በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሐዋሳና የሲዳማ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከሐምሌ 11/2011 አንስቶ አለመረጋጋት መከሰቱ ይታወሳል፡፡ በሲዳማ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለአብመድ በስልክ እንዳስታወቁትም በተከሰተው የሠላም እጦት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ ዘረፋም ተፈጽሟል፡፡

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ተጠባባቂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ለአብመድ እንዳስታወቁት ደግሞ አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት ተፈጥሮ ሐዋሳ አካባቢ ሰው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እየገባ ነው፤ ‹‹በተለይም ትናንት እና ዛሬ የተፈጠረ የፀጥታ ችግር የለም፡፡ የፀጥታ ኃይሉ ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር በመሆን ሌት ተቀን ጠንክሮ እየሠራ ነው፤ ሐዋሳ ሠላም ነው፡፡ ቀሪው ሥራ ከሕዝብ ጋር ሆኖ ወንጀለኞችን ይዞ ወደ ሕግ ማቅረብ ነው›› ብለዋል፡፡

አቶ አንድነት እንደገለጹት ከይርጋለም አንስቶ ሞሮቱ፣ ጭኮ፣ ለኩ፣ ተፈሪ ኬላ፣ ወንዶገነት፣ አለታ ወንዶ እስከ ሀገረ ሠላም ድረስ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ አንጻራዊ ሠላም ሰፍኗል፡፡ ሠራዊቱ አካባቢውን በመቆጣጠሩ ‹‹ነውጠኛ ቡድኑ ተበትኗል›› ያሉት አቶ አንድነት ‹‹ከትናንት ጀምሮ ሀገረ ሠላም አካባቢ ችግሩ ወደ ገጠር መስፋፋት ታይቶበት ነበር፤ ነገር ግን ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ችግሩን ለመቀነስ ተሠርቷል፤ ሠራዊቱም አብሮ እያረጋጋው ነው፡፡ የፌዴራልና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመቀናጀትም የአካባቢውን ሠላም ወደ ነበረበት ለመመለስ እየጣሩ ነው፡፡ ከትናንት ጀምሮ በእነዚህ አካባቢዎች ዝርፊያም ሆነ ግጭት አልተስተዋለም›› ብለዋል፡፡

ከትናንት ጀምሮ የተስተዋለው መረጋጋት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከክልልም ከዞንም መሪዎች አካባቢዎቹን ለማረጋጋት እየሠሩ መሆኑንም ነው ያመለከቱት፡፡
‹‹አረቤጎና ወረዳ ውስጥ ትናንት ከሰዓት በኋላ የተወሰኑ ቤቶች ላይ ዝርፊያ፣ ጥቃትና ዕቃዎችን ማቃጠል ተሞክሯል፡፡ የአካባቢው ኅብረተሰብ በከፍኛ ሁኔታ ለመከላከል ጥሯል፤ ፖሊስም ሞክሯል ግን ከአቅሙ በላይ ሆኖበት ጥቃቶች ደርሰዋል›› ነው ያሉት፡፡ ወደ ምሽት 1፡00 አካባቢ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመግባቱ ጥቃቱ መቆሙን ያስታወቁት አቶ አንድት ‹‹ዘራፊ ቡድን›› የተባለው ኃይልም ሠራዊቱ ሲገባ እንደተበተነ አስታውቀዋል፡፡

‹‹አነሳሱ የክልል ጥያቄው በምንፈልገው ጊዜ አልተመለሰም፤ ስለዚህም ሐምሌ 11 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ ክልልነትን እናውጃለን፣ የሕዝበ ውሳኔ ቀንም በይፋ አልተገለጸም›› በሚል መሆኑን ያመለከቱት አቶ አንድነት መንግሥት በቅርቡ መግለጫ ቢሰጥም ምላሹን ያልተቀበሉ ቡድኖች ወደ ብጥብጥ እንደገቡ አስረድተዋል፡፡

ጥቃቱ የብሔር መልክ የያዘ ስለመሆኑ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽም ‹‹ግድያውና ጥቃቱ ብሔርን መሠረት ያደረገ ስለመሆኑ ዝርዝር ግምገማ ማድረግን ይጠይቃል፤ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የአካባቢውም የሌላ ብሔር ተወላጆችም ሕይወት አልፏል፤ ዝርፊያው ግን ከአካባቢው ተወላጆች ውጭ ባሉ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ላይ ነው የተፈጸመው›› ብለዋል፡፡

የግጭት ሥጋት መኖሩን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች እንደነበሩና ለምን በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ መከላከል እንዳልተቻለ የተጠየቁት አቶ አንድነት ‹‹ጥያቄው ሲጠየቅ ቆይቶ ግልጽ መረጃ የተሰጠው በጣም በተጣበበ ጊዜ ውስጥ ነው፤ የተሰጠው ምላሽና ዝርዝር መግለጫ ወደ ሕዝቡ ከመድረሱ በፊት በሕገ ወጥ መንገድ ‹ክልል መሥርተናል› የሚል አዋጅ ለማወጅ የተዘጋጀው ቡድን ሐዋሳን ማዕከል አድርጎ እንደሚንቀሳቀስም ተጠብቆ ነበር›› ብለዋል፡፡ የዚህን ቡድን እንቅስቃሴ የሚገታና የከተማዋን ሠላም መጠበቅ የሚችል የፀጥታ ኃይል በሐዋሳ ዝግጁ መደረጉንና በሐዋሳ ላመድረስ ታቅዶ የነበረውን ጥፋት ማክሸፍ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

ነገር ግን ቡድኑ ሐዋሳ ላይ የጎላ ችግር መፍጠር እንደማይችል ሲያረጋግጥ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መበተኑንና ያልተጠበቀ ጉዳት ማድረሱን ነው የገለፁት፡፡ ‹‹ሐዋሳ ላይ የጥፋት ዕቅዱ የከሸፈበት ኃይል አለታ ወንዶ፣ ይርጋለምና ሀገረ ሠላም አካባቢ መንገድ በመዝጋትና ሠራዊቱ እንዳይደርስ በማድረግ ጥፋት ፈፅሟል›› ብለዋል፡፡ ሠራዊቱ ገብቶም የነውጥ ኃይሉ ቁጥር ከፍተኛ ስለነበር በፍጥነት ለመቆጣጠር አለመቻሉን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ግጭት ለማስቆም ነው ሲሠራ የነበረው፡፡ በከተማም በገጠርም ሕዝቡን በማወያዬት ወዥንብሮችን ለማምከን እየሠራን ነው፡፡ ሕዝቡ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ሠላምና ሕግ የማስከበሩ አካል እንዲሆን እየሠራን ነው›› ያሉት ተጠባባቂ ቢሮ ኃላፊው በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታትና አስተማማኝ ሠላም ለማስፈን እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በከተማም በገጠርም ሕዝቡን በማወያዬት ችግሩ እንዲፈታና ሕዝቡ በትክክለኛ የመገናኛ ብዙኃን በሚተላለፉና በሕዝባዊ መድረኮች በሚሰጡ መረጃዎች እየተመሠረተ ሠላሙን እንዲጠብቅ፤ ለአሉቧልታዎችም ጆሮ እንዳይሰጥ አሳበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 14/2011 ዓ.ም (አብመድ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *