የቡራዩ ከተማ ሰላምና  የልማት  ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ነዋሪዎች ገለጹ። በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ ከተማ ዛሬ የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

ነዋሪዎቹ በኮንፈረንሱ ላይ እንደገለጹት፤ መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ አለበት።

በውይይቱም ላይ የተለያዩ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈውበታል።

ተሳታፊዎቹ የከተማዋን ብሎም የክልሉን ሰላም በማስጠበቅና በልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

”ሰላም ከሌለ ምንም ነገር መስራት አይቻልም፣ ወጥተው መግባት፣በልማት ላይ መሳተፍ ብሎም ሰርቶ ማደር አይቻልም” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ህዝቡ በከፈለው መስዕዋትነት የተገኘውን ለውጥ ወደ ኋላ ለመመለስ የሚጥሩ ኃይሎችን እንደሚታገሉም ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ “ሸኔ ኦነግ” ነን በማለት በሰፋት የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ አስፈላጊውን ርምጃ በመውሰድ መንግስት ህግን የማስከበር ተግባሩን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል አመራሮችና በመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ላይ የተፈጸመ ግድያም እንዳሳዘናቸው በመግለጽ ድርጊቱን አውግዘዋል።

መንግስት የህግ የበላይነትን ለሚወስደው ርምጃ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉና የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በሰላም በአብሮነት የመኖር ባህሉንና ትስስሩን የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥልና በህዝቦች መካከል ልዩነት የሚፈጥሩትን እንደሚታገሉም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

የቡራዩ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰለሞን ፈዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የከተማ ነዋሪ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ከመንግስት ጋር እየሰራ ያለውን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።

”መንግስትም የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እየሰራ ይገኛል፣የህዝቡን የልማት ጥያቄም ለመፍታት ላይ ነው” ብለዋል።

በከተማው የጸጥታ ችግር እንዳይከስት ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት የፍተሻና የጸጥታ ሁኔታ የበለጠ እንዲጠናከር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ከውይይቱ በኋላ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ባለ 6 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ በመላ ኦሮሚያ አካባቢዎች መካሄዱን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የያዘውን አቋም እንደግፋለን… በባሌ ዞን የሕብረተሰብ ክፍሎች

መንግስት የአገሪቱን የጸጥታ ችግሮች በመፍታት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የያዘውን አቋም እንደሚደግፉ የባሌ ዞን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። የዞኑ የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ዛሬ በባሌ ሮቤ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት መንግስት በሀገሪቱ የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የጀመረውን እንቅስቃሴ ይደግፋሉ፡፡

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል የጎባ ከተማ ተወካይ ሼህ ኡመር ሉጎ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋቱና ሌሎች የማሻሻያ ሥራዎችን በመስራቱ ሊበረታታ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ይሁንና የመንግስትን ሆደሰፊነት ወደ ጎን በመተው ስልጣንን ከአግባብ ውጭ ለማግኘት ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን በሚያራምዱ አካላት ላይ መንግስት እየወሰደ ያለው ህጋዊ እርምጃ በቂ እንዳልሆነም ገልጸዋል።

እንደ ሼህ ኡመር ገለጻ መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ወደ ጠንካራ እርምጃ መግባት መጀመሩ ወቅታዊና የሚደግፉት ተግባር ነው።

የአገሪቱን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በመንግስት በኩል የተያዘው አቋም እንዳስደሰታቸው የተናገሩት ደግሞ የጎሮ ወረዳ ተወካዩ አቶ አህመድ ሙክታር ናቸው፡፡

በተለይ ሕዝቡ ከስጋት ነፃ ሆኖ እንዲኖርና ህገወጥነት እንዲቆም መንግስት ጠንካራ የፀጥታ አደረጃጀት እንዲገነባ ጠይቀዋል፡፡

አቶ አህመድ እንዳሉት የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በመንግስት እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በልበሙሉነት የሚደግፉትና የሚያደንቁት ተግባር ነው።

በአካባቢያቸው የሕግ የበላይነትን በማስከበር ወንጀለኞችን ከማጋለጥ ጀምሮ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ የጊኒር ወረዳ ተወካይ ወይዘሮ ፈጡማ አብደላ ናቸው፡፡

ኮንፈረንሱን የመሩት የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሀጂ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ህገወጥ ድርጊቶችን በማውገዝ እና በማስቆም መንግስት የህግ የበላይነት እንዲከበር እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

አስተዳዳሪው እንዳሉት፣ ኮንፈረንሱ ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ በተለያዩ አካላት የሚደረጉ የጥፋት ሙከራዎችን ለማጋለጥና ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ አለው፡፡

በተጨማሪም ለውጡ በስኬት እንዲቀጥል የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስና በየቦታው እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በህብረተሰቡ ድጋፍ መከላከል ሌላው የኮንፈረንሱ ዓላማ መሆኑንም ነው አቶ ኢብራሒም ያስረዱት፡፡

ኮንፈረንሱ በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር በኩል ያገጠሙ ፈተናዎችና ቀጣይ ስራዎች ላይ ያተኮረ ባለ ሰበት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡

ለአንድ ቀን በተካሄደው የሰላም ኮንፍረንሱ ላይ ከዞኑ 18 ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፏል፡

ENA

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *