Samson Michailovich

ሳይኮሎጂስቶች ( ዛሬ ጽሁፍ የምጀምረው እንደ ቬሮኒካ ፈረንጅ በመጥቀስ ነው ) የመኪና አደጋ እና እንደ ኤች አይ ቪ ኤይድስ የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ የምንሆነው በተፈጥሯችን እንዲህ አይነቱ ሁነቶች ” እኔ ላይ አይደርስም” ብለን እንድናስብ የሚያደርገን ተፈጥሯዊ ዝንባሌ በተፈጥሯችን ስላለን ነው ይላሉ። ይህንን አመለካከት ለመቀየር የሰውን ልጅ በአደጋ እንደተከበበ እንዲረዳ መወትወት አንድ መፍትሄ አድርገው ይወስዳሉ። ለምሳሌ በሀገረ እንግሊዝ የመኪና አደጋን ለመቀነስ ከሚደረጉ ነገሮች አንዱ ሾፌሮች የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ሲወስዱ defensive driving የሚባለውን ሀሳብ አዕምሯቸው ውስጥ እንዲያኖሩ ማስቻል ነው። ይህ ማለት ባጭሩ መንገዱ ላይ ያሉት ሌሎች የሾቁ አሽከርካሪዎች እንደሆኑ ማመን ነው። እንዲህ ብሎ የሚያስብ ሰው ሾፌር ወንበር ከተቀመጠባት ቅጽበት ጀምሮ በጥንቃቄ ይነዳል ማለት ነው።

ዛሬ ከሀዋሳ የሰማሁት ታሪክ ሩዋንዳን አስታውሶኝ ነው ተው ይህ የመተራረድ ታሪክ ሩቅ አይምሰለን ፣ ደጃችን ቆሟል ለማለት የፈለግኩት። ባላምባራስ ታምሩ ( ስም ተቀይሯል ) ዕድሜ የጠገቡ የጃንሆይ ዘመን ሹም ናቸው። በዘመናቸው የግምጃ ቤት ሹም ፣ የትምህርት ሚ/ር ወኪል ሆነው በቀድሞው ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት አገልግለዋል። የሰውየው ልጆቹ አራቱ ዲላ የተቀሩት ሁለቱ ሀዋሳ ነው የተወለዱት። ባላምባራስ ደርግ ፊውዳል ብሎ አንገላቶ የፈታቸው ልጆቻቸውን ጥንቅቅ አድርገው ያሳደጉ አዛውንት ናቸው። ይህ ማለት ሰውየው በደርግም ኢህአዴግም ዘመን የሲዳማ ህዝብ ላይ አንዲት የአስተዳደር በደል አላደረሱም ማለት ነው። ባላምባራስም ልጆቻቸውም ሂዱ ቢባሉም የሚሄዱበት ክልል ፣ ሀገር የላቸውም። ሀዋሳ ከተማቸው ናት ሀዋሳ መቀበሪያቸው ነች !

ዛሬ ጠዋት የሆነው ጉዳይ ግን እጅግ የሚገርም ነው። ኤጄቶ የተባለው የወጣት ሚሊሻ ቡድን ገና በማለዳው የሰውየውን ቤት ያንኳኳል። እንደ ብዙው የሀዋሳ ነዋሪ ( መጤ ተብሎ የሚጠራው ) አዛውንቱ ከቀናት በፊት ወደ አዲስአበባ ‘ ለማንኛውም’ ብለው ለጥንቃቄ አምርተው ነበር። ወጣቶቹ የሰውየው ቤት ውስጥ ገብተው የሚፈልጉትን ሁሉ ወስደው ከጨረሱ በኃላ ሆቴላቸውን እሳት ካልጫርን ማለት ይጀምራሉ። የአካባቢው ሰው ተሰብስቦ ወጥቶ በእንብርክክ ኤጄቶን ሲለምን ውሎ ንብረቱ ከቃጠሎ ዳነ።

Image result for rwanda masaccar

ዛሬ ሀዋሳ ፣ ይርጋለም ፣ ለኩ ወዘተ የሰማናቸውን ታሪኮች ብናወራ ብዙ ጉድ ይሰማል። ትናንት በጎንደር አካባቢ የአማራና ቅማንት ግጭት ተብሎ የሆነው ነውር 1% ለአደባባይ አልበቃም። ቤኒሻንጉል አማሮች ሲፈናቀሉ የአካባቢው ሹማምንትና ሚሊሻዎች አይሱዙ ይዘው እየተከተሉ ከብትና ንብረት ይዘርፉ ነበር። ቡራዮ የሆነውም የዘር ፍጅቱ ቀን የጎደለ ዕለት መዲናይቱ ለመግባት ደቂቃዎች እንደማይፈጅበት ማሳያ ነው። ተጨካክነናል ፣ እርስ በእርስ ተጠላልተናል ወደ አርማጌዶናዊ ዕልቂት ለመግባት ትንሽ ክብሪትና ክፍተት ብቻ ነው የሚበቃን። ሩዋንዳ ሩቅ አይምሰለን ፣ ወጣቶቻችን ከቴክኖሎጂ ይልቅ በአካባቢያቸው ያሉትን ” መጤዎች ” ነው ጠንቅቀው የሚዬውቁት። አብሮ ከመኖር ይልቅ መቼ እነዚህን ” መጤዎች ” ወደ መጡበት እንደሚሸኙ ነው የሚናፍቁት። ምሁራኖቻችን ከምክርና ተግሳጽ ይልቅ ወጣቶቻችንን ቁጣ ፣ ብሶትና የተጠቂነት ፊደል ነው የሚያስቆጥሯቸው።

ሩዋንዳ ሩቅ አይምስለን !

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *