስለአገሪቱና ስለምትከተለው ፖሊሲ ብዙ ይወያዩ ነበር፡፡ የማይስማሙበት ፖሊሲ ብዙ ነበር፡፡ ለምሳሌ የሰፈራ ፖሊሲ፣ በሚሊታሪውና በሕዝቡ መሐል ብዙ ቅሬታን ፈጥሮ ነበር፡፡ በኤርትራና በትግራይ የሚደረጉት ጦርነቶች የብዙ ኢትዮጵያውያን ሕይወት በማጥፋት አገሪቱ ላይ ያመጣው ቀውስ እንቅልፍ ይነሳቸው ነበር፡፡

የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውድቀት ለሰራዊቱ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ፣ ከምግብ ፣ ከውሃ ጀምሮ በተገቢው ማቅረብ አለመቻሉ ያበሳጫቸው ነበር። የሚሰማ መሪ ባለመኖሩ መፍትሄ ማግኘት አልተቻለም።

ጄኔራል ፋንታ ከታሰሩ በኋላ በኢትዮጵየ ቴሌቪዥን የተቀዳው ቃለ መጠይቅ መንግስቱ ኃይለማርያም ከሸሸ በኋላ ለህዝብ ተለቆ ነበር፡፡ እሳቸው እንዳሉት የመፈንቅለ መንግስቱ ዓላማ ለጦርነቱ መፍትሔ ለመስጠት “ከወንበዴው ጋር ጭምር በጠረጴዛ ዙርያ ለመነጋገር ነበር”። ታዲያ አሁን አንዳንዶች ሲጽፉ ለስልጣን ብለው ነው ሲሉ ይገርመኛል፡፡ ለመሆኑ ስንቱ ናቸው ሰልጣን የሚይዙት? የአገር መሪ የሚሆነው አንድ ሰው ነው፡፡ ከአስመራ ብቻ ከ 20 በላይ የሚሆኑ ጄኔራሎች ተሳትፈዋል፡፡ አዲስ አበባም እንዲሁ፡፡ መፈንቅለ መንግስት ያክል ለሕይወት ተቆርጦ የሚገባበት ሙከራ በነዚህ ሰዎች ሁሉ ስምምነት ሲደረግ እንዴት ለስልጣን ነው ይባላል? ስልጣን ደግሞ ነበራቸው፡፡ እንዳልኩት ከአንድ ወይም ከሁለት ሰዎች ሌላ የቀሩት ከነበራቸው ስልጣን የሚጨምሩት ብዙም አልነበረም፡፡ ስልጣን መጨመር ከሆነ ዓላማው ለመንግስቱ ኋይለ ማርያም እያጎበደዱ ስልጣን መጨመር ይቀል ነበር፡፡ እዚህ ላይ መንግስቱ ሃ/ማርያምን ለምን በአክብሮት አንቱ እያልኩ እንደማልጽፍ ትንሽ ላስረዳ። በመጀመሪያ በታሪክ የተወሰኑ ግለሰቦች ሲነሱ አንተ ተብለው የሚጠሩ አሉ። የሰሩት አጸያፊ እና ጭካኔ የተሞላባቸው ተግባራት ምክነያት። ለምሳሌ ሙሰሊኒ፣ ሂትለር፣ ግራኝ አህመድ፣ በታሪክ ሲነሱ በእድሜም ይሁን በስራ የሚገኝ ከበሬታ አይሰጣቸውም።

አንዳንድ የመንግስቱ ሃ/ማርያም ደጋፊዎች በ 29 አመት በኋላም በአገራችን ላይ ያደረሰውን ጥፋት ረስተው ይሁን ወይንም ኣውቀው ለመሸፈን የሚናገሩትን ስሰማ ይገርመኛል። መንግስቱ ሀ/ማርያም አገራችን አሁን ለደሰችበት ቀውስ ዋነኛ ተጠያቂ ግለሰብ ነው። በሀገራችን ታሪክ አገሪቷን ወደ ተሻለና ትልቅ ደረጃ እንዳትደርስ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱ ግለሰቦች መካከል በዋናነኝነት የሚመደብ ግለሰብ ነው። እውቆ አደረገው ለማለት ባይቻልም። አገር ለማጥፋት ሆን ብሎ አውቆ አደረገው አልልም። ያደረሰው ጥፋት በአብዛኛው የኢትዮጵያን የሩቅ ዘመን ጥቅም ማየት አለመቻሉ፣ የሚወስነው ውሳኔ ከአገሪቷ የሩቅ ዘመን ጥቅም ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን የራሱን ስልጣን ማጠናከር እና ማደላደል ያል የተመሰረተ በመሆኑ ነበር።

ለዚህም ነው ገና ሲጀመር የታሪክ ቅርጽ የሆኑትን እሱ እንደገና ጊዜ ቢፈጠር የማይመጥናቸውን እንደ ጸሃፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ እና ልጅ እንዳልካቸው መኮንን የመሳሰለቱን ኢትዮጵያውያን ያለፍርድ በግፍ የገደለው። ከዚያም እነ ጀ/ል ተፈሪ ባንቲን የወደፊት የአገሪቷን ጥቅም በማየት ከተቃዋሚ ድርጅቶች ኢህአፓንም ጨምሮ እንወያይ ሲሉ በተቀነባበረ መንገድ ገደላቸው። ጀ/ል አማን እንዶም የኤርትራን ችግር ለመፍታት መንገድ ሲፈልጉ አርቆ ማስተዋል ስለተሳነው ገደላቸው። ደጋግሜ እንደተናገርኩት በእኔ ቆጠራ ብቻ 54 ጀነራሎችን ገድሎአል። ከሁሉ የሚያሳዝነው በመፈንቅለ መንግስቱ በመጨረሻው ደቄቃ ተስማምተው ተሳትፈዋል ተብለው የተከሰሱትን 18 ምርጥ ጀነራሎች ከአንድ አመት እስር በኋላ አገራቸውን እንዲያገለግሉ ከማድረግ ይልቅ በግፍ ገድሏቸዋል። ከኤርትራ ብቻ 435 መኮንኖችን እስር ቤት ወርውሮ ጦሩ ያለብቁ የስትራቲጂክና የፊልድ መሪዎች እርቃኑን እንዲጋለጥ አድርጎአል።

ይህ በጦሩ ውስጥ ያደረገው በከፍል ነው። ሲቪሉን ህዝብ ደገሞ በሰፈራ፣ በብሄራዊ ውትድርና፣ በጸረ አብዮተኛነት፣ ውንጀላ ወዘተ ሲያጉላላና ሲያሰቃይ ለ17 እመት በሰአት እላፊ ገደብ ህዝቡን ሲያሰቃይ፣ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመቃወም መብቶች ተነግፎ ይህ ሁሉ አልበቃ ሲለው የመንግስት ሰራተኛ የሚለብሰው ልብስ በሰሜን ኮሪያ ሞዴል የተሰራ ስማያዊ ካኪና የካኪ ቀለም ያለው በጣም የሚያስቀይም ጃኬትና ሱሪ እንዲሆን አዞ፣ ህዝብን መሳቂያ ያደረገ ሰው ነው።

ያን ግዜ አይደለም አሁን ለብዙ አመት በኋላ እንኳን ኢትዮጵያን የሚያክል አገር ለማስተዳደር የሚችል አእምሮ፣ ተመክሮ፣ እንዲሁም ምንአልባት አስተዳደጉም ጭምር የነፈገው ሰብእና እንዳልነበረው ግልጽ ነው። እስካሁን የሰራውን ስህተት አንድ ቀን እንኳን በጸጸት ገልጾ አያውቅም። በቅርቡ ዶ/ር አበይ የኢትዮጵያን ህዝን ዝቅ ብዬ ይቅርታ እጠይቃለሁ ሲሉ በመካከላቸው ያለው ትልቅ ልዩነት ጎልቶ ታየኝ። መግደል፣ ማሰር፣ ማሰቃየት ቀላል ነው። የጥሩ መሪ ባህሪ ግን አይደለም። ችግሮችን በህግ መፍታት፣ የዜጎችን መብት መጠበቅ፣ ለስልጣን ሳይሆን ለሀገር እና ለህዝብ አስቦ መወሰን ጥሩ አእምሮና ህሊና ይጠይቃል። መንግስቱ ትምህርቱም፣ እውቀቱም፣ ተመክሮ፣ ሰብእና፣ ስነምግባር፣ ራእይ፣ አስተዳደግ ወዘተ እንዳልነበረው ጭካኔዎቹ ይመሰክራሉ። አንድ አገር ተረክቦ ለሁለት ከፍሎ፣ ህዝቡን አራቁቶ፣ እነደጠላት እንዲተያይ አድርጎ፣ ብዙዎችን አፈናቅሎ፣ ለስደት ዳርጎ፣ ብዙ ጀግኖችን ገድሎ እስከ አንድ ስውና አንድ ጥይት የሚል የሞኝ መፈክር ሲያሰማ ከርሞ በመጨረሻ ቤተሰቡን አሸሸ፣ እሱም ፈረጠጠ።

በቅርቡ የታተመው የጄኔራል መርዕድ ንጉሴ መጽሐፍ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው ይህንኑ ሃቅ ነው፡፡ መጽሐፉ በልጆቻቸው ቢጻፍም በውስጡ የያዘው ሃሳብ በጄኔራል መርዕድ የዕለት ማስታወሻ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ጄኔራል መርዕድን እንደ አጎት ነበር የማየው በጣምም ያቀርበኝ ነበር። ስለ አገሩ በጣም የሚጨነቅ ሰው አንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ከአባቴ ጋር ሐረር አንድ ቤት ውስጥ ለጥቂት ወራት ሲኖሩ እኔም ለክረምት ዕረፍት ሄጄ ብዙ ጊዜ አብረን አሳልፈናል፡፡ነገር ግን መጽሐፉን ሳነብ በጣም ተደነቅሁ፡፡ የነበረውን አርቆ አስተዋይነት አሁን ባለሁበት የእውቀት ደረጃ መለስ ብዬ ሳየው በዚያን ዘመን በዛ ውጥረት ይህን አይነት አርቆ አስተዋይ አዕምሮ በመኖሩ ተገረምኩ፡፡ ብዙ በቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር አባላት የተጻፉ መጻሕፍትን አንብቤያለሁ የዚህን አይነት የበሰለ የጦር ፣ ማሕበረ ሰብ፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ዕሳቤዎች የያዘ ጽሑፍ አላየሁም፡፡

አንብቤ ስጨርስ የተሰማኝ ስሜት “ትላልቆቹ አልቀዋል” የሚል ነበር፡፡ አገራችን በዚህ አልታደለችም፡፡ የጀግኖቹን ታሪክ የሚጽፉት ጀግኖቹ ሳይሆኑ የተረፉት ናቸው ግማሾቹም የጀግኖቹ ገዳዮች፡፡

ወደ ኋላ ልመለስ፡፡

መፈንቅለ መንግስቱን የሞከሩት የጦር መሪዎችና ተከታዮቻቸውን ሳስብ አገራችን ምን ያህል እንደተቀየረች አስተዋልኩ ፡፡ ይህን ያልኩት ምክንያት እነዚያን ሰዎች ያገናኛቸው ብሔር ወይም ሃይማኖት ወይም የፖሊቲካ አመለካከት ሳይሆን ለአገራቸው የነበራቸው ፍቅር በመሆኑ ነው፡፡ ከዛም አልፎ ምንም እንኳን በአገሪቱ ከፍተኛ አመራር ላይ ቢሆኑም አገራቸው በአንድ ሰው አምባገነን አመራር ስር እየማቀቀች በጦርነት ተወጥራ መኖርና መቀጠል እንደሌለባት ስለወሰኑ ነበር፡፡ ኦሮሞ ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ትግሬ ፣ ኤርትራ እንዲሁም ከሌሎች ብሔሮች የተውጣጡ ቢሆንም ያን እንደ ምክንያት፣ እንደ መሰብሰቢያ፣ እንደ ጥሩ ወይም አንደ መጥፎ ማሰብ ወይም ማንሳት ቀርቶ ከቁጥር ሳይከቱ ነገር ግን አንዱ የአንዱን ብሔር በማክበር ነበር የሚሰሩት፡፡ የብሔር ጭቆና አለ የለም የሚለው ጥያቄ ወደ ጦር ሠራዊቱ ውስጥ ስንገባ መልሱ የተለዬ ነበር፡፡ ከአባቴ ጋር ከከረን አልፌ ማሳህሊት ተራራ ላይ ሆነን ከጄኔራል በሃይሉ ክንዴ (ያኔ ኮሎኔል) በጦር ሜዳ ሬድዮ ጠርቶ ጋር በኦሮሚኛ ወታደራዊ ትዕዛዝ ሲሰጥ አይቻለሁ፡፡

ከሁሉ በላይ የሚያቀርበውና በስራው የሚመካበት ረዳት መኮንን ኮ/ል ተስፋ የትግራይ ተወላጅ የሐረር አካዳሚ ምሩቅ ነበር፡፡ የደቡብ ዕዝ የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ነበር፡፡ ከብዙ አመት በኋላ አባቴ ወደ ኤርትራ ሲመደብ ካለበት አስፈልጎ ኮ/ል ተስፋን ወደ ኤርትራ አዛወረው፡፡ ኮ/ል ተስፋ ከኤርትራ ተነስቶ አዲስ አበባ ዙሪያ ወረቀት አስበትኗል፡፡በመፈንቅለ መንግሥቱ ጊዜ፡፡ መፈንቅለ መንግስቱ ሲከሽፍ በአስመራ አየር ሃይል ግቢ እንደተገደለ ሰምቻለሁ፡፡ አስመራ ከተገደሉት ጄኔራሎች መሃል ያኔ የኤርትራ ክፍለ ሀገር የነበረችው ተወላጅ የሆኑት ጄኔራል አፈወርቅም ወልደ ሚካኤል ይገኙበታል፡፡ ሀሉንም ያገናኛቸውና ለአንድ ኣላማ ያሰለፋቸው ኢትዮጵያዊነታቸውና ለአገራቸው የነበራቸው ፍቅር ነው፡፡

በመጨረሻም ልጠቅሰው የምፈልገው በጄኔራል መርዕድ ንጉሴ አዲስ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው የመፈንቅለ መንግስቱ ተሳታፊዎች ከተለያዬ የጦር ክፍል የተውጣጡ እንደነበሩ ነው፡፡ ከከብር ዘበኛ ሁለት (አባቴና ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ) ከጦር ሠራዊት በጣም ብዙ (ጄኔራል ኃይሉ ገብረ ሚካኤል፣ ጄኔራል አበራ አበበ፣ ጄኔራል ቁምላቸው፣ ጀ/ል አለማየሁ ደስታ፣ ጀ/ል ነጋሽ ወልደየስ፣ ጀ/ል ወርቁ ቸርነት፣ የሃረር ጦር አካዳሚ ምሩቆች የነበሩት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው። ከሳንድረስት የእንግሊዝ የጦር አካዳሚ 1ኛ ወጥቶ ከእንግሊዝ ንግስት ከፍተኛውን ሽልማት የተቀበልለው ጀ/ል ተስፋዬ ትርፌ፣ ጀ/ል ደሳለኝ አበበ፣ ጀ/ል እርቅይሁን ባይሳ፣ ጀ/ል ታደሰ ተሰማ፣ ኮ/ል አርጋው ባንቲይርጉን ጨምሮ) በተጫማሪም ከአየር ኃይል (ጀ/ል ፋንታ በላይ፣ ጀ/ል አመሃ ደስታ፡ ጀ/ል ሰለሞን ደሳለኝ)፣ ከባሕር ኃይል (አድሚራል ተስፋዬ ብርሃኑ) እንዲሁም ከፖሊስ (ጀ/ል ወርቁ ዘውዴ፣ ጀ/ል እንግዳ ወልደአምልክ) ሁሉ ተሳትፈውበታል፡፡

የኢትዮጵያን ያንን ግዙፍና ስመጥሩ ጦር መሳቂያና ማፈሪያ ያደረገው መንግስቱ ኃይለ ማርያም ነው፡፡ እንደ ምሰሶ ሆነው የተሸከሙትን የጦር አለቆች አስገድሎና ገሎ የቀሩትንም አስሮ ጦሩን ባዶ ካደረገ በኋላ እንደ ክብሪት ሲያጠፋው የኖረውን የሌላውን ሕይወት የሱ ህይወት አደጋ ላይ ሲሆን ግን ህይወቱ አጓጉቶት በፍርሃት አገሩን ለቆ ጠፋ።

ካለ መንግስቱ ኃይለማርያም አመራር ወደፊት መሄድ አትችልም እየተባለ ሲነገረው የቆየው ጦር መንግስቱ ሄደ ሲሉት ለመንግስቱ ሲዋጋ እንደኖረ ሁሉ መሳሪያውን ቢችል እየሸጠ ካልሆነም እየጣለ ወደ የቦታው ተበተነ፡፡

ቀድሞውንም ኢትዮጵያን የምታክል በአፍሪካና በአለም ከፍተኛ ቦታ የነበራትን አገር ለመምራት ብቁ አዕምሮም፣ ተመክሮችም፣ አስተውሎም፣ ብቃቱም እንዳልነበረው ግልጽ ነው፡፡ አሁን ወደኋላ ዘወር ብለን ስናስብ መንግሥቱ በዚህ ሁኔታ ያን የሚያክል አገርና ሕዝብ እመራለሁ ብሎ ሲነሳ ማሰቡ ራሱ የሚገርም ነው።

ጭካኔውን መለስ ብዮ ሳየው ምን ያክል ስብእና የሌለው ሰው መሆኑ ይገርመኛል። አባቴ 38 አመት አገሩን አግልግሎ ሲያልፍ አስክሬኑን እንኳን ለቤተሰቡ ተልኮ የቀብር ሰነስርአት እንዲደረግ አልፈቀደም። ወይም አላሰበውም። ከሁለት እመት በኋላ አገር ለቆ ሲሄድ እናቴ ኮሚቴ አቋቁማ የኢህአዴግን መንግስት አስፈቅዳ፣ አስመራ ድረሰ በመሄድ በኤርትራ መንግስትና የአካባቢ ህዝብ ባደረጉት ከፍተኛ ትብብር፣ ፈቃድ አግኝታ ፣ በጉዋዶቹ ጋር በአንድ ላይ የተቀበሩበትን ቦታ በአገሬው ህዝብ ተመርታ፣ አስከሬናቸውን ቆማ አስቆፍራ፣ አስወጥታ፣ ለአካባባዊው ህዝብ ፍየልና እና በግ አሳርዳ ጋብዛ፣ በአካባቢዊው በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን አስቀድሳ፣ ተዝካር አብልታ፣ የጀግኖቹን አስክሬን ይዛ ተመልሳለች። በአገራችን ታሪክ የባለቤቷን አስከሬን ከወደቀበት አምጥታ በክብር ያስቀበረች የማውቀውን እናቴን ወ/ሮ አስቴር አዳሙን ብቻ ነው።

በቅርቡ ከአንድ የቀድሞ ጄኔራል ጋር በስልክ ሳወራ ለሃያ ሰባት አመት የቀድሞ ሠራዊት አባላትና ቤተሰቦቻቻው አንገታቸውን እንዲደፉ ተደርጓል አሉኝ፡፡ አባባላቸው ቢገባኝም የእኔን ስሜት ግን እንደማይገልጸው ነገርኳቸው፡፡ አባቴ ዕጁን ሰጥቶ ተማርኮ በእስር ቤት እዚህ ሂድ፣ እዛ ቁጭ በል ፣ ና ! ተመለስ ! ሲባል ባይ ኖሮ እርግጥ አንገቴን ደፍቼ እኖር ነበር፡፡ አባቴ በሞትና በሕይወት ውስጥ ይኖር እንደነበር አብሬው ጦር ሜዳ ድረስ ሄጄ ያየሁት ስለነበር የሞትን ሐቅነት ከተቀበልኩ ቆይቼ ነበር፡፡ እንደ አንድ የጦር መሪ ለቆመለት አላማ ሲታገል ሕይወቱ አልፏል፡፡ እንደ አንድ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ አገሩን አገልግሎ ለአገሩ ሲል የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአምባ ገነን አገዛዝ ነጻ ለማውጣት በመረጠው መንገድ ተሰውቷል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር የኢትዮጵያ እንጂ የደርግ እንዳልነበረ ከደርግ በፊት ያበረከተው 23 ዓመታት የውትድርና ዘመን ብቻ ሳይሆን በደቡብ በምስራቅና በሰሜን የከፈለው መስዋዕትነት በመጨረሻም ለአገሩ ያፈሰሰው ደም ይመሰክራል፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን የ 12 እና የ15 አመት ልጆቼ ስለአያታቸው በኩራት አንገታቸውን ቀና አድርገው ነው የሚያወሩት።

ECADF 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *