በአማራ ክልል ከመንግስት የፀጥታ ሀይል ውጭ ፀጥታ ለማስከበር ማንም መንቀሳቀስ እንደሌለበት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአዴፓ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ። ከዛሬ ጀምሮ የሚንቀሳቀስ ካለም የክልሉ መንግስት የፀጥታ ሀይል እርምጃ ይወስዳል!

በባህር ዳር ከተማ በክልሉ የዴሞክራሲ ምህዳር መስፋት እና በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ አተኩሮ ሲካሄድ የቆየው ውይይት ተጠናቋል።

በዚህ ውይይት ተሳታፊዎች በጥፋተኞች ላይ የሚወሰድ እርምጃ ባለመኖሩ የህግ የበላይነት፣ ሰላምና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንቅፋት መሆኑን አንስተዋል።

ይህም በሀገር አቀፍና በክልሉ ለዜጎች መፈናቀልና ሞት መፈጠር ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። እንዲሁም የወጣቶች የስራ አጥነት፣ መሰረታዊ የሆኑ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ልማቶች የክልሉ ችግሮች መሆናቸውን ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር የክልሉን የዴሞክራሲ ምህዳር ለማስፋት፣ ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር ከመንግስት የፀጥታ ሀይል ውጭ ማንም መንቀሳቀስ እንደሌለበት ተናግረዋል።

ከዛሬ ጀምሮ የሚንቀሳቀስ ካለም የክልሉ መንግስት የፀጥታ ሀይል እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በቀጣይ ችግሮች እንዳይፈጠሩም የክልሉ መንግስት ከፀጥታ ሀይልና ከህዝቡ ጋር እስከታች በመውረድ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ የወጣቶችን የስራ እድል ለመፍጠር ከመንግስት፣ ከባለሀብቱ፣ ምሁራን እና ከህብረተሰቡ የተውጣጣ ኮሚቴ እንደተዋቀረ ተነግሯል።

መሰረታዊ የሆኑ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታትም ክልሉን የኢንቨስትመንት እና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ ለውጡ የደረሰበት ደረጃ፣ ችግሮቹና መፍትሄዎቹ በሚል በክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሀላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ እና በዶክተር ዮናስ ተስፋ የህግ የበላይነትን ማስከበር የአማራ ህዝብ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማረጋገጥ ያለው ወሳኝ ሚና በሚል የመነሻ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ – (ኤፍ ቢ ሲ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *