በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ 249 ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸውን የከተማው ፖሊስ አስታወቀ። የከተማው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ጉተን ሌሊሳ እንደገለጹት፥ ሰሞኑን በመኖሪያ ቤትና በኬላ ላይ በተደረገ ፍተሻ ነው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎቹ በቁጠጥር ስር የዋሉት።

በተደረገው ፍተሻም 138 ጠብመንጃዎች፣ 76 ሽጉጦች እና 35 ጩቤዎች የተያዙት ሲሆን፥ በተጨማሪ 90 የሺሻ እቃዎች መያዛቸውንም ተናግረዋል። ኮማንደር ጉተን እንዳሉት መሳሪያዎቹ ሊያዙ የቻሉት ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ እና በተደረገ ክትትል ነው። ወንጀልን በጋራ ለመከላከል ህብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ኮማንደሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመተከል ግጭት የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ከሁለት ቀናት በፊት በተፈጸመ የሰዎች ግድያ የተጠረጠሩ አምስት ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሀመድ ሃምደኒል እንደገለጹት ሰኔ 30 ቀን 2011ዓ.ም በወረዳው ገነተ ማርያም ቀበሌ ተፈጥሮ በነበረ ግጭት የሰዎች ሕይወት አልፏል።

በግድያው የተጠረጠሩ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን የተናገሩት ኮሚሺነሩ፥ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሁለቱ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው ለፖሊስ በሰጡት የእምነት ቃል አረጋግጠዋል ብለዋል።

በቀሪ ሦስት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራው መቀጠሉን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት አካባቢው እየተረጋጋ በመምጣቱ ከነዋሪዎች ጋር ህዝባዊ ውይይት መጀመሩን ተናግረዋል።

በግጭቱ የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉን የተናገሩት ኮሚሽነር መሃመድ፥ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም በጤና ተቋም የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

“ፖሊስ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የሚያካሂደውን ዞኑን የማረጋጋት ሥራ ዘላቂነት እንዳይኖረው በድብቅ ትንኮሳ የሚያካሂዱ ግለሰቦች አሉ” ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ከግጭቱ በስተጀርባ ያለውን ድብቅ ሴራ ለማክሸፍ ፖሊስ በአዲስ ስልት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽነር መሀመድ እንዳሉት ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ምሽት በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩና የአሁኖችን ጨምሮ 98 ሰዎች ተይዘዋል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ በማሰባሰብ ጉዳያቸው በጊዜ ቀጠሮ እየታየ መሆኑንም ኮሚሽነር መሃመድ ጨምረው ገልጸዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *