የህወሐት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ በበርካቶች ዘንድ የተለያዩ ጉዳዮችን በማስነሳት እያነጋገረ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ዶ/ር አደም ካሴ አበበ፣ ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ገቢሳ፣ እንዲሁም አቶ ልደቱ አያሌው በመግለጫውና በገዢው ፓርቲ ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

ኢህአዴግ ዕጣ

ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ገቢሳ እንደ ጥምረት ፓርቲዎቹ አንድ ሃሳብ እንዲኖራቸው የሚጠበቅ አይደለም ይላሉ። ለፕሮፌሰሩጥምር ፓርቲ ውስጥ ያሉ ቡድኖች ካልተግባቡ የመፍረስ እድል ይኖራል፤ ይህም አዲስ ነገር አይደለም።

ዋናው ነገር የኢህአዴግ ፓርቲዎች ጥምረት ከሌለ ሃገሪቱ እንዴት እንደምትተዳደር ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ “ገዢው ፓርቲ ችግር ውስጥ ከገባ ሰንብቷል” ሲሉ አስተያየታቸውን ይቀጥላሉ።

ኢህአዴግን በአንድነት አዋህዶ ይዞት የነበረው ህወሐት እንደነበር የሚናገሩት ፕሮፌሰር ህዝቅኤል አሁን ህወሐት ያንን ለማድረግ በሚችልበት ደረጃ ላይ ስላልሆነ እያንዳንዱ የጥምረቱ አባል የሆነ ፓርቲ በተለያየ አቅጣጫ መሄድ ከጀመረ ቆይቷል ባይ ናቸው።

ወደፊት ልዩነቶቻቸውን አቻችለው አብረው ሊቀጥሉ ይችላሉ ወይም ደግሞ ሊታረቅ ወደማይችል ቅራኔ ውስጥ ገብተው ፓርቲው ሊፈረካከስ ይችላል ሲሉም ያላቸውን ግምት ያስቀምጣሉ፤ ነገር ግን በማለት “አሁን ካለው ሁኔታ ተነስተን ይሄ ሌሆን ይችላል ለማለት አስቸጋሪ ቢሆንም ከሁለቱ ግን አንዱ ይሆናል”ብለዋል።

የኢህአዴግ ጥምር ፓርቲዎች ውስጥ እየታዩ ካሉት ነገሮች በመነሳት በጥምረቱ ውስጥ በአንድነት የመቆየት እድላቸው የመነመነ ይመስላል የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ቢሆንም ግን ሃገሪቱ ወደ ምርጫ እየሄደች በመሆኗ ያሉባቸውን ችግሮች አቻችለው ለዚያ ሲሉ አብረው ሊቆዩ ይችላሉ ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

አቶ ልደቱ በበኩላቸው ህወሐት አሁን ሀገሪቱ የገባችበት ችግር እውነት ያሳስበው ከሆነ በመውቀስ በመክሰስ ሳይሆን፣ ለዚህ ችግር አገሪቷንና ሕዝቡን የዳረጉት መሰረታዊ ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚለው ገምግሞ፣ የእርሱ ተጠያቂነት ከፍተኛ እንደነበር አምኖ በመቀበል ነው መፍትሄ ማግኘት የሚቻለው” ይላሉ አቶ ልደቱ።

ህወሐት “ባለፉት 27 ዓመታት የተሰራው ሁሉ መልካም እንደሆነና፣ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ችግር እርሱ ከስልጣን ከተነሳ በኋላ የተፈጠረ አድርጎ የማቅረብ ሙከራው ካለፈው ውድቀቱ አለመማሩን ነው የሚያሳው” ይላሉ።

አቶ ልደቱ አክለውም “ህወሐት የችግሩ አካል ነው፤ የመፍትሄውም አካል መሆን አለበት፤ መፍትሄው አካል ሲሆን ደግሞ በሙሉ የሀላፊነት ስሜት መሆን አለበት” ሲሉ ይመክራሉ።

ኢህአዴግImage copyrightEPRDF

ኢህአዴግ በድሮ ግርማ ሞገሱ አለን?

ኢህአዴግ እንደ ድርጅት አለ፤ በድሮው በጥንካሬው በድሮው አስተሳሰብና ሞገስ ግን የለም ያሉት ደግሞ አቶ ልደቱ አያሌው ናቸው። “ተወደደም ተጠላም ግን ኢህአዴግ አለ፤ አሁን ሀገሪቱን እየመራት ያለው እርሱ ነው” በማለትም አሁን ለውጡን እየመሩት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትርም የተመረጡትም በኢህአዴግ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ኢህአዴግ እርሳቸውን ሲመርጣቸው የህወሐት አባላትም እዚያው ቁጭ ብለው እጃቸውን አውጥተው ነው የመረጧቸው ያሉት አቶ ልደቱ ይህንን ሀገርና ህዝብ ወደዚህ አይነት ከፍተኛ ችግር የከተተው እንደ ድርጅት ራሱ ኢህአዴግ የሚባለው ድርጅት ስለሆነ ከዚህ ችግር ለማውጣትም መስራት ከፍተኛ ሚና መጫወት ያለበት ራሱ ኢህአዴግ ነው ብለው ያምናሉ።

“ኢህአዴግ ስንል ደግሞ ህወሐትንም ይጨምራል። ስለዚህ ከመነጣጠል ይልቅ በአብሮነት በመስራት ለለውጡ መትጋት አለበት።” በማለትም የፕሮፌሰሩን ሀሳብ ይሞግታሉ።

የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር አደም ካሴ በበኩላቸው ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ የድሮው ኢህአዴግ ነው ለማለት ይከብዳል ይላሉ፤ ከመሪዎቹ አንፃርም አብረው ሊታዩ ቢችሉም አብረው እየሰሩ ነው ለማለት ይከብዳል። ከዚያ አንፃር የኢህአዴግ የድሮው ጥንካሬና ሞገስ አለ ብሎ ማሰብ አይቻልም በማለት ህወሐት መግለጫ ላይ ከዚያ አንፃር ያዩት አዲስ ነገር እንደሌለ ጠቅሰው “አዲሱ ነገር ግልፅ ማድረጋቸው ነው” ብለዋል።

ህወሐት ከአዴፓ ጋር ለመስራት እንደሚቸገር ከገለጸበት ይልቅ ከአዳዲስ ኃይሎች ጋር ለመስራት ያለውን ፍላጎት አንድ ላይ ሲታይ የሚያሳየው ነጥብ ከኢህአዴግ መልቀቅን እንደ አንድ አማራጭ እያቀረቡ መሆኑን ነው ያሉት ዶ/ር አደም “ይህ ለኢህአዴግ ከግንባርነት ወደ ወጥ ፓርቲነት እሸጋገራለሁ እያለ ባለበት ጊዜ ላይ መከሰቱ የኢህአዴግ ዕጣ ፈንታ ላይ ጥያቄዎች እንድናነሳ ይጋብዘናል” ሲሉ የፈጠረባቸውን ጥያቄ ያነሳሉ።

ፕሮፌሰር ህዝቄል በበኩላቸው ከሁሉ ግልጽ እየሆነ የመጣው በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች በግንባሩ ዉስጥ የፈጠሩትን ጥምረት በማስቀረት ወደ አንድ ወጥ ውሁድ ፓርቲነት እንሸጋገራለን ያሉት ዕቅድ ፈጽሞ ሞቶ የተቀበረ ጉዳይ መሆኑን በመግለፅ የግንባሩ ውህደት የማይሆን እንደሆነ ይናገራሉ።

ዶ/ር አደም አክለውም ከዚህ በፊትም ህወሐት ‘ኢህአዴግ ይዋሃዳል’ ሲባል ጥያቄ ማንሳቱን አስታውሰው “ከዚያ አንፃር የምንጠረጥረውን ነገር እውነተኛነት የሚያረጋግጥና ኢህአዴግ በአንድ ግንባርነት መቀጠል እየተሳነው መሆኑን የሚያመለክት ነው” በማለት ከፕሮፌሰር ህዝቄል ጋር የሚመሳሰል ሀሳብ ያነሳሉ።

እንደ ግንባር የአባል ድርጅቶቹ ድክመትና ጥንካሬ የግንባሩ ድክመትና ጥንካሬ ነው የሚሉት ዶ/ር አደም አሁን ግን ሁሉም ፓርቲዎች በራሳቸው የተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ናቸው ሲሉ ያክላሉ።

በተለይ ሦስቱ አዴፓ፣ ኦዴፓና ደኢህዴን በየክልላቸው የራሳቸው ፈተናዎች አለባቸው ያሉት ዶ/ር አደም፤ እስካሁን በክልሉ ውስጥ ጠንካራ ሆኖ የሚታየው ህወሐት ብቻ ነው በማለት ግንባሩ ኣለበትን ፈተና ለማሳየት ይሞክራሉ።

ስለዚህ እነዚህ ድርጅቶች እንደፓርቲ ከችግሮቻቸው ተላቀው ጠንካራ ካልሆኑ በስተቀር ግንባሩ ጠንካራ ሆኖ እንደበፊቱ ሊቆም ይችላል የሚለው አስቸጋሪ ነው ያሉት ዶ/ር አደም፣ ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ማጠናከር ላይ መስራት ካልቻሉ የግንባሩ ህልውናን ማስቀጠል ፈታኝ እንደሆነ ይናገራሉ።

ፓርቲዎቹ ራሳቸውን አጠንክረው መቆም ካልቻሉ ለራሳቸው ህልውናም ሆነ ለኢህአዴግ አንድ ሆኖ መቆም ፈታኝ ነው የሚሆነው ሲሉም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ክልሎች ግጭት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ?

“እንደዚያ የሚያስቡ ወይንም ሙከራ የሚያደርጉ ኃይሎች ሊኖሩ ይችላሉ” ኣሉት አቶ ልደቱ ናቸው። ነገር ግን የትግራይም ሆነ የአማራም ህዝብ በአሁኑ ወቅት አሁን ከገባበት ችግር መውጣት ነው እንጂ ወደሌላ አሳሳቢ ውጥረትና ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት አለው ብዬ አላምንም በማለት በሕዝቡ ላይ ያላቸውን ጠንካራ እምነት ይገልፃሉ።

“ህዝቡ የዚያ አይነት እምነት እስካለው ድረስ እንደዚያ አይነት የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች የሚፈልጉትን ነገር ያደርጋሉ ብዬ አላምንም።”

ዶ/ር አደም በበኩላቸው ህዝቡ መንግሥታችን ጠንካራ ነው ካለ መረጋጋቱ ሰላሙ ይኖራል። ካልሆነ ግን ደካማ መንግሥት ነው ያለው ብሎ በሚያስብ ማህበረሰብ ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ማሰብ አስቸጋሪ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

አክለውም መንግሥት የተለያዩ የሕግ ጥሰቶች ላይ መለሳለስ ሲያደርግ መታየቱን በማንሳት ግጭቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ያላቸውን ግምት ያስቀምጣሉ። “እነዚህ ግጭቶች በተለያዩ ብሔሮች መካከል ሊከሰቱ ይችላሉ። በአንድ ብሔር ውስጥም፣ እርስ በእርስ ሊሆን ይችላል። ሌላው ደግሞ በክልሎች መካከል ሊከሰት ይችላል።”

ለኢትዮጵያ የወደፊት ችግር የሚሆነው የኢህአዴግ የወደፊት ሁኔታ ነው የሚሉት ዶ/ር አደም፣ የአባል ድርጅቶች አቋም መለያየት፣ ምርጫ ላይ ያለው ሁኔታና የሲዳማ ጉዳይ ከሚኖሩ ችግሮች መካከል መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

እነዚህ ጉዳዮች በብስለትና በትዕግስት ካልታዩ ግጭት አይኖርም ማለት እንደሚከብድ ዶ/ር አደም አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አብሮ መስራት

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከራስ ቡድን ፍላጎትና ጥቅም በላይ የሀገር ጥቅም የሚያሳስባቸው ከሆነ አማራጩ እርስ በእርስ መካሰስ፣ የፖለቲካ ሽኩቻው ወስጥ መግባት ሳይሆን አንድ ላይ መቆም ነው የሚሉት አቶ ልደቱ አያሌው ናቸው።

ህወሐት 27 ዓመት ሙሉ የበደለውን ህዝብ ለመካስ የሚፈልግ ከሆነ መፍትሔው ጥሎ መውጣት አይደለም የሚሉት አቶ ልደቱ፤ ግንባሩ ውስጥ ሀቀኛ የሆነ ትግል አድርጎ ችግሩን በጋራ እንዲፈታ መጣር እንዳለበት ይመክራሉ።

“ኢህአዴግ እንደ አንድ ድርጅት መቆም የሚጠበቅበት ጊዜ ዛሬ ነው።”

በዚህ ሰዓት አኩርፎ መውጣት የኢትዮጵያን ችግር የበለጠ ያወሳስበዋል እንጂ መፍትሄ የሚሰጥ አይሆንም በማለትም ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ከሌላ ድርጅት ጋር በጋራ ስለመስራት

ይህ ሀሳብ ከፋፋይ ነው፤ አሁን ኢትዮጵያዊያኖች በአጀንዳ በተለያየ መልኩ ተከፋፍለን እርስ በእርስ የምንታገልበት ወቅት መሆን የለበትም። አንድ ላይ ሆነን ይህንን ችግር ተወጥተን ህዝቡ ወደ ሚፈልገው አቅጣጫ፣ ይህችን ሀገር ለማሻገር ነው መጣር ያለብን የሚሉት አቶ ልደቱ ናቸው።

ስለዚህ ህወሐት “ከልጅነት ጀምሮ የተጠናወተው የመከፋፈል ባህሪ” አሁንም እንዳልለቀቀው ያወጣው መግለጫ በደንብ ያሳያል ይላሉ አቶ ልደቱ። ስለዚህ ከዚህም አንፃር የያዘው መንገድ ትክክል አይደለም። አሁን የሚጠበቀው አንድ ላይ ቁጭ ብሎ መስራት ነው እንጂ መነጠል እንዳልሆነ ይመክራሉ።

በሀሳብ ደረጃ ካየነው በሚያራምዱት ሀሳብ፤ የህወሐት አይነት የብሔረተኝነት አስተሳሰብ ከሆነው፣ ጠንካራ ብሔርተኝነት ካለባቸው ጋር እንደሆነ የሚጠቁሙት ዶ/ር አደም፤ “ስለዚህ ወደፊት ከሚመሰረተው ክልል ከሲዳማ ጋር፣ ጠለቅ ብለህ ካሰብከው ደግሞ በመርህ ደረጃ ከአማራ ክልሉ አብን ጋር፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ካለው ከኦነግ ጋርም የሚመሳሰል ነገር ነው ያለው” በማለት ህወሀት ከኢህአዴግ ጋር አልቀትልም ቢል ከነማን ጋር እሰራል ለሚለው ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ነገር ግን ህወሐት ከአማራና ከኦሮሚያ ክልል ውጪ ካሉ ቡድኖች ጋር አብሮ ሊሰራ ይችላል በማለት ቢሆንም ግን ውጤታማ ትልቅ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመሆን እንደሚከብደው አመልክተዋል።

ህወሐት እንደ ፓርቲ ትልቅ ለመሆንና አሁን ያለውን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለማስቀጠል ከትልልቅ ክልሎች ከወጡ ፓርቲዎች ጋር መስራት ይጠበቅበታል ይላሉ ዶ/ር አደም።

ድርጅቱ በግልፅ ከእነዚህ ከእነዚህ ጋር እሰራለሁ ባላለበት በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት ይቸግረኛል የሚሉት አቶ ልደቱ “ነገር ግን ፖለቲከኛ ስለሆንኩ በተዘዋዋሪ ምን ለማለት እንደፈለገ ይገባኛል” በማለት “ይህ አካሄድ አፍራሽ ነው አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኃይል አሰላለፍ በከፍተኛ ደረጃ የሚያናውጥ ሀገሪቱን ወደበለጠ ውስብስብ ችግር የሚከት ነው።” ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

በዚህ መግለጫ ትኩረት የተደረገው አዴፓ ላይ ነው። እርሱን እንደጠላት በመፈረጅ ከእርሱ አመለካከት ጋር የሚሄዱ ሌሎች ድርጅቶችን ምናልባትም ከኢህአዴግ ውጪ ካሉ ድርጅቶች መካከል ከህወሓት አመለካከትና አደረጃጀትጋር አብረው ከሚሄዱ ኃይሎች ጋር ለመስራት የመፈለግ ነገር እንደሚያዩ ይናገራሉ አቶ ልደቱ።

የአዴፓ ሎጎImage copyrightADP

ኢህአዴግ ምን ያድርግ?

ገዢው ፓርቲ፤ ኢህአዴግ የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ በብቸኝነት ተቆጣጥሮ እያለ በሀላፊነት ስሜት መስራት አቅቶት የሚበታተን ከሆነ እርሱ ውስጥ የሚፈጠረው መበታተን ለሀገርም ሊተርፍ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው አቶ ልደቱ።

ስለዚህ ትልቅ ሀገርና የሕዝብ ሀላፊነት ያለባቸው መሆናቸውን አውቀው ከመቼውም በላይ ከግል እንዲሁም ከቡድን ስሜትና ፍላጎት፣ ከፖለቲካ ሽኩቻ በፀዳ መልኩ አብረው መስራት አለባቸው ሲሉም ይመክራሉ።

“አዴፓም አሁን ባለበት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ሊረዳ የሚገባው ነው” ያሉት አቶ ልደቱ ከፍተኛ አመራሮቹ ተገድለውበት ተዳክሟል፤ ይህንን ድርጅት በዚህ ወቅት ለማጥቃት መሞከርም ተገቢ አይደለም ሲሉም ይወቅሳሉ።

ሀገር እንደሚመራ ትልቅ ፓርቲ ኢህአዴግ ያለበት ሀላፊነት ትልቅ ነው ያሉት ዶ/ር አደም፤ በእርግጥ በገዢው ፓርቲ አባላት መካከል ልዩነቶች አሉ። ይህ ደግሞ በፓርቲዎቹ መካከል ብቻ ሳይሆን በአንድ ፓርቲ ውስጥም ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል።

“ነገር ግን መሰረታዊ በሆኑት ጉዳዮች ላይ መስማማት ያስፈልጋል።” በማለትም ሰላምን መጠበቅ፣ በሕዝቦች መካከል መከባበር እና ትግስት እንዲኖር ማድረግ፣ ያንን ለማድረግ ግን እንደፓርቲ እየተነጋገሩ መሄድ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቅሳሉ። “ሀገርን የሚመለከት ጉዳይን በጋራ ማሳካት ካልቻሉ ግን ሀገርን እንደሚመራ ፓርቲ የእነሱ ችግር ሀገሪቱን ችግር ውስጥ ሊጥላት ይችላል” በማለት ያላቸውን ስጋት ያስቀምጣሉ።

አክለውም እነዚህ ግን ኢህአዴግ ብቻውን የሚፈታቸው ችግሮች አይደሉም በማለት አንዳንዶቹ ችግሮች ላይ ሌሎች ፓርቲዎችም ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ይጠቅሳሉ።

“ዋናው ነገር ልዩነት ተፈጥሯዊ እንደሆነ ተማምኖ በተፈጠረው ነገር ሳይደናገጡ የጀመሩትን የዲሞክራሲ መንገድ ማስቀጠል ነው” በማለት ዶ/ር አደም ሀሳባቸውን ያጠናቅቃሉ።

BBC 

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *