የአማራ ክልል የጸጥታና የሰላም ሃላፊ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ባህር ዳር ዘንዘልማ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የጸጥታ ሃይል በወሰደባቸው እርምጃ መገደላቸውን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ። ጀነራሉ የተከሰሱበትን የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ከማድረጋቸው በፊት የጸጥታ አካላትን በየቢሯቸው አስረው እንደነበርም ታውቋል። መንግስት በምህረት ወደ አገር ቤት ያስገባቸው፣ በበረሃ ሲንከራተቱ የነበሩ፣ ከእስር የተፈቱ ሴል መስርተው ውስጥ ውስጡን ለውጡን ሲቦረቡሩ መቆየታቸው ተጠቁሟል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አንዳሻው ጣሰው በሰጡት መግለጫ የሴራው ዋና አቀነባባሪ የተባሉት ጄነራል አሳምነው በሰዓታት እንደሚያዙ በገለጹ በደቂቃዎች ውስጥ የክልሉ ፖሊስ እንዳለው ጄነራሉ ባህር ዳር አካባቢ ዘንዘልማ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በጸጥታ ሃይሎች መመታታቸውን ይፋ አድርጓል።

ኮሚሽነሩ እንዳሉት መንግስት በይቅርታ፣ በምህረት፣ በመደመር ስሌት ያቀፋቸው ከእስር የተፈቱ፣ በበረሃ በትግል ስም ሲንከራተቱ የነበሩ፣ ጠላት የነበሩ የተመቻቸላቸውን መልካም አጋጣሚ ለክፉ አላማ ተጠቅመውበታል። በከፍተኛ የጸጥታና የድህንነት ሃላፊነት ተመድበው ሲሰሩ  በህቡዕ የሚሰሩ ሴሎችን ፈልፍለው ለውጡን ሲቦጠብጡ ነበር። ለውጡን ለማሰናቀል ሲሰሩ ነበር።

ኮኒሽነሩ ቃል በቃል ባይናገሩም በረሃ ለበረሃ ሲነከራተቱ የነበሩና በምህረት ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የተደረጉ ያሉዋቸው በተለይም በአማራ ክልል ስርዓት አልበኝነትን በማንገስ፣ አንዳንዴም በመሳሪያ የተደገፈ እንቅስቃሴ በማድርገና ከተማዋን በማወክ ህዝቡን ስጋት ላይ የታሉትን ወገኖች እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

በጠቅላይ ኤታምዦር ሹም ሰዓረ መኮንን በመኖሪያ ቤታቸው በባህር ዳር የተሞከረው ቀውስ በቁጥጥር ስር እንዲውል አመራር እየሰጡ ባለበት ሁኔታ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ አጥፍቶ እንዲጠፋ በተመደበ የግል ጠባቂያቸው መገደላቸውን ያወሱት ኮሚሽነሩ ” አጥፍቶ ጠፊ መቅጠር እቅዱ ሰፊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው” ብለዋል። በርካታ መረጃዎች መገኘታቸውንም አመላክተዋል።

በአዲስ አበባና በባህርዳር ከፍተኛ አመራሮች ያሉበት የምርመራ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የምርመራ ስራ እየተሰራ መሆኑንን ኮሚሽነሩ አመልክተዋል። እጅግ ጥቂት የሚባሉ ሲቀሩ በርካታ የሴራው ተሳታፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል። 

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የአሜሪካ ሴናተሮች የኢትዮጵያ ምርጫ እንዲራዘም ያቀረቡት ጥሪ ብልህነት የጎደለው እጅግ አደገኛ ነው - ሎረንስ ፍሪማን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *