የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ በአቶ በረከት ስምዖንና በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ ያቀረባቸውን የቃል ምስክሮች በዛሬው ዕለት ማዳመጥ ጀምሯል።

ፍርድ ቤቱ ግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ዓቃቤ ህግ በአቶ በረከት ስምዖንና በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ አሉኝ ያላቸውን የቃል ምስክሮች ከግንቦት 21 ጀምሮ እንዲያሠማ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል። በተከሰሱባቸው የሙስና ጉዳዮች 13 የሰው ምስክሮች ቀርበው ዛሬ መደመጥ ጀምሯል፡፡

በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ የሚገኘው ተከሳሾቹ ከዚህ ቀደም በጠበቆቻቸው ላይ በሚደርሰው እንግልት በጠበቃ መከራከር አልቻልንም በሚል አቤቱታ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ያቀረቡትን አቤቱታ በመቀበልም ጠበቆችን ለይተው እንዲያሳውቁና ተገቢው ጥበቃ እንደሚደረግ ፍርድ ቤቱ ባለፈው በዋለው ችሎት ተዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

በዛሬው እለት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ለችሎቱ የህግ ጠበቃ ይዘው ቀርበዋል፡፡

ለቀረቡት የህግ ጠበቃም በሚያርፉበት ሆቴል፣ ደንበኞቻቸውን ለማግኘት ወደ ማረሚያ ቤት ሲጓዙና ከኤርፖርት ወደ ፍርድ ቤት ሲጓጓዙ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ ታዟል።

ተከሳሾቹ አሰራርን በማያመች ሁኔታ በመምራት ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል አራት ክስ ተመሰረቶባቸው ቆይቷል፡፡

በቀረቡባቸው ክሶችም ወንጀሉን አልፈፀምንም ሲሉ ሁለቱም ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃል መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

በተከሰሱባቸው የሙስና ወንጀሎች የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ 13 የሰው ምስከሮችን አቅርቦ ዛሬ ማሰማት ጀምሯል፡፡

ዛሬ ከጥዋት ችሎቱ የአንድ ሰው ምስክር መስማት የቻለ ሲሆን ከሰዓት፣ ነገ እና ከነገ ወዲያ ሁሉንም ምስክሮች ለመስማት ችሎቱ ቀጠሮ ይዟል፡፡

ከሁለቱ ተከሳሾች ጋር ተከሰው የቀረቡት አቶ ዳንኤል ግዛው ዛሬ ጠበቃቸው ባለመቅረቡ ለነገ ይዘው እንዲቀርቡና ምስክሮች መመስከር እንዲችሉ ተእዛዝ መስጠቱትን ከኢዜአ ያገኘነው ተጨማሪ መረጃ ያመለክታል፡፡

በናትናኤል ጥጋቡ –  (ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *