የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2012 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን አቅርበዋል፤ በረቂቅ በጀቱም 386 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር መሆኑን የተዘጋጀውን መግለጫ ሲያነቡ ገልጸዋል።

የተዘጋጀው የረቂቅ በጀት እቅድ ከ2011 ወይም አሁን ሊጠናቀቅ ካለው በጀት አመት አንጻር የ6 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወይንም የ1 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሬ አለው ።

ይህ የበጀት ብር ሲታቀድ የኢኮኖሚ፣ የገቢ እና የልማት ሁኔታዎች ታሳቢ ተደርገው መሆኑንም ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ከኢኮኖሚ አንጻር ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮችን ስናይ፥ 387 ቢሊየን ብር ረቂቅ በጀት የታያዘው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በ2012 በጀት ዓመት የተወሰነ ማንሰራራት በማሳየት ከ9 በመቶ በላይ ያድጋል የሚለው አንዱ ነው።

አሁን ላይ ባለ ሁለት አሃዝ የዋጋ ግሽበት ወደ አንድ አሃዝ ዝቅ ብሎ 9 ነጥብ 6 በመቶ ይሆናል በሚል፤ የሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት በጊዜው ዋጋ /nominal GDP/ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት/ጂዲፒ/ 19 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ይኖረዋል በሚልም ነው።

የገቢ እቃዎች የ10 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ይኖራቸዋል፤ እንዲሁም የብር የውጭ ምንዛሬ ከአሜሪካ ዶላር አንጻር በ6 በመቶ ዝቅ ይላል ወይንም አንድ የአሜሪካ ዶላር 29 ነጥብ 74 ብር ይሆናል የሚል ታሳቢም ይገኝበታል።

ከታክስና ታክስ ነክ ካልሆኑ ገቢዎች አንጻርም ረቂቅ በጀቱ ታሳቢ ያደረጋቸው ጉዳዮች አሉ፤ ታክስ ነክ ከሆኑት አንጻር የ2012 የኢኮኖሚ እድገት በጊዜው ዋጋ ወይንም ኖሚናል ጂዲፒ ሲለካ 19 ነጥብ 7 በመቶ ያድጋል ተብሎ ስለሚገመት ይህ የኢኮኖሚ እድገት የሚሰበሰበውን ግብር ያሳድገዋል፤ እንዲሁም የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ኤክሳይዝና የቀረጥና ታክስ ማበረታቻ ህጎች የሚሻሻሉ በመሆኑ እነዚህ በገቢ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።

ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚገኙ ትርፎች፣ ከመንግስት እቃ ሽያጭና አገልግሎቶች እንዲሁም የውጭ ብድርና እርዳታ ታክስ ነክ ካልሆኑት ገቢዎች ውስጥ ታሳቢ ተደርገዋል።

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

እንግዲህ ከ387 ቢሊየን ብር ረቂቅ በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 109 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር፣ ለካፒታል 130 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር እና ለክልል መንግስታት ድጋፍ 140 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚውል ይሆናል።

የካፒታል በጀት ወጪ አሸፋፈኑ ከሀገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ገቢ 94 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ቀሪው ከውጭ ሀገር የሚገኝ ብድርና እርዳታ ሌሎች ገቢዎች የሚገኝ ሲሆን፥ ቅድሚያ ለተሰጣቸው ትምህርት፣ ጤና፣ መንገድ፣ ግብርና እና የከተማ ልማት ወጪዎች ይሆናል።

ከመደበኛ ወጪው 109 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ውስጥ 34 በመቶው የደሞዝ አበልና ልዩ ልዩ ክፍያዎች፣ ቀሪው 66 በመቶ ለብድር ክፍያ፣ ለልዩ ልዩ ወጪዎችና ለሌሎች ክፍያዎች የሚውል ነው።

387 ቢሊየን ብር ለመንግስት 2012 በጀት አመት ወጪ ሲታቀድ የመንግስት ገቢ ደግሞ በተመሳሳይ 289 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ይሆናል ተብሎ ነው የታሰበው።

ይህ የሀገር ውስጥ ገቢን እና የውጭ እርዳታን ጨምሮ ነው። ስለዚህ የ97 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የበጀት ጉድለት አለ ማለት ነው።

ይህን የበጀት ጉድለት ለመሙላት በቀጥታ የበጀት ድጋፍና በፕሮጀክቶች ብድር 40 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር እንዲሁም፥ ከሀገር ውስጥ ብድር ደግሞ 56 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለማግኘት ታስቧል ።

ስለዚህም የበጀት ጉድለቱ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ምርት አንጻር 3 በመቶ ነው። ከዚህ ውስጥ የሀገር ውስጥ ብድር ድርሻ ደግሞ 1 ነጥብ 8 በመቶ ነው።

ይህም ተግባራዊ እየሆነ ካለው የግንዘብ ፖሊሲ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ በመሆኑ በዋጋ ንረት ላይ ተጸእኖ አያስከትልም ተብሏል።

ከዚህ ውጭ ግን ሊሰበሰብ የታሰበው የታክስ ገቢ ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ተነስቷል። በዚህ አመት 211 ቢሊየን ብር ገቢ ይሰበሰባል ተብሎ ነበር። ነገር ግን በ10 ወራት ውስጥ የታየው ይህ እንደሚሰበሰብ አያሳይም።

Related stories   Egypt-Sudan alliance shifting in row with Ethiopia over Nile dam

ከግቡ ለመድረስ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 68 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ከባድ መሆኑ ስለታመነበት ለ2012 በጀት ስጋትም ይሄው የታክስ ጉዳይ ነው።

ከምክር ቤቱ አባላት ለገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ሰጥተውባቸዋል።

ለበጀት ጭማሬ ምጣኔው ካለፈው አመት አንጻር ለምን ቀነሰ የሚለው ይገኝበታል። ለዚህ ሚኒስትሩ ምላሽ ሲሰጡ “የበጀት ጭማሬ ምጣኔው የቀነሰው ከገቢያችን ጋር ለማቀራረብና የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ነው” ብለዋል ።

በሌላ በኩል “ለክልሎች የበጀት ድጋፍ ከፍተኛ ገንዘብ እየተደረገ ነው። ነገር ግን አሁን ላይ በተለይ በክልሎች በኩል ሚሊሻና ልዩ ሀይልን የማሰልጠን ከፍተኛ አዝማሚያ ይታያል፤ ታዲያ ለክልሎች የሚመደበው በጀት ለታለመለት የልማት አላማ እየዋለ ለመሆኑ ምን መከታተያ ዘዴ አለ?” የሚል ጥያቄ ተነስቶ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ “ይሄንን ጉዳይ መሬት ላይ ወርዶ ማየት ያስፈልጋል፤ የሚባለው ከሆነም ከክልሎቹ ጋር ተቀራርቦ መስራት ያስፈልጋል” የሚል ነበር ምላሻቸው ።

ሌላው በሰፊው ጥያቄ የተነሳበት ጉዳይ የካፒታል በጀቱ ፍትሀዊነት ይጎድለዋል የሚለው ሲሆን፥ ይህ በተለይ የተነሳው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ካወጣው ቀመር አንጻር ነው።

ሚኒስትሩ ለዚህ ምላሽ ሲሰጡ፥ “ይህ ቀመር ከመተግበሩ በፊት ለአንድ አመት ጊዜ አለ፤ በሌላ በኩል መሰረተ ልማቶች በተለያዩ ስፍራዎች ሲሰሩ ቦታዎቹ ላይ የሚኖሩ የልማት ስራዎችም ከግምት ውስጥ እንደሚገቡም መታወቅ አለበት” ብለዋል።

“በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢኮኖሚ ሪፎርም ጸድቆ ተግባራዊ ይሆናልተብሏል፤ ይህን ሪፎርም ምክር ቤቱ ሊያውቀው ይገባል፤ ምንድነው ይህ ሪፎርም?” ተብለው ተጠይቀዋል ሚኒስትሩ አቶ አህመድ።

እሳቸውም ሪፎርሙ ለኢኮኖሚው አድገት ጥሩ መሆኑን አንስተው በቀርቡ ይፋ ሆኖ ይገለጻል የሚል ምላሽ ነው ለምክር ቤቱ የሰጡት።

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

ከበጀት ጉዳዩ በፊት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላለፉት አመታት የመጣበት ሁኔታ ሰፊ ማብራሪ ተሰጥቶበታል።

የወጪ ንግድ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑ ተነስቷል። በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ ተቀማጭ ላይ ችግር እንዳይመጣ ገቢ እቃ እንዲቀንስ ተደርጓል ሆኖም የሚገቡ እቃዎች መጠን ቢቀንስም የእቃዎቹ ዋጋ ግን በመጨመሩ ተጽእኖው አሳርፏል።

ባለፉት አመታት የዋጋ ግሽበት በአማካይ 13 በመቶ ሆኖ ቆይቷል፤ ይህ ማለት በነጠላ አሀዝ የማቆየቱ ጉዳይ አልተሳካም ማለት ነው። በዚህ አመትም ግሽበቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጥሏል ። ቀድሞ የዋጋ ግሽበት መነሻው ምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ ነበር፤ በዚህ አመት ግን ምግብ ነክ ባልሆኑት እቃዎችም የዋጋ መናር መከሰቱ ተነስቷል።

የውጭ ምንዛሬ አጥረት፣ የገበያ መዛባትና የምርታማነት ችግር ለዚህ በምክንያትት ተጠቅሷል። እንዲሁም የገንዘብ አቅርቦትን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በጊዜው የገበያ ዋጋ እድገት ተመጣጣኝ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም ባለፈው አመት መጠነኛ ብልጫ በማሳየቱ በወቅቱ ለታየው የዋጋ ንረት መጨመር አስተዋጽኦ ሊኖር እንደሚችል ይታመናል ተብሏል። ይህ በመንግስት በኩል ሲታመን ብዙ ጊዜ አይሰማም ነበር።

እነዚህን ችግሮች የማስተካከል እርምጃዎች በሰፊው እንደሚወሰዱም ተነስቷል። ሌላው የተነሳው የብድር ጫና ጉዳይ ነው፤ይሄ የወጪ ንግድ ከመዳከሙ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው በማብራሪያቸው ያነሱት።

ከዚህ ቀደም እንደተባለው አሁን ላይ የኮሜርሻል ብድሮች እንዲቆሙ ተደርጓል ። ከአበዳሪዎች ጋር ብዙ የመክፈያ ጊዜን ለማራዘምና የንግድ ብድሮችን ወለዱ ዝቅ ወዳለና መክፈያው ወደረዘመ ጊዜ ለማስቀየር ድርድር ተካሂዷል። ይህም በመሳካቱ ኢትዮጵያ ቢያንስ ለሚቀጥሉት አምስት አመታት የብድር ጫና አይኖርባትም ብለዋል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ።

Vኤፍ ቢ ሲ)

በካሳዬ ወለዴ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *