አመራሩ ለፀጥታ ችግሩ ዋና ተጠያቂ መሆኑ መረጋገጡን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ ተናገሩ!!

ሕዝቡ አንድ በመሆኑ ከሚገኘው የላቀ ጠቀሜታ ይልቅ የሕዝብ ግጭቶችን የሚያባብሱ ገመዶችን ከልክ በላይ በመወጠር ጀግና ሆኖ ለመታየት የሚደረጉ መፍጨርጨሮች በአመራሩ ውስጥ መስተዋላቸውም ተገልጿል፡፡

ከሳምንታት በፊት በምሥራቅ አማራ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች ተከስተው ነበር፡፡ በግጭቶቹም የሰው ሕይወት አልፏል፣ ንብረት ወድሟል፤ ለዘመናት አብረውና ተደጋግፈው የኖሩ ሕዝቦችም በጥርጣሬ እና በስጋት እንዲተያዩ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡ የችግሮቹን መሠረታዊ ምክንያቶች ለመለየት፣ የሕዝቡን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እና ችግር ፈጣሪዎችን በመለየት ተጠያቂ ለማድረግ የሚያግዝ ምክክር አጣዬ ከተማ ላይ ተካሂዷል፡፡ በምክክር መድረኩ ከደቡብ ወሎ እና ከሰሜን ሸዋ ዞኖች፣ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የተውጣጡ የዘጠኝ ወረዳዎች አመራሮች፣ የዞን፣ የክልል እና የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ፣ የፀጥታ ችግሮቹን ሂደት እና አሁን ያለበትን ደረጃ በመተንተን ለምክክር መድረኩ የመነሻ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ‹‹የፀጥታ ችግር የተፈጠረባቸው አካባቢዎች የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአርጎባና የአፋር ሕዝቦች ስብጥር የሚስተዋልባቸው ናቸው›› ያሉት አቶ ምግባሩ በአካባቢው ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ምንነትና አሰላለፍም ለችግሩ የየራሳቸው ድርሻ እንደነበራቸው አመልክተዋል፡፡ በተለይም ክልሉን የሚመራው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ክትትልና ድጋፍ ውስንነት እንደነበረበትም ነው የተናገሩት፡፡

ተመሳሳይ ምክክሮች የፀጥታ ችግር በነበረባቸው ሌሎች አካባቢዎችም ቀጥለዋል፡፡ አመራሮች የችግሮቹን መንስኤዎች ገምግመውና አጥርተው የፀጥታ ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ማድረግ እና ችግር ፈጣሪ አካላትን በማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ለሕግ ማቅረብ የውይይቶቹ ዋነኛ ዓላማ መሆኑንም አቶ ምግባሩ አስረድተዋል፡፡
በየደረጃው ያለው አመራር ከግጭቱ ጀርባ ድብቅ አጀንዳ ያላቸውን አካላት በዝምታ በማለፍ እና ተባባሪ በመሆን የፀጥታ ችግሩ ዋና ተጠያቂ መሆኑን በግምገማ ለማረጋገጥ እንደተቻለም አቶ ምግባሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከአመራሩ ውስጥ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል የማይፈልጉ አካላት አሉ›› ያሉት አቶ ምግባሩ ‹‹ሕዝቡ አንድ በመሆኑ ከሚገኘው የላቀ ጠቀሜታ ይልቅ የሕዝብ ግጭቶችን የሚያባብሱ ገመዶችን ከልክ በላይ በመወጠር ጀግና ሆኖ ለመታየት የሚደረጉ መፍጨርጨሮች በአመራሩ ውስጥ ተስተውለዋል›› ነው ያሉት፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝቡን ዋጋ እያስከፈለ መሆኑ ጠቁመዋል፡፡

Related stories   የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች በኢህአዴግ ጉባኤ አጀንዳ ሆነው አቋም ይወሰድባቸዋል፤ ወልቃይት፣ ራያ፣አፋር፣ ሲዳማ...

በግጭቱ የተለያዩ እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ከዚያም ከዚህም በማሠራጨት ሕዝቡ ከመጠን በላይ መረጃዎች እንዲምታቱበት እና በዚህም አንዱ ሌላውን በጥርጣሪ እንዲያይ መደረጉን ነው አቶ ምግባሩ የተናገሩት፡፡ የምክክር መድረኩ በየደረጃው ያለው አመራር ራሱን እንዲገመግም ማድረጉንና በቀጣይም በአጭር ጊዜ ውስጥ በየደረጃው ከሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል ጋር ውይይት እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

ሕዝቡ በመደራጀት፣ መረጃ በመስጠት እና ለፀጥታ መዋቅሩ በመተባበር በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ የድርሻውን እንዲወጣም አቶ ምግባሩ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከአጣየ

(አብመድ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *