በኢትዮጵያ ከፖለቲካው ቀውስ በማያንስ መጠን የኢኮኖሚው መላሸቅ፣ የሥራአጥነትና ድህነት የሚያስከትሉት አደጋ አሳሳቢና አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ተጠቆመ። የለውጡ ኃይሎች ለውጡን በሚያደናቅፉ ላይ ፈጥነው እርምጃ አለመውሰዳቸው ስህተት መሆኑ ተነገረ።የጎልጉል ታማኝ የአሜሪካ ዲፕሎማቲክ ምንጭ እንዳሉት ኢትዮጵያን ከለውጡ በኋላ አላላውስ ያላት ችግር የኢኮኖሚው ጣጣ ነው።
ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሲቀነቀን የነበረው የኢኮኖሚ መርህ የተነሳ ዜጎች ለሥራአጥነት ተዳርገዋል፤ የሥራአጡ ቁጥርም ከሚገመተውና በይፋ ከሚነገረው እጅግ የበለጠ ነው። በአሁን ወቅት የመንጋ፣ ቡድን፣ ጥርቅም የሚባሉት አካሎች ይኸው ድህነቱ የፈጠራቸው ክፍሎች እንጂ ሌላ እንዳልሆኑ የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉት ዲፕሎማት አመልክተዋል። የመንደርና የጎጥ ፖለቲካውም የራሱን ጫና ማሳደሩን ዲፕሎማቱ አይክዱም።
ችግሩን ይባስ ያወሳሰበው ደግሞ ይህንን ኃይል ገንዘብ ያላቸው ክፍሎች እንዳሻቸው መጠቀም መቻላቸው ነው። የለውጡ ኃይሎች ወደ ሥልጣን እንደመጡ ወዲያውኑ ሊወስዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች ባለመውሰዳቸው “ፌዴራል መንግሥት አይነካንም፤ አያዘንም” የሚሉ ጡንቸኛ አካላት እንዲፈጠሩ አድርጓል።
