ተከሳሾች 1ኛ ተከሳሽ አማረ አምሳሉ፣ 2ኛ ተከሳሽ ወልደጊዮርጊስ ወልዱ፣ 3ኛ ተከሳሽ ኢሳያስ ዳኘው፣ 4ኛ ተከሳሽ አብዱል ሃፊዝ አህመድ፣ 5ኛ ተከሳሽ ማስረሻ ጥላሁን፣ 6ኛ ተከሳሽ ሰይፈ ኃይለስላሴ፣ 7ኛ ተከሳሽ ፀጋየ መኮንን፣ 8ኛ ተከሳሽ አይተንፍስ ወርቁ፣ 9ኛ ተከሳሽ ጌታሁን ያሲን እንዲሁም 10ኛ ተከሳሽ ሳሙኤል ፈጠነ ሲሆኑ ስልጣንን ያላግባብ በመገልገል እንዲሁም የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ከ 259 ሚሊየን ብር በላይ በኢትዮ ቴሌኮም፣ በህዝብና በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል ተጠርጥረው ዐቃቤ ሕግ በዛሬው ዕለት ክሱን መስርቷል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በክሱ እንዳመለከተው ተከሳሾች በሶማሌ ክልል የሞባይል ማስፋፊያ ግንባታ የአገልግሎት ግዥ ውል በሚከናወንበት ወቅት ለራሳቸው ብሎም ለብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ለማስገኘት በማሰብ የኢትዮ ቴሌኮምን የግዥ መመሪያ ብሎም የፌዴራል መንግስት የመንግስት ግዥ አፈፃፀም መመሪያ ወደ ጎን በመተው የ ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያቀረበውን የሲቪል ስራ የሚሰራበትን ዋጋ 99,905,731 ብር ወደ ጎን በመተው ያለውድድር የብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በ321,710,424 ብር እንዲሰራ በማድረግ 221,804,693 ብር ጉዳት በማድረስ እንዲሁም በኢትዮ ቴሌኮም የግንባታ ርክክብ ዝርዝር ስፔስፊኬሽንን መሰረት ሳያደርግ 51 ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ ርክክብ በመደረጉ በዚህም ከ69,027,085 ብር በላይ ከደንብና መመሪያውጭ እንዲከፈል በማድረግና 161 የመፀዳጃ ቤቶችና 161 የጥበቃ ቤቶች የግንባታ ሂደታቸው ሳይጠናቀቅ እንደተጠናቀቁ በማስመስል ርክክብ በማድረግ በአጠቃላይ ከ295,586,120 ብር በላይ ጉዳት በማድረስ በከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ከችሎቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዛሬው ዕለት ክሱ የተነበበላቸው ለ5ኛ ና 8ኛ ተከሳሾች ሲሆን ተከሳሾች በበኩላቸው ክሱን ተረድተነዋል በማለት የዋስትና መብት እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀል ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣቸው ከባድ የሙስና ወንጀል በመሆኑ የዋስትና መብታቸው ይከልከልልኝ በማለት አመልክቷል፡፡

በሌላ መዝገብ ተከሰው በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ክሱ ደርሷቸው በችሎት እንዲነበብ እና በሌላ ክስ የጋዜጣ ጥሪ የተላለፈላቸው 2ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪው መሰረት እንዲስተናገዱ ብሎም 1ኛ፣ 6ኛ፣ 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሾች የፌዴራል ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ ማለቱን ከችሎቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ የወንጀል ችሎት ሐምሌ 2/2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት 5ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ ያደረገ ሲሆን ተከሳሾች ከጠበቃ ጋር በመሆን የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለሐምሌ 8/2011 ዓ.ም እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ በሌላ መዝገብ ተጠርጥረው በማረሚያ ቤት የሚገኙት 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ክሱ ቀድሞ እንዲደርሳቸውና ለሐምሌ 8/2011 ዓ.ም ችሎት እንዲቀርቡ ብሎም ያልተያዙ ተከሳሾችን በተመለከተ የፌዴራል ፖሊስ ለሐምሌ 15/2011 ዓ.ም አፈላልጎ እንዲያቀርብ እንዲሁም 2ኛ ና 7ኛ ተከሳሾች በሌላ መዝገብ የጋዜጣ ጥሪ ቢደረግም በዚህኛው ክስ ግን የስነስርአት ሕጉን መሰረት በማድረግ የክስ ሂደቱ የሚከናወን መሆኑን ከችሎቱ ለመረዳት ተችሏል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *