በአማራ ክልል የታሰበበት የመፈንቅለ መንግስት መሞከሩን ተከትሎ ለአራት ሰዓታት ስርጭቱን አቋርጦ የነብረው የአማራ ክልል ሚዲያ ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን እንደመሩ አዲፓን ጠቅሶ ይፋ አድርጓል። ዶክተር አምባቸው ህይወታቸው ማለፉም እየተነገረ ነው።

ተደረገ የተባለው የመፈንቅለ መንግስት የአዴፓ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አገር ውስጥ በሌሉበት ሁኔታ አጋጣሚ ጠብቆ መከናወኑ ጉዳዩን አነጋጋሪ አድርጎታል። መንግስት ታቅዶና በተደራጁ ሃይሎች የተፈጸመ ነው ሲል ለተናገረው ማጠናከሪያ ሆኖ ተገኝቷል።

ከሁሉም በላይ በየክልሉ ያሉ የጸጥታ ሃይሎች የህግ መተላለፍን፣ ህዝብ እየወተወተ ያለውን የጸጥታ ማስከበር ስራ እንዲሰሩ በኢህአዴግ ደረጃ የተወሰነውን ተግባራዊ ለማድረግ በተወሰነ ውሳኔ አጠቃላይ አለመግባባት እንዳለ ይሰማ ነበር። ጀነራል አሳምነው ጽጌ በተደጋጋሚ የሚሰጡት መግለጫና የክልሉን ሰላም የማስከበር አቅማቸው አነስተኛ በመሆኑ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ አስቀድሞ በተያዘው እቅድ መሰረት ተገምግመው ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ አቋም መያዙን የዛጎል ምንጮች ይናገራሉ።

ወሳኔው ምን ሊሆን እንደሚችል መረጃ ያላቸው ጀነራል አሳምነው ጽጌ አስቀድመው ልዩ ሃይል አዘጋጅተው ወደ ስብሰባ እንደገቡና በግምገማው አለመግባባት ላይ ሲደረስ እሳቸው የሚያዙት ሰራዊት ገብቶ እርምጃ እንዲወስድ ሲያዙ በተነሳ አለመግባባት ሽጉጥ መታኮስ ተጀመረ። ዶክተር አምባቸው ክፉኛ ተጎድተው ወደ ሃኪም ተወስደዋል። ” ባህር ዳር ቀበሌ ፲፫ አሳምነውን ለመውሰድ ውጊያ ተጀምሯል። ይህንን ሰው መክቶ መታደግ የ አማራው እጣ ፈንታ ነው።ይጥፉ ወይስ እንጥፋ የሚለው ጥያቄ ዛሬም ህያው ነው” ሲል በፊስ ቡክ ገጹ ያሰፈረው ሄኖክ የሺ ጥላ መረጃ እንዳለው ጠቅሶ ዶክተር አምባቸው መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።

የአማራ ክልል በአስመሳይ ተቆርቁሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቂያ አስቀምጦ ወደ ተግባር ለመሸጋገር በተለያዩ መድረኮች የህዝብ ይሁንታ ያገኘው የዶክተር አምባቸው መንግስት፣ በቀናት ውስጥ ክልሉን የሚያተራምሱ ወገኖች ላይ እርማጃ ለመውሰድ ዝግጅቱን ባጠናቀቀበት ወቅት መፈንቅለ መንግስት መካሄዱ ጉዳዩ ከድርጅትም በላይ እንደሆነ በርካቶች አስተያየት እየሰጡ ነው።

በርካታ ሰራዊት እያሰለጠኑ የክልሉን ጸጥታ ማስከበር የተሳናቸው የክልሉ ጸጥታ ሃላፊ ከእስር ለቆ የሾማቸውን ሃይል በጠመንጃ ለመገልበጥ መሞከራቸው ዜናውን ለሰሙ ሁሉ መርዶ ሆኗል።

የፌደራል የጸጥታ ሃይላት በህብረት በሰዓት ጊዜ ውስጥ የተቆጣጠረው ኩዴታ መጨረሻው ወዴት እንደሚያመራ ባይታወቅም፣ በርካታ የድርጊቱ ተባባሪዎች መያዛቸው ታውቋል። የተገፈፈው ማዕረጋቸው የተመለሰላቸው አሳምነው ጽጌን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።

የእነ በረከት ስምዖንን ጉዳይ የያዙት አቃቤ ህግ ምግባሩ ከበደና አቶ አዘዘ ዋሴ በጸና መቁሰላቸውን የቅርብ ምንጭ በመጥቀስ የተለያዩ ምንጮች ይገልጻሉ። 

ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ላይ የተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት የሚፃረር፣ የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ለረጅም ጊዜ የታገሉለትን ሰላምና መረጋጋት ለመንጠቅ የተደራጀ በመሆኑ የፌደራል መንግሥት ሙሉ በሙሉ ያወግዘዋል።

የፌደራል መንግሥት የጸጥታ መዋቅር የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር አውሎ በፈጸሙት አካላት ላይ ተገቢውን ርምጃ እንዲወስድ ትእዛዝ ተቀብሎ ተፈጻሚ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ ጥቃት በመንግሥት መዋቅር ላይ ብቻ ሳይሆን በአማራ ሕዝብ ላይ የተቃጣ መሆኑን በመገንዘብ የክልሉ ሕዝብ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅና ተረጋግቶ ሁኔታዎችን እንዲመለከት ጥሪ ቀርቧል።

ይህን ሕገ ወጥ ሙከራ ክልሉ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ክልልና መላው ኢትዮጵያዊ ሊያወግዘው የሚገባ ሲሆን የፌደራል መንግሥት የታጠቁ ቡድኖችን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ የመቀልበስ፣ የመግታትና በቁጥጥር ሥር የማዋል ሙሉ ዐቅም ያለው መሆኑን ያረጋግጣል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   "ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሊያጠፏት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *