ጀርመናዊትዋ ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ሆነዉ ተመረጡ። ፎን ዴር ላየን ከአዉሮጳ ኅብረት የሕዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት 747 አባላት የ383ን ይሁንታ አግኝተዋል። ቀድሞዋ የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ፎን ዴር ላየን፤ የኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ለመሆን 374 ድምፅን ማግኘት ብቻ ይበቃቸዉ ነበር።

የፎን ዴር ላየን የአመራረጥ ሂደት

የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት፣የህዝብ እንደራሴዎች ህብረቱ ለኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ያጫቸውን የኡርዙላ ፎን ዴር ላየንን ሹመት ዛሬ ማምሻውን አጽድቋል።የጀርመን የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር ፎን ዴር ላየን፣ ሳይጠበቅ እና ከተለመደው አሰራር በተለየ ለዚህ ኃላፊነት መታጨታቸው ሲያወዛግብ ከርሟል። የአውሮጳ ህብረት መሪዎች ከሁለት ሳምንት በፊት ከብዙ ውዝግብ በኋላ ነበር የሥራ  ዘመናቸው በመጪው ህዳር የሚያበቃውን 4 የህብረቱን ከፍተኛ ሃላፊዎች የሚተኩ እጩዎችን የመረጡት።በዚህ ምርጫም የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ወይዘሮ ኡርዙላ ፎን ዴር ላየንን የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት፣የቤልጂግ ጠቅላይ ሚኒስትር ቻርልሰ ሚሼልን የህብረቱ የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እንዲሁም የዓለም የገንዘብ ድርጅት በምህጻሩ IMF የበላይ እና የቀድሞ የፈረንሳይ የገንዘብ ሚኒስትር ወይዘሮ ክርስቲን ላጋርድን ለአውሮጳ ማዕከላዊ ባንክ ገዥ፣ እንዲሁም የስፓኝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴፕ ቦሬልን ለህብረቱ የውጭ ጉዳዮች ሃላፊነት አጭቷል። ሁለት ሴቶች ለነዚህ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች መመረጣቸው ህብረቱ የሴቶች ተዋጽኦን ለማስተካከል ከዚህ ቀደም የገባውን ቃል አሳክቶለታል።ሆኖም መሪዎቹ በእጩዎቹ ስየማ ላይ የተስማሙት ሦስት ቀናት ከወሰደ ከባድ ክርክር በኋላ ነበር።የቀደመው ግምት መሪዎቹ በተለመደው አሠራር በአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ ፣አብላጫ ድምጽ ያገኙትን የአውሮጳ ህዝቦች ፓርቲ በምህጻሩ የEPP ተቀዳሚ እጩ፣ ማንፍሬድ ቬበርን ይመረጣሉ የሚል ነበር።በቀደመው የአመራረጥ ስርዓት በምርጫው አብላጫ ድምጽ ያገኘ ፓርቲ ቀዳሚ እጩ ነበር ለኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት የሚታጨው።የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም የእህት ፓርቲያቸው የጀርመኑ የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ አባል ቬበር  የኮሚሽኑ ሃላፊነቱን እንዲወስዱ ነበር የሚፈልጉት።የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ ግን ቬበር ብቃትም እና ልምድ ያንሳቸዋል ሲሉ አጥብቀው መቃወማቸው እና ሴቶችም ለነዚህ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች እንዲመደቡ በመፈለጋቸው ቬበር ሳይመረጡ ቀሩ።ቬበር ሲቀሩ በምርጫው ሁለተኛ ደረጃ ያገኙት ኔዘርላንዳዊው የሶሻል ዴሞክራቶች ተቀዳሚ እጩ ፍራንስ ቲመርማንስ በእጩነት ቢጠቆሙም በተለይ የምሥራቅ አውሮጳ ሃገራት እና ኢጣልያ በመቃወማቸው ይህም ሳይሳካ ቀረ።በመጨረሻም በጀርመን መራሂተ መንግሥት አስተዳደር ለ14 ዓመታት በሦስት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሚኒስትርነት ያገለገሉት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን በሁሉም መሪዎች ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተው

Deutschland Merkel mit Von der Leyen CDU-Parteitag in Karlsruhe (picture-alliance/Sven Simon)

ለኮሚሽኑ ፕሬዝዳንትነት ለመታጨት በቁ።ይሁን እና የፎን ዴር ላይን ሳይታሰብ እና ከተለመደው መንገድ ውጭ የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ መታጨታቸው ሲያነጋግር ነበር የከረመው።ወይዘሮ ፎን ዴር ላየን በብቃትም ሆነ በልምዳቸው ለቦታው የሚመጥኑ ስለ መሆናቸው መሪዎቹም ሆኑ ሌሎች አስተያየት ሰጭዎችም ይስማማሉ።ሆኖም ለሃላፊነቱ የተወዳደሩትን እና ያሸነፉትን ወደ ጎን ትተው እርሳቸው በምርጫ ሳይወዳደሩ ለቦታው መታጨታቸው የህብረቱን ዴሞክራሲያዊ አሠራር የሚፃረር አድርገው የሚተቹ ጥቂት አይደሉም።ከሜርክል ፓርቲ ከጀርመኑ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ጋር ተጣምሮ ጀርመንን የሚመራው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ የርሳቸውን እጩነት አለመቀበሉ ሌላው ችግር ነበር።ፎን ዴርላየን የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎችን ሙሉ ይሁንታ አግኝተው ቢመረጡም ሜርክል ግን የመንግሥታቸው ተጣማሪ ፓርቲ SPD ባለመስማማቱ ጽምጽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሜርክል SPD ከጎናቸው አለመቆሙ ሁኔታውን እንዳከበደባቸው ተናግረው ነበር።
«ኡርዙላ እንድትመረጥ እየሰራን ነው።በጥምር መንግሥቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ ማስታወስ ያለብን ጀርመን የህብረቱን ኮሚሽን ፕሬዝዳንት የመምረጥ እድል ስታገኝ ከ52 ዓመት በኋላ የመጀመሪያው ነው።ሁኔታው ቀላል አይደለም።የጥምሩ መንግሥት አካል የሆነው «SPD»  ግን ከኛ ጋር አብሮ አልቆመም።» 
በግንቦቱ የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ ከቀደሙት ምርጫዎች በተለየ የመሀል ቀኙ የአውሮጳ ህዝቦች ፓርቲ እና የመሀል ግራው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በጋራ ያሸነፉት ድምጽ .አብላጫ ባለመሆኑ ህብረቱ ፎን ዴርላየንን ከተለመደው የህብረቱ አሠራር በተለየ መንገድ ለኮሚሽኑ ፕሬዝዳንትነት ያጨበት አንዱ ምክንያት ነው።የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ

Bildkombo Manfred Weber Ursula von der Leyen

እንደሚለው ባለፉት ዓመታት አብላጫ ድምጽ ያገኙ የነበሩት ሁለቱ ፓርቲዎች ተደራድረው የአሸናፊው ፓርቲ ቀዳሚ እጩ ሥልጣኑን እንዲይዝ ነበር የሚያደርጉት። ይህ የእስከዛሬው አሰራር ግን ዘንድሮ ሊተገበር አልቻለም።ለዚህም ሦስት ምክንያቶች አሉ ይላል ገበያው።  
በልዩ ሁኔታ ለአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንትነት የታጩት ወይዘሮ ፎን ዴር ላየን ከጀርመን መከላከያ ሚኒስትርነታቸው እንደሚነሱ ትናንት ተናግረዋል።ሥልጣኑን ለርሳቸው ለመስጠት እና ላለመስጠት ለመወሰንም የህብረቱ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ድምጽ በመስጠት ላይ ናቸው። ፎን ዴር ላየን የህዝብ እንደራሴዎችን ለማሳመን ዛሬ ጠዋት በምክር ቤቱ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።በዛሬው ድምጽ አሰጣጥ በቂ ድምጽ ላያገኙ ይችላሉ የሚል ስጋት የመኖሩን ያህል አሸንፈው ሃላፊነቱን ቢወስዱም ችግሮች ሊያጋጥማቸው እንደሚችልም ነው ከወዲሁ የሚነገረው።  የ60 ዓመትዋ ወይዘሮ ፎን ዴር ላየን ጀርመንን ትተው ወደ ተወለዱባት የቤልጂግ ዋና ከተማ ብራሰልስ በህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንትነት ይመለሱ አይመለሱ ከዛሬው ድምጽ አሰጣጥ በኋላ ነው የሚታወቀው።እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ አቀላጥፈው የሚናገሩት ፎንዴር ላየን ከሌሎች የሥራ ባለደረቦቻቸው በተለየ በዓለም አቀፍ መድረኮች በራስ መተማመናቸው ጎልቶ የሚታይ ሴት ናቸው። ከተሳካላቸው የመጀመሪያዋ ሴት የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ነው የሚሆኑት።በተወለዱባት በብራሰልስ 13 ዓመት ኖረዋል።አባታቸው እርንስት አልብሬሽት የያኔው የአውሮጳ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ ከፍተኛ ባለሥልጣን በኋላም የጀርመኑ የኒደርዛክሰን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ፕሬዝዳንት ነበሩ።በአንድ ወቅት የሜርክል ተተኪ ተደርገው ይታሰቡ የነበሩት ፎን ዴር ላየን የበርሊኑን ፖለቲካ የተቀላቀሉት መራሂተ መንግሥት  አንጌላ ሜርክል ሥልጣን ከያዙበት ከዛሬ 14 ዓመት አንስቶ ነው።የሰባት ልጆች እናት ፎን ዴር ላየን በ2005 በመጀመሪያው የሜርክል ካቢኔ የቤተሰብ ሚኒስቴር ሆነው እስከ 2009 አገልግለዋል።በዚህ ወቅትም ለወላጆች የገንዘብ ድጎማ የሚያሰገኘውን መርሃግብር በማነቃቃት እና

 Ursula von der Leyen CDU Verteidigungsministerin Deutschland (picture-alliance/dpa/K. Nietfeld)

 በመንግሥት ድጋፍ የህጻናት እንክብካቤ በሃገር አቀፍ ደረጃ እንዲዳረስ በማድረግ ይታወቃሉ።በሜርክል ሁለተኛ ካቢኔም በሙያቸው ሐኪም የሆኑት ፎን ዴር ላየን በጤና ሚኒስትርነት ለ4 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2017 የመጀመሪያዋ የጀርመን ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሆኑ። በተሾሙባቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን አዲስ ሃላፊነት በታላቅ ቁርጠኝነት በመወጣት እና ነባር መዋቅሮችንም ፈትሸው ለማስተካከል በሚያደርጉት ጥረት ይደነቃሉ።የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ታማኝ ፎን ዴር ላየን በሜርክል ዘንድም የካቢኔያቸው ምሶሶ ተደርገው ነው የሚቆጠሩት።በመከላከያ ሚኒስትርነታቸውም ጊዜ ሳይሰጡ የጀርመን ጦር ኃይሎችን ችግሮች አንድ በአንድ በመቅረፍ ይወደሳሉ።ከመካከላቸው በብዙ ጥረት የመከላከያ በጀት እንዲያድግ ማድረግ መቻላቸው እና የጀርመን ጦር ኃይል ቁጥር እንዳያድግ የተጣለበትን ገደብ ማስቀረታቸው በነዚህ ተግባራቶቻቸው የሚወደሱት ፎን ዴር ላየን የሚያስተቿቸው ጉዳዮችም አልጠፉም።የአንዳንድ ዋነኛ የጦር መሣሪያ ፕሮጀክቶች መዘግየት አንዱ ነው፣ መስሪያ ቤታቸው ለወታደራዊ አማካሪዎች ብዙ ክፍያ ፈጽሟል በመባል ተከሶም ጉዳዩ እየተጣራ ነው። በሥራቸው የተመሰገኑት እና ብዙ ልምድ እና ክህሎት ያላቸው ፎን ዴር ላየን  የአውሮጳ የመከላከያ ህብረት መዋቅርን በማዘጋጀትም ተሳትፈዋል።የአውሮጳ ህብረት ይበልጥ የተዋሀደ እንዲሆን እና ወደ ወደ ተባበሩት የአውሮጳ መንግሥታት ምሥረታ እንዲኬድ ጥሪ ያደረጉ ፖለቲከኛም ናቸው።ፎን ዴር ላየን የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ለመሆን ከ747ቱ የአውሮጳ ህብረት የህዝብ እንደራሴዎች ቢያንስ የ374ቱን ድምጽ ማግኘት አለባቸው።ከተመረጡ ስራቸውን የሚጀምሩት በጎርጎሮሳዊው ህዳር አንድ 2019 ነው።ከሚጠብቋቸው ዐበይት ጉዳዮች ውስጥም መቋጫ ይልተገኘለት የብሬግዚት ጉዳይ አንዱ እና ዋነኛው ይሆናል። 

ኂሩት መለሰ –አዜብ ታደሰ DW

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *