መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ
በሚል ርዕስ መምህር ታዬ ቦጋለ ለጻፉት መጽሐፍ
በተዘጋጀ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት የቀረበ አስተያየት
ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 
አዲስ አበባ (ራስ ሆቴል)
ወርቅዓለማሁ ንጋቱ

ታሪክን ከነስህተቶቹና ስኬቶቹ በመቀበል ማወቅና መማር የሚያስፈልገው፣ለዛሬ ስምረትና ለነገም ተስፋ ያስቀመጠው ፣መጪውን ጊዜ የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል ኃይል፣ ለዛሬ ማንነትና ለነገ ብሩኅ ግንኙነት የሚያስቀረው በረከት ስላለው ነው፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ ሁኔታ ከታሪካችን ጋር ተያይዞ ባለው መረዳት የተለያዩ ጽንፎች የመኖራቸው እውነታ ዘመናችንን ዕጅ ለዕጅ በመያያዝ በሠላም፣ በፍቅርና በአንድነት ከመምራት ይልቅ በጥላቻ፣ በንትርክ ፣ በጥርጣሬ፣በመቆሳሰልና በመገዳደል መቀጠሉ፣ውጤቱ ተስፋ አስቆራጭ መራራ የድህነት ጽዋን እንድንጎነጭ አስገድዷል፡፡ ትናንትን መድገም ወይም የጊዜን ወደፊትነት ሕግ ሽረን ፣ምንጠላውንም ሆነ ምንወደውን ልንደግመው ባይቻልም፣ ጥቂቶች ዛሬን በትናንት ሂሣብ ለማወዳደቅ ብዙሃኑን ፍዳ እያበሉ የሚገኝበት አሳዛኝና አሳፋሪ ምዕራፍ፣ የሁላችንም ኢትዮጵውያን የዘወትር ዐቢይ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ታሪክ ትናንት በብዙ ትውልዶች ውጣ ውረድ ያለፈ ረዥም ማህበራዊና ተፈጥሯዊ ሂደት ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ነው ፣ወደ ትናንትና ሊቀለበስ አይችልም፡፡ ትናንትም ያለፈና ስለነገም የትናንት ትውልዶች ተስፋ የማያደርጉበት እውነታ ነው ታሪክ፡፡ ስለ ታሪክ ያለንን የምዘና ፋይዳ በዚህ መነጽር ከተመለከትን አንዱ በክብርና በኩራት ሌላው ደግሞ በቁጭትና በጸጸት የሚያስቡትና የሚገልጹት የሰው ልጆች ሕይወት ዘርፍ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ነባር ሕዝቦች የብሄራቸው ወይም ጎሳ መሪያቸው ማንም ይሁን ማን ፣ለዘመናት እርስ በርስ ያስተሳሰራቸው የፈጠሩት ባህል፣ልማድ፣ ያቆራኛቸው ጥብቅና ረቂቅ ሥነልቦናዊ ትስስር አለ፡፡ አብረው እየሰሩ፣ እየነገዱ፣ እየተዋጉ፣ እየተጋቡ በሺ የሚቆጠሩ ዘመናት በማኅበራዊ መስተጋብር ተቀላቅለው ጉራጌነታቸውን፣ አማራነታቸውን፣ ትግሬነታቸውን፣ ኦሮሞነታቸውን ፣ ጋምቤላነታቸውን፣ ሶማሌነታቸውን፣ አፋርነታቸውን ወዘተ እንደያዙ በልዩነት የተዋበ፣ በጋራ የሚታወቁበት ኢትዮጵያዊ የወል ማንነት ፈጥረዋል፡፡ የተዛባ የታሪክ ትርክታቸውን ለፖለቲካ ዓላማቸውና ቅጥ ላጣ የሥልጣን ጥማቸው ማሳኪያ ማድረግ የሚሹ የጎሳ ፖለቲከኞች ሊቀበሉት የማይፈልጉት፣ ግን ሕይወታቸውና መገለጫቸው ሆኖ የሚኖሩት ይሄ ሂደት አሁንም ድረስ አለ፣ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡
ታሪካዊውን ኢትዮጵዊነት ለማደብዘዝ፣ ጥቂት የጎሳ ፖለቲከኞች ብድግ ብለው ራሳቸውን የዚህ ወይም የዚያ ብሄር ወኪል በማድረግ የራሳቸውን ፍላጎት ‹‹የብሄሩ ጥያቄ›› እንደሆነ በማንገብ፣ ማንነት የአንድ ብሄር አባላትን ብቻ የሚያቅፍ አድርገው በማቅረብ፣ የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ የተከበረ ታሪክ በውስን የትንታኔያቸው ፍረጃ በመበየን ትልቅ ስህተት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡
በጽንፈኛ ብሄረተኝነት ታውረው ታሪካችን የፈጠረልንን የአሁን ኢትዮጵዊ ማንነት በመካድ የሁሉንም ኅልውና በሚያናጋ ድርጊት ተጠምደዋል፡፡ ለዚህም ታሪክ አባይ ግብር፣ ሽፋን ይሆናቸው ዘንድ ትናንት የነበረውን አንድ አስከፊ ገጽ ብቻ ለይተው ከልክ በላይ በማራገብ ፣ሠላማዊ አብሮነትን ልማትና ተስፋችንንም በጨለምተኛ ከፋፋይነት ለማዳፈን ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ታች ሲሉ ይታያል፡፡ 
ታሪክን የጠሉና ከታሪክ የተጣሉ ከየትኛውም ጎሳና ብሄረሰብ የወጡ ጽንፈኛ ብሄረተኞች ለአዲሱ ትውልድም ይሄንኑ የተሳሳተ አስተሳሰብና አመለካከት በመመገብ ረገድ ያለ እረፍት በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ራሳቸውን በምሁርነት ማዕረግ የሚጠሩና የሚያስቀምጡ ሀኬተኞች፣ በቋንቋ መለያየታችንን እንደ ሀብትና ውበት ተቀብለው፣ በየቋንቋው ውስጥ ያለውን ዕውቀትና ጥበብ አንጥሮ በማውጣት እንወክለዋለን የሚሉትን የኅብረተሰብ ክፍልንም ሆነ መላውን ኢትዮጵያዊ ከመጥቀም ይልቅ፣ ቋንቋን የጠብና የመለያያ መሣሪያ በማድረግ ወጣቱን ትውልድ በማደናገር ረገድ አይዘልቅም እንጂ ለጊዜውም ቢሆን የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ 
በተለይም እንደእኔ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ (አጋነንክ ባልባል አዳም ከተፈጠረ ጀምሮ) እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ወደር የሌለው ባሕላዊ የአስተዳደርና የፖለቲካ ድንቅ አገር በቀል አስተዳደራዊ ሥርዓት የዘረጋ ስለመኖሩ የሚጠራጠር ሰው ፣ ሁኔታው ልብን በሚነካ ሀዘን እንደሚደቀድቅ ይታመናል፡፡ ዛሬ ቀለም ቀመስ ልጆቹ አስቀድመው ‹‹ የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት በማይታይ ቅርስነት በዩኔስኮ ይመዝገብልን›› ብለው ወደ ዓለም አቀፉ ተቋም ከመጮኽ ይልቅ፣ በጥልቅ መርምረውና ዘመኑን በሚዋጅ አግባብ አዘምነውት ትሩፋቱ ለኢትዮጵያውያን፣ ለአፍሪካና ለዓለምም በደረሰ እንዴት መልካም ነበር፡፡
በዚህ ዘመን መልስ ያጣሁለት ጥያቄዬ ፣ ምነው ይህንን ህዝብ የሚመጥን የፖለቲካ ፕሮግራምና ዓላማ ያለው የበቃ ፓርቲና ተጽዕኖ ፈጣሪ ፣ሩቅ አሳቢ መሪ እንዴት ሊፈጠር አልቻለም ? የሚለው ነው፡፡ ልጆች አባቶቻቸውን አልሰሙም ይሆን ? ወይስ አባቶች ለልጆች እንዲሰርጽ አድርገው አልተናገሩም ? እስኪ የባዕድ ርዕዮተዓለሙንና ፍልስፍናውን ተወት በማድረግ፣ ወደ ቦረናና ጉጂ ባሕላዊ ማኅበረሰብ ወርደን በአገር በቀል አስተዳደራዊ ጥበባቸው ሥልጣን እንዴት እንደሚከፋፈሉና እንደሚጋሩ፣ ያለሁከት ወቅት ጠብቀው በትረ-ሥልጣኑን እንዴት እንደሚለዋወጡና ኅ/ሰቡም በፍጹም ልቡ እንዴት እንደሚምናቸው እንመልከት፡፡ ከዚህ ገሃድና አኩሪ እውነታ ጀርባ፣ ተምሬያለሁ ተመራምሬያለሁ የሚል፣ ልብና ልቦናውን በጥላቻ፣ በፍቅረ-ንዋይና ሰቀቀነ-ሥልጣን የሞላው የጎሳ ፖለቲከኛ፣ምንያህል ልቦናው ወደ መንደር ደረጃ ጠቦ እያደረሰ ያለው ጥፋት፣ ለኅሊናና ለታሪክ ፍርድ ፣ሞትና መቃብር በእማኝነት የሚቆጥሩት የውርደት ሪከርድ እንዳስመዘገበ መግለጽ ለማንኛችንም ግልጽ የአደባባይ ትርዒት ነው፡፡ 
ዛሬ የወገኖቹን ደም በከንቱ ከሚያፋስስ ነውጠኛ አማራጭ ይልቅ፣ በቀናው የመግባባት ፣ የመከባበርና የመረዳዳት መንገድ ቢሰለፍ፣ እወክላቸዋለሁ ከሚላቸው ወገኖቹ እግር ስር ቁጭ ብሎ ከዳበረ ዕውቀታቸው ቢማር ፣ከምን ‹‹ነፃ›› ሊያወጣቸው እንደሚገዳደር በአስቂኝ ሁኔታ ለመረዳት ዕድል ባገኘ ነበር፡፡ ቀደምቶች ከፈጣሪ የተሰጣቸውን የዕውቀት ፀጋና በረከት ቢያውቅ ቢያከብረውም ፣ከሥልጣንና ሀብት የበለጠ ክብር የሚያጎናጽፈው ማዕረግ ባገኘ፡፡ ሲሆን ሚታየው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ 
በሠላም ከወገኖቻቸውና ከመላው ዓለም ጋር በፍቅርና በትጋት መኖር የሚገባቸውን የብሄረሰባውን ወጣቶች ልብ በጥላቻ መሙላት፣ ማስጨነቅና ግራ ማጋባት፣ በየትኛውም ሚዛን ተገቢ የሚሆንበት ዕድል ባይኖርም ሲያደርጉት ግን ይታያል፡፡ ሁልጊዜ በስሜታዊነት ተናግሮና ሰንዝሮ በመፀፀት ከማጎንበስ ይልቅ ፣ ቢመርምና ትዕግሥትን ቢፈታተንም ከፍጻሜ በፊት አብዝቶ ማሰላሰል ለሁሉም እንደሚበጅ ይታመናል፡፡ 
ቀደምት ኢትዮጵውን የኖሩበት አገረ-ምድር አሁን ያለውና ወደፊትም የምንኖርበት መሆኑን ዓለም ሁሉ የሚያውቀውና የሚመሰክረው ገሀድ እውነት ሆኖ ሳለ፣ ዛሬን እንዴት መኖር እንዳለብን በማያመለክት የክፋት አቅጣጫ እየገፉ እንዳችን ከሌላው ወገናችንና ቤተሰባችን እንዳንደራረስ ከውስጣቸውም ሆነ ከውጪ ደመኞች በሚፈጠር ግፊት ስለመለያየት ተግተው ይሰራሉ፡፡ በታሪክ ፀብ ምክንያት፡፡
አብሮ አለመኖር ለተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ሆነ ለጠቅላላው ሕዝብ ፍላጎትም ሆነ ችግር መፍትሄ እንደማይሆን ቢያውቁም ፣ ትናንትም ዛሬም በተቃራኒው ያለዕረፍት ይሰራሉ፡፡ የኛም የነሱም የሆነውን የጋራ ታሪካችንን ባለመቀበል፣ ማንም ሊለየውና ሊለውጠው የማይቻለውን ሕብረ ብሄራዊ የሆነውን ውብ ኢትዮጵዊነት፣ ለዚያውም በ‹‹ነፃነት›› ስም የመኮነናቸውና የመጥላታቸው ውጤት ምን እንደሆነ ከየክልሉ በየቀኑ የምንሰማውና የምናየው፣ ሰብዓዊነትን ያዋረደ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፡፡ 
የጎሣ ፖለቲካ አራማጅነት ፣ትናንት ከነበረና ዛሬም እየተሳተፍነው ካለ ታሪክ መጣላት ፣ራስን ያለማወቅና ማንነትን የመክዳት ያህል ከባድ ከመሆኑ በላይ፣ አይደለም ሰፊ ማኅበረሰብን ግለሰብን እንኳ የመቆሚያና የመለያ መሠረት እስከማሳጣት የሚወርድ፣ አበሰኛ የአስተሳሰብ ዝንፈት ነው፡፡ በአንድ ኢትዮጵያዊ የማንነት ዘርፈ ብዙ ሕይወት ውስጥ በባህሉ፣ በሥነ-ልቦናውና በደሙም ተዋሕዶ ያለውን ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት፣ እስላምነት፣ ክርስቲያንነት የቄፈታነት፣ እንደምን ባለ ምድራዊ ጥበብ መለየት ይቻላል ?
ነፃነት፣ ፍትህ፣እኩልነት፣ ብልጽግና ለእያንዳንዳችን፣ ለሁላችንም ኢትዮጵውያን ያለልዩነት የሚገቡን ሆነው ሳለ፤ እንወክለዋለን ወይም ቆመንለታል ለሚሉት የተለየ ብሄረሰብ ወይም ጎሣ ከሱም በቤተሰብ ደረጃ ወርደው ከአንዱ ነጥቀው ለሌላ፣ ከልጅ ነጥቆ ለአባት፣ ከሚስት ነጥቆ ለባል የሚሰጡት ዓይነት የመሆኑ እንቆቅልሽ ደግሞ፣ ግራ አጋቢና ከግርምትም በላይ፣ የሚባል ሚያሳጣ መሆኑን፣ በልቅሶም ሆነ በዘፈን ለመግለጽ የሚቸግር የመሆኑ ነገር፣ የአደናጋሪነቱን መባባስ የት እንደደረሰ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡
የጋራ መገለጫ የሆነ የኢትዮጵዊ ማንነት ፣የተመሠረተበትን ዕምነት ባህልና ወግ፣ ማለትም በሀዘንም ሆነ በደስታ፣ በሠርጉም ሆነ በለቅሶው፣ በልደቱ፣ በምርቃቱ፣ በደቦው በጉዲፈቻው፣ በሰንበቴውና በተዝካሩ፣ በሠደቃውና በዘካው፣ በእነዚህና በሌሎችም የመንፈስና የነፍስ መጋራትና ጉድኝቶች የተጣመረ ተራክቦ ፣በታሪክ ዘመናት ሁሉ በውስጣችን አትመው ያስቀመጡት የማይነዋወጽ የአንድነት ፣የኑሮ መርህና ፍልስፍና ፣ አይደለም ለምድሩ ለሠማዩም መተማመኛችን የመሆኑን ነገር ቢያስተውሉ፣ ዛሬ ለዛሬው ትውልድ በሕብረት ልንሰራ የሚገባንን በማደነቃቀፍና በማጓተት ሊያውኩን ባልደከሙ ነበር፡፡ ከታሪክ ተጣልቶ ትውልድ ላይ ቀን ማጨለም ማለት ይህ ነው፡፡ 
በጎሣ ጥላቻ ሆድና ጀርባ ሆኖ መኖርና መጠላለፍ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ፣ የደረሰብን አሳምረን ከነህመሙ አይተነዋል እናውቀዋለን፡፡ የትናንት ታሪክ ፣ የዛሬ ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶቻችንና የነገም መድረሻ ግባችን፣ መነሻና ዕምብርት ከመሆኑ አንጻር ፣የጋራ ሀብታችንን የኢትዮጵያን ልዕልና ባከበረ/በተቀበለ ሚዛናዊነት ልናውቀውና በተግባራዊ ትምህርት ሰጪነቱ ልንገለገልበት በተገባ፡፡ እውነተኛ የታሪክ ምሁራን ሆይ የፍርሃት ካባችሁን በማውለቅ የሁላችንም የጋራ ሀብት ስለሆነው ታሪክ ወደ አደባባይ ወጥታችሁ ለትውልዱ ለመንገር ተነሱ፡፡
አንድ ሆነን በሠላምና በፍቅር መነጋገር የተከለከልን እስኪመስል ድረስ፣ ጫፍና ጫፍ ይዘን ከተማ ገጠሩን፣ ተማሪ ሠራተኛውን በጠቅላላው አገር ምድሩን በጥላቻ፣ በመለያየት፣ በዕምባና በደም በክለን ስናበቃ፣ እንደ እንደበጎ አድራጊ ፣ያለሀፍረት በሸንጎ ፊት የምንቆምና የምንናገር፣ የገዛ ወገናችንን ቅስም ሰብረን ፣ደርሶ እንደ ጥሩ ሕግ አስከባሪና ፍትህ አደላዳይ የምናስመስል፣ ባቃጠልነው፣ ባፈረስነው፣ ባወደምነው፣ በገደልነውና ባስገደልነው ሳንፀፀትና ሳናፍር፣ በየሚዲያው አደባባይ በድል አድራጊነት መንፈሥ የምንቦርቅ፣ በየማዕዘኑ በዘር ጥላቻ ተሰነካክለን ፣ለአዲሱ ትውልድ የምናቀርብለት ስጦታ ዱባ ሲባል ቅል፣ ሎሚ ሲባል ዕምቧይ እየሆነ የዓለም መዘባበቻና የትውልዶች ማፈሪያ የመሆናችን ነገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ 
ወገኖቼ ! በጎሳ ተለያይቶ በጋራም ይሁን በተናጥል ስኬታማ መሆን እንደማይቻል ለመረዳት፣ በቂ ጎጂና ከንካኝ መክሸፎች በየዘመናቱ አስተናግደናል፡፡ ግን የሚበቃን መቼ ይሆን ? አሸናፊ በሌለው የርስ በርስ ጦርነት መቆራቆሳችን ምን አተረፈልን ? ግዴለም አባቶቻችን ወዳቆዩልን ወደ ቀድሞ ፍቅራችን እንመለስ፡፡ ይሄ አማራ፣ኦሮሞ ፣ትግሬ፣ሱማሌ ፣ሲዳሞ፣ ወላይታ አፋር በመባባል፣ ከዚህም ዝቅ ብለን ከኦሮሞም ጉጂ ቦረና፣ ወለጋ አሩሲ፣ ከአማራም ሸዌ ጎንደሬ፣ ወሎ ጎጃሜ፣ ዝቅ ሲልም ቡልጌ ተጉለቴ፣ ዳሞት ጋይንቴ፣ በአፋሩም በሱማሌውም በሌላውም ሁሉ እንዲህ በሽርፍራፊ እየተቀናነስን፣ በወረደ አስተሳሰብ መነታረኩ እስከመቼ ?? ከታሪክ በመማር ቀደምቶች ያቆዩልንን መልካሙን በመኮትኮት፣ የቆሰለውን በማከም፣ ክፉውንም በመንቀል እንትጋ፡፡ ከሁሉም በላይ በኛና በልጆቻችን የወደፊት በተስፋ ላይ እንስማማ፡፡ በፍቅር አንድ ከሆንን ፣በሠላምና በብልጽግና ፣ከነበረውም የተሻለ በዓለም ፊት እናበራለን፡፡ በልጆቻችንና በልጅ ልጆቻችንም ፊት ሞገስ ይሆንልናል፡፡
ልብ በሉ ! በምጥ የፈሰሰው የወላድ እናቶቻችን ደም፣ በዚህች ምድር ሰርጓል፡፡ በጀግንነት፣ በፍቅር፣ በክብር፣ በችግርና በሀዘንም የኖሩና ያረፉ አባቶቻችን፣ ወንድምና እህቶቻችን አጽም በአፈሯ ውስጥ አለ፡፡ ሕይወት አስተሳሳሪ እትብታችንም በዚህች ቅድስት ሀገር ተቀብሯል፡፡
ኢትዮጵያውያን ልባችን በፍቅር፣ በተስፋና ትዝታ ሠንሠለት፣ከሀገራችን ሁለንተና ጋር በብርቱ ተቆራኝቷል፡፡ ለዚህ ነው ሞትን ያህል የፍጻሜ ዕዳን በናቀ ጽኑ ጀግንነት የምንወድቅላትና፣ሌሎችን ግር በሚያሰኝ ትንግርት አብዝተን የምንወዳት፡፡ ለዚህ ነው ዕጅ ለዕጅ ተያይዘን ትውልዳዊ ቁም ነገር ለመሥራትና ቋሚ አሻራ ለመተው በአንድነትና በፍቅር ደፋ ቀና የምንልላት፡፡ ‹‹..ፍቅር የሁሉ ነገር በኩርና ማሰሪያ ነው፡፡›› እንዲል መጽሐፍ፡፡
የዛሬ ኢትዮጵያውያን ቀደምት ወላጆቻችን ያቆዩልንን፣የአብሮነት ውበትና ኃይል፣ለዘመናት ደክመው በውስጣችን ያነጹት፣ ጉራማይሌ ሕብረ-ብሔራዊ ማንነት፣የዕውቀትና ንጹሕ የሰብዓዊ አመለካከት ትሩፋቶች፣ በውስጣችን ምንጊዜም ይኖራሉ፡፡ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን ካላስተላለፍናቸው ግን ይጠፋሉ፡፡ ስለዚህ ዘወትር በምንምና በማንም በማይነዋወጽ ሥጋዊና መንፈሣዊ ሕይወት፣ እርስ በራሳችን እንከባበር፣እንዋደድ፡፡ ሌሎችንም እንዲሁ በፍቅር፣በእውነትና በአክብሮት እንቅረብ እንያዝም፡፡ ለሺህ ዘመናት ከተቀመመ ኢትዮጵያዊነት የወረስነው መለያ ቅርሳችን ይሄው ነውና፡፡
በመጨረሻም ! በሥጋ ባልተወለድንበት፣ በአያት ቅድመ-አያቶቻችን ዘመን፣ እኛን በፀነሰ የኅልውናቸው ማኅጸን ውስጥ ነበርን፡፡ በዚህም አማካይነት የእነሱንና የሀገራችንን ፍቅርና በረከት ሁሉ፣ ልክ አብረን ያለን ያህል ተቋድሰናል፡፡ የዚህን እውነተኛ ትስስራዊ የፍቅር ምሥጢር ልባችን በትክክል ያውቀዋል፡፡ ወደፊትም በማንኖርበት የትውልዶች ዕድሜ፣በሥጋዊ አካል ባንኖር እንኳን፣በልጅ ልጆቻችን የመንፈሥና የደም ጽኑ ኢትዮጵያዊ ቅስም ውስጥ፣በግልጽና በስውር በታሪክ ዘላለም እንኖራለን፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *