የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የክልሉን ሰላም እያደናቀፉ ባሉ አካላት ላይ የህግ የበላይነትን ለማርጋገጥ የክልሉን የጸጥታ አካላትን አቅምና ብቃት በማሳደግ ህግን በሚጥሱ አካላት እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ መሆኑን ተናገሩ፡፡ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ይህን ያሉት የክልሉን የ2011 የስራ አፈፃጠም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።

መንግስት በቁርጠኝነት የሰላም እና ልማት ስራዎችን ሲሰራ ቢቆይም በክልሉም ሆነ በሀገር የመጣው ለውጥን የሚጻርሩ አካላት ህብርተሰቡ መካክል ግጭት በመፍጠር ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ማፈናቀላቸው ለክልሉ መንግስት ፈተና እንደነበር አንስተዋል።

የመንግስትን፣ የህዝብን እና የአባ ገዳዎችን ጥሪ የተቀበሉ የታጠቁ አካላት ቢኖሩም ጥሪውን ያልተቀበሉት የጥፋት ሃይሎች ተልእኮን በመቀበል በክልሉ ህዝብና አመራሩ ላይ የፈጸሙት አሰቃቂ ተግባራትም ሌሎች ችግሮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ርእስ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ አክለውም፥ በ2011 በጀት ዓመት በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት አቅም ላይ ጥናት በማድረግ 50 ሺህ ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ገልፀው፥ በዚህም 9 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 27 ፕሮጄክቶች 1 ነጥብ 758 ሄክታር መሬት መሰጠቱን ገልፀዋል።

በክልሉለ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድለ ለመፍጠር ታቅዶ በተሰራው ስራም ለ606 ሺህ ዜጎች በቋሚነት፤ ለ386 ሺህ ዜጎች ደግሞ በጊዜያዊነት በድምሩ ለ993 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን አክለው ገልፀዋል።

በመጠጥ ውሃ አቀርቦትም በክልሉ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን በ2010 በጀት ዓመት ከነበረበት 63 ነጥብ 8 በመቶ በ2011 በጀት ዓመት 66 ነጥብ 13 በመቶ ማድረስ መቻሉንም ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራም በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው፤ በክልሉ 2 ቢሊየን የዛፍ ችግኞችን ለመትከል እየተሰራ መሆኑን እና አስካሁን ባለው ጊዜም 661 ነጥብ 8 ሚሊየን የዛፍ ችግኞችን መትከል መቻሉን አስታውቀዋል።

በግብርናው ዘርፍም በ2011/12 የምርት ዘመን በ6 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችን በመዝራት 184 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ሰብል ለማግኘት ታቅዶ እስካሁን 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል አይነት መሸፈኑን ጠቅውሰው እቅዱን ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ  ተናግረዋል።

በትምህርት መስከም በክልሉ ውስጥ በሚገኙ 17 ሺህ 16 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 9 ነጥብ 24 ሚሊየን ተማሪዎችን የትምህርት እድል እንዲያገኙ በተያዘው እቅድ መሰረት 9 ነጥብ 16 ማለትም ከአቅዱ 99 ነጥብ 2 በመቶው የትምህርት እድል እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ በተሰራው ስራም በጤና 774 ሺህ እናቶች በጤና ተቋማት መውለዳቸውን ጠቅሰው፥ ተላላፊ የሆኑ እንደ ቲቢ፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስ እና የወባ በሽታዎችን ለመከላከልም ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በርካታ ስራዎች መስራት መቻሉን አስታውቀዋል።

በገቢ ዘርፍም በበጀት ዓመቱ 18 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በተሰራው ስራ ከመደበኛ ገቢ 15 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር፤ ከማዘጋጃቤታዊ ገቢ 3 ነጥብ 27 በድምሩ 18 ነጥብ 69 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል ያሉት አቶ ሽመልስ፥ ይህም እቅዱን 101 በመቶ ማሳካት መቻሉን እንደሚያመላክት አንስተዋል።

በ2012 በጀት አመት የህግ የበላይነትን ለማስርጋገጥ ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሰራ የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በህገ ወጥ የመሬት ወረራ ዙሪያ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እና ሌሎች ተጀምረው ያልተጠናቀቁ መሰረተ ልማቶች መፍትሄ እንዲበጅላቸውም እና በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ያለውን የጸጥታ ችግር እንዲፈታጠይቀዋል።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ በበኩላቸው በጉባኤው የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ እንዳሉት÷ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር እና የህግ የበላይነት እንድርጋገጥ ባለፈው አመት በተሰራው ስራ አበርታች ውጤት ተመዝግቧል ።

የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማርጋገጥ ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት አፈ ጉባኤዋ የክልሉ መንግስት የተገኘውን ለውጥ ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ባለበት ሁኔታ የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ አካላት ሂደት በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደሌላቸው ተናግረዋል። የ2011 የስራ አፈጻጸም ሪፖርትም በምክትል ርእሰ መስተዳደሩ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል፡፡

በምክር ቤቱ አባላት በኢንቨስትመንት የተያዘ መሬት ያለመልማት በጤና ተቋማት በቂ የህክምና መሳሪያ እና መድሃኒት አቅርቦት እጥርት እንዳለ ተነስቷል። ጨፌ ኦሮሚያ በዚህ ጉባኤው በክልሉ የ70 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ ያጸደቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሀገሪቱ በፖለቲካው መስክ የተገኘውን ድል ወደ ኢኮኖሚው ለማሸጋገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አቅጣጫ ማስቀመጥ እና ሹመቶችን መስጠትም ከጉባኤው ይጠበቃል።

ቀደም ሲል የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሃምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ የተለያዩ መመሪያዎች እና ደንቦችም ይጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

ጨፌው ባለፈው በጀት አመት 16 የተለያዩ ደንቦች እና መመሪያዎችን በማጽደቅ በተለያዩ አማራጮች ለክልሉ ስራ አስፈፃሚዎች እና ህዝብ እንዲደርስ ማድረጉንም አፈ ጉባኤዋ አስታውሰዋል፡፡

በአዳነች አበበ -FBC

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አስከሬን እንዲለቀም ታዘዘ - ትህነግ የአጽም ፖለትካ ድራማ ይፋ ሆነ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *