ዋናው ሰውዬ (አቶ መለስ) ሰሞኑን የደህንነትና የስለላ ኃላፊ በሞት ከተለየ (ከተወገደ) በኋላ ያንን ለሥልጣን መዋቅራቸው ምሰሶ የሆነውን ቦታ ለማንም አሳልፈው መስጠት እንደሌለባቸው አምነዋል። በተለይ ከቅርብ የትግል ጓዶቻቸው በተደጋጋሚ እየተሰነዘሩባቸው የሚመክቷቸው በሥልጣናቸው ሕልውና ላይ የሚቃጡ ሙከራዎች፣ በደህንነቱ ቢሮ በኩል ከመጣ መቋቋሙ ሊከብዳቸው እንደሚችልም ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ተገንዝበዋል። በዚያ ላይ የደህንነት ሹመኞችን እንዳይከዷቸው መለማመጡ፣ አንዳንዴም እሳቸው ከበድ ያለ ኦፕሬሽን እንዲካሄድ ፈልገው ቶሎ በመፈፀም ፈንታ “ይኼማ እንዴት ይሆናል” የሚሉ የሕግና የተገቢነት ጥያቄዎች መነሳታቸው ሲያበግናቸው ኖሯል።

ዋናው ሰውዬ ይህን ችግር ለመፍታት ለሁለት ሳምንታት ሙሉ ሲታገላቸው የከረመውን ሀሳብ አምጠው ወልደው መቋጫውን ስላገኙለት፣ የተጫጫናቸው የድካም ስሜት በአንዴ ሲለቃቸው ታወቃቸው። በሲጋራ ብዛት የጠቆረውን ከንፈራቸውን ፈልቀቅ፣ በጊዜ ዕጦት ጭፍርር ያለውን ጢማቸውን ገለጥ፣ አድርገው በበለዙ ጥርሶቻቸው ብቻቸውን ፈገግ አሉ። በሰሞኑ የቢሮ ውሏቸው፤ ሀሳባቸውን ለማቀጣጠል ያግዝ ይመስል በየ 30 ደቂቃዎቹ ሲያቦኑ የሰነበቱትን ሲጋራ፣ ለዕለቱ የመጨረሻቸው የሆነችዋን አንድ ፍሬ ኒያላ ከፓኳቸው አውጥተው በደስታ ስሜት እንደ ድል ችቦ ለኮሱ።

በደስታ ታጅበው ካሳለፉት ከስኬታማው ምሽታቸው በኋላ ወደ መኝታቸው ከማምራታቸው በፊት ስልካቸውን አነሱ። ከህወሓት አምስት፣ ከብአዴን ደግሞ ሶስት ቁልፍ ሰዎቻቸውን እና ሚስጥረኞቻቸውን መርጠው በጠዋት ጽ/ቤታቸው እንዲገኙ እንዲያደርጉ ለአቶ በረከት ጥብቅ መልዕክት አስተላለፉ። የተጠሩት ጓዶች ከአንድ ሳምንት በፊት ስለ ስብሰባው ርዕሰ ጉዳይ ፍንጭ በሚሰጣቸው መልኩ በሰውዬው ጽ/ቤት ለሌላ ጉዳይ በተገኙበት ወቅት ቀለል ያለ ገለፃ ተደርጎላቸው ነበር።

ሰውዬው በነጋታው ጠዋት ማልደው ከደረሱት ጓዶቻቸው ጋር ለምስጢራዊው ስብሰባ በጽ/ቤታቸው ተገኙ። ደስታቸውን ዋጥ ለማድረግ እየጣሩ ለመሆናቸው ሁኔታቸው እያሳበቀባቸው፣ በደህንነቱ ቢሮ አሰራር ዙሪያ አንድ ዕቅድ ስለመንደፋቸውና ሀሳባቸውን ለውይይት ለማቅረብ መሰናዳታቸውን ሲጋራቸውን የለኮሱበትን የክብሪት እንጨት ለማጥፋት እያወዛወዙ ገለፁ። ወዲያው ከወንበራቸው እመር ብለው ተነሱና…

“ጓዶች ባለፈው እንደተወያየነው የደህንነት ቢሮውን ሙሉ ኃላፊነት ለአንድ ሰው ብቻ አሳልፎ ማሸከም፣ በተደጋጋሚ እንዳየነው በተሰዉ ታጋይ ሰማዕታት ደም እጃችን የገባውን ሕገመንግሥታችንን እና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓታችንን አደጋ ላይ መጣል ነው። በመሆኑም ሕገመንግሥታዊ ሥርዓታችንን ከፀረ ሠላም ኃይሎች መከላከል የሚችል ብቃትና ልማታችንን ለማስቀጠል ማገዝ የሚችል አቅም ያለው፣ ከበላይ አመራር የሚሰጠውን አቅጣጫ ለመቀበል የማያንገራግር አንድ ብቁ ግለሰብ ማግኘቱ ቀላል እንዳልሆነ ግንዛቤ ወስደናል።

ስለዚህ እዚህ የምንገኘው ጓዶች የደህንነት መ/ቤቱን በምስጢር እና በጋራ እንድንመራው ዕቅድ ተነድፎ መጨረሱን ሳሳውቃችሁ ኩራት እየተሰማኝ ነው። አያችሁ ይኼን ቢሮ በዚህ መልኩ በቁጥጥራችን ስር ካዋልነው ከአሁን በኋላ 30 እና አርባ አመታት በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለንን መደላድል አመቻቸን ማለት ነው። ዋናው ነገር ጉዳዩን በተለመደው ኢሕአዴጋዊ ታላቅ ምስጢር ጠባቂነታችን ይዘን መቀጠል እንዳለብን አለመዘንጋቱ ላይ ነው።” አሉ ኮስተር ብለው።

ሰውዬው የዕቅዳቸውን አፈፃፀም ማብራራቱን ቀጠሉ። “ምን መሰላችሁ የምናደርገው… ከተሰዉ ከቀድሞ የትግል ጓዶቻችን መካከል የአንዱን ስም እንመርጥና የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ሹመት ለእዚያ ሰው መሰጠቱን እናፀድቃለን። በዚያ ሰው ስም የሚዘጋጅ ፊርማና ማኅተም ተጠቅመን የደህንነት ቢሮውን እኛው በጋራ እንመራዋለን ማለት ነው።” ብለው ገባችሁ? በሚል አተያይ ጓዶቻቸውን ተመለከቷቸው።

ንግግራቸውን ቀጠሉ “ለምሳሌ በብዙ ታጋዮች ዘንድ ይኑር ወይ ይሰዋ የማይታወቀውን የድሮ የትግል ጓዳችንና በትግል ወቅት ጥሩ የስለላ አመራር ተሰጥኦ የነበረውን የታጋይ ጌታቸው አሰፋን ስም መጠቀም እንችላለን። በዚያ ላይ “ጌታቸው አሰፋ” የሚባሉ ከአንድ በላይ ታጋዮች ስለነበሩ “ጌታቸው የቱ ነው?” የሚሉ ከሕዝቡም ሆነ ከአባሎቻችን ሳይቀር ለሚነሱ ጥያቄዎች ራሱን የቻለ አቅጣጫ ማሳቻ እንደሚሆንልን ግልፅ ነው።

“አቶ ጌታቸው አሰፋ” በእኔ ጠቋሚነትና ምልመላ ለመረጃና ደህንነት መ/ቤቱ ዋና ኃላፊነት መሾሙን በዜና እናስነግራለን። ቀጥለንም ስለ ጌታቸው የስለላ ብቃትና ጥንቁቅነት ያፈተለኩ የሚመስሉ የፈጠራ መረጃዎችን አልፎ አልፎ እየለቀቅን ሕዝቡን እናጥለቀልቀዋለን። ዋናው ነጥብ እዚህ ካለነው ውጭ ያሉ የድርጅታችን አመራሮች እንኳ ስለ “ጌታቸው አሰፋ” ትክክለኛ ማንነት በፍፁም፣ በምንም መንገድ ፍንጭ ማግኘት እንደሌለባቸው አለመዘንጋቱ ላይ ነው።

በመሆኑም የነገሩን ዱካ ለማጥፋት በየጊዜው የተለያዩ ዘዴዎችን ልንጠቀም እንይላለን። ለምሳሌ “ጌታቸው አሰፋ” የመራው ስብሰባ መሳተፋችንን ልናስወራ እንችላለን። በህወሐት ማዕከላዊ ኮሜቴ ውስጥም መመረጡን መረጃ ልንለቅ እንችላለን። ሁሉም ካድሬዎቻችንና አመራሮቻችን ከቢሮው ጋር እንጂ ከኃላፊው ጋር የግድ በአካል መገናኘት ስለማያስፈልጋቸው አለቃቸውን አለማየታቸው፣ ከብቃቱና ከጠንቃቃነቱ የመነጨ እንደሆነ ሊያሳምናቸው ይችላል” አሉና የተጋመሰችውን ሲጋራቸውን አንድ ዓይናቸውን ጨፈን አድርገው፤ በአንድ ትንፋሽ እስኪቂጧ ድረስ መጠው ሳቧትና መተርኮሻ ላይ ደምድመው አጠፏት።

ተሰብሳቢዎቹ ሁሉ በግራ መጋባት ስሜት ዐይናቸው ፈጠጠ፣ እርስ በርስ ተያዩ። ደንገርገር አላቸው። ብዙም ባልገባቸው ጉዳይ ከብአዴኖቹ አንዱ ጓድ ፈጠን ብለው ነጥብ ለማስቆጠር የሚረዳ ንግግር አደረጉ። “ይኼን ቦታ ከመለስ በቀር ሊመራው የሚችል ሰው አልተፈጠረም፣ ብዬ ገና ድ…ሮ ተናግሬ ነበር። ያንን ለማድረግም እሱ ካሰበበት መላ አያጣም ብዬ ለበረከት አውርቼዋለው። ይኸው ያልኩት ሁሉ ሲሆን እያየሁ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ።” አሉና ኩራታቸውን ገለፁ።

የብአዴኑ ዋና ሰው ወዲ ስምኦን ደግሞ ፌዝ በተሞላበት ፈገግታ ታጅበው አጨበጨቡ። በሴራ ብቃታቸው የተመሰከረላቸው የስምኦን ልጅ በዚያው ሰሞን ስለዕቅዱ ከሰውዬው ጋር በድብቅ እየተገናኙ ሁለት፣ ሶስቴ ገንቢ በሆነ መልኩ ተወያይተውም ነበር። ዛሬ ጉዳዩን ሰውዬው በብቸኝነት ይምሩት እንጂ የሴራውንም ዋና ክፍል አብረው አቡክተው አብረው ነበር የጋገሩት።

ዋናው ሰውዬ ገለፃቸውን በመቀጠል “በደህንነቱ መ/ቤት በኩል መፈፀም የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ሲገጥሙን፣ መወሰድ ስላለባቸው ርምጃዎችና ኦፕሬሽኖች እዚህ የምንገኘው ጓዶች በዴሞክራሲያዊ መንገድ በድምፅ ብልጫ እንወስናለን። በአስቸኳይ ጉዳዮች ላይ ደግሞ እኔ ውሳኔዎችን አሳልፋለሁ። ስለዚህ “ጌታቸው አሰፋ” የሚባለው ሰው በዚህ ሰአት በዚህች ጽ/ቤት የተገኘነው ነባር ታጋዮችና አመራሮች በአንድ ላይ ለራሳችን እና ለትግላችን የሰየምነው የቃል ኪዳናችን ሰነድ መጠሪያ ነው። ሁላችንም ጌታቸው አሰፋዎች ነን።” አሉና በስሱ ፈገግ አሉ።

በጥቅሉ ዋናውን የመረጃና ደህንነት ሥራውን የመምራት ሙሉ ኃላፊነቱን እሳቸው እንደሚወስዱና እንደሚመሩት አስገነዘቡ። ወዲያው ከባድ ፀጥታ ሰፈነ። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ዋናው ሰውዬ ሁላችንንም ዕኩል “ጌታቸው አሰፋዎች” ነን ቢሉም፣ እሳቸው የበለጠ “ጌታቸው አሰፋ” መሆናቸው እንደማይቀር ተሰብሳቢዎቹ ሁሉ ያውቁ ነበር።

በቢሮዋ ውስጥ ከፍርሃት በመነጨ የሰፈነው ፀጥታ፣ የተሰብሳቢዎቹን የልብ ምትና በስብ ከተጨናነቀው ሆድ ዕቃቸው የሚወጣውን የትንፋሻቸውን ሲርሲርታ አግንኖ ያስደምጥ ነበር። ከአንድ አስር ሰከንዶች ረጭታ በኋላ ጥያቄዎችና ሥጋቶች መዥጎድጎድ ጀመሩ። ዋናው ሰውዬ አንድ ሀሳብ ካነሱ ከማስፈፀም እንደማይመለሱ የሚያውቁ ጓዶቻቸው፣ ሀሳባቸውን ተቃርነው ጥርስ ከመግባት ይልቅ፣ ይበልጥ የሚጠነክሩባቸውን መላዎችና ያልታዩባቸው ክፍተቶች ካሉ ለማጎልበት የሚረዱ ሀሳቦችን ይሰነዝሩ ጀመር። የሁሉንም ተስፋ፣ ሥጋትና የማጎልበቻ ሀሳቦች ከተንሸራሸሩ በኋላ ዋናው ሰውዬ ማብራሪያቸውን ቀጠሉ።

“ሁሉም ሥራ በጸሐፊዋና በምክትል የቢሮው ኃላፊ በኩል እንዲሳለጥ ይደረጋል። ሆኖም ግን ጸሐፊዋም ሆኑ ምክትሉ የደህንነት ኃላፊ ከአለቃቸው “ጌታቸው አሰፋ” ጋር በአካል እንደማያገኙት ገና ወደ ቢሮው ሲመጡ ጀምሮ እንዲያውቁት ይደረጋል። አስፈላጊ የመልዕክት ልውውጦችን እኔ ወይም በረከት እየደወልን በፋክስና በስልክ እንመራለን፣ እናስፈፅማለን።

ሌላው ድምፅ ማጎርነንና መቀየር የሚችል መሳሪያ በቢሮ ስልኬ ላይ አስገጥሜ ጨርሻለሁ። ስለዚህ አንዳንዴ በስልክ ማናገር አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች እኔ ራሴ ጌታቸው አሰፋ መሆኔን ገልጬ ትዕዛዝ እሰጣለሁ። የእኔ የቢሮ ስልክ ቁጥሩ ስለማይወጣና ስለማይጠለፍ በዚህ በኩል ሥጋት አይገባንም። ድምፅ መቀየሪያው ማሽን አንዴ ቋሚ ኮድ ከተሰጠው በኋላ ምንም ዓይነት ሰው ከወዲህ ቢናገር ከወዲያ በኩል የሚያስደምጠው ድምፅ ሁሌም አንድ ዓይነት ነው። ስለዚህ እኔም ሆንኩኝ አዜብ በዚህ ቁጥር ብናወራ ለአድማጩ የሚደርሰው አንድ ዓይነት ድምፅ ነው።

ይህን ቴክኖሎጂ ከሰሞኑ ለበረከትም ቢሮው ውስጥ ይገጠምለታል። ከእኔ ጋር እየተነጋገርን አስፈላጊ በሆኑባቸው ጊዜያት በረከትም፣ ጌታቸው አሰፋነቱን ይጠቀምበታል ማለት ነው።” እያሉ ስለ ረቂቁ ሴራቸው ማብራራያቸውን ቀጠሉ። ሰውዬው ማብራሪያቸውን በሰከነ አነጋገርና በአፅዕኖት ቀጠሉ። “አንዳንዴ የመረጃ እና ደህንነት ኃላፊው በውጭም ይሁን በሀገር ውስጥ በአካል የግድ መገኘት በሚያስፈልግባቸው ቦታዎች አንድ ዘዴ መጠቀም እንደሚቻልም አስረዱ። ለምሳሌ በውጭ ሀገራት “አቶ ጌታቸው” መገኘት አለበት ተብሎ ከታመነ፣ ሚሽኑን ለሚወስደው የደህንነት ባለሙያ ፓስፖርትም ሆነ አስፈላጊ ሰነዶች በ”ጌታቸው አሰፋ” ስም ይዘጋጅለታል።

ያንን ኃላፊነት የሚወጣውን ሰው መምረጡና ማዘጋጀቱ የቅርብ አለቃው ስራ ይሆናል። ‘አለቃህን ሆነህ እዚህ ቦታ ትገኛለህ’ ተብሎ ሚሽን የሚሰጠው የስር የደህንነት ባለሙያ ትኩረቱ ኃላፊነቱን መወጣቱ ላይ እንጂ ለምን ብሎ አይጠይቅም። ሙያውም የታዘዘውን እንዲፈፅም ብቻ ነው የሚያዘው። በዚህ መንገድ አንድ የደህንነት ሰው በቢሮ ዕውቅናና ድጋፍ ሚሽን እስከተሰጠው ድረስ “ጌታቸው አሰፋ” ነኝ ካለ ማንም ሰው አይደለህም ብሎ ሊከራከር አይችልም።

ሌላው ሚሽኑን የሚወስዱ የደህንነት ሠራተኞች በምንም መልኩ በሚዲያ የሚተላለፍ ዝግጅት ላይ እንዲገኙ፣ ፎቶ እንዲነሱ፣ ምስላቸው በካሜራ እንዲቀረፁና ቃለ መጠይቅ ላይ እንዲሳተፉ አይደረግም። በዚህ ሁኔታ በአንድ ቀንና ሰአት ውስጥ ጌታቸው አሰፋ አዲሳባም፣ መቀሌም ሆነ ሳውዲ ዓረቢያ እንዲገኝ ማድረግ እንችላለን። ሰዎችም በአንድ ሰአት ጊዜ ውስጥ በተለያየ ቦታ ማየታቸውን እየተማማሉ እንዲከራከሩና ሰውዬውን ወደ መንፈስነት የተጠጋ ስለመሆኑ እንዲያወሩ ማድረግ እንችላለን። ሃሃሃ

የፖለቲካ ሥልጣን ዘላለማዊ አይደለም። አንድ ቀን ከቁጥጥራችን ውጭ ሆኖ ከእጃችን ሊወጣ ይችላል። ኢሕአዴግ ብዙ የጥፋት ኃይል የሆኑ ጠላቶች አሉት። በዚህም የተነሳ ከበድ እና ረቀቅ ያሉ ምርምራዎችንና የስለላ ስልቶችን መከተል ይጠበቅብናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ተቃዋሚዎችም ሆኑ የመብት ተሟጋች ነን ባይ የሆኑት ነጮቹ በወንጀል ድርጊት ሊጠይቁን መነሳሳታቸው አይቀርም።

አያችሁ የጠበቀ ነገር የገጠመን ጊዜ አቶ “ጌታቸው አሰፋ” ወዳልታወቀ ሀገር ኮበለለ ብለን እናስወራለን። አብረን እናፋልጋለን። በዚህም ለሕገመንግሥታችን መከበርና ለድርጅታችን ሕልውና ሲባል ለሚወሰዱ ርምጃዎች እንደ አመራር የሚጠይቀን አካል አይኖርም። ሁሉም ነገር ከጌታቸው አሰፋ መጥፋት ጋር ይቀበራል” ብለው ለአጭር እረፍት በፈጣን ርምጃ ወደ ውጭ አመሩ።

 By Samson Getachew T S (ይህ ጽሑፍ ልብወለድ ነው)

ግንቦት 19 ቀን፣ 1993 ዓ.ም…

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *