መንግስት ለመግልበጥ ውስጥ ውስጡን የተዘረጋው መረብ መበጠሱን የዛጎል የመረጃ ምንጮች አመለከቱ። እቅዱ የቆየ ቢሆንም ተግባራዊ ለማድርግ የተፈለገው የለውጡን መሪዎች ተቀባይነት ካመናመኑ በሁዋላ ሲሆን፣ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ የህዝቡን ንቃተ ህሊናና ባህል ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በከፍተኛ በጀት፣ በባለሙያዎችና በማዕከላዊ እዝ ደረጃ የተደራጀ የማህበራዊ ሚዲያ ሰራዊት ትልቁን ሚና እንደተጫወተ ታውቋል።

የመረጃው ምንጮች እንዳሉት ከፌደራል መንግስት ቀጥሎ ከፍተኛ ሰራዊትና የትጥቅ አቅም ያደራጀው ቡድን መንግስት አመኔታ እንዳይኖረው ባሰማራው የማህበራዊ ሚዲያ ሰራዊት አማካይነት ውጤታማ ስራ መስራቱን ግምግሟል። በግምገማውም ጠቅላይ ሚንስትር አብይን ለይቶ መምታት የሚለው ስትራቴጂ ግቡን መቷል። ለዚሁም በዋናነት የዜጎች መፈናቀል፣ በተለይም በሚፈለገው መልኩ የትጠለፈው የአዲስ አበባ የባለቤትነት አጀንዳ፣ የለገጣፎ ህገወጥ ግንባታ አፈራረስና ኦሮሞ መምራት አይችልም የሚለው ስልት ከሚፈለገው በላይ ሰርጿል። የለውጡ መሪዎች የገነቡት የህዝብ ድጋፍ እንዲተን ተደርጓል።

ዳግም ወደ ስልጣን ለመምጣት እየሰራ ያለው ቡድን ሃሳቡን እውን ለማድረግ ቢነሳ  የሚገዳደረው ሃይል የመከላከያ ሰራዊት ብቻ እንደሆነ ገምግሞ የመከላከያው ሰራዊት ውስጥ ሰርጎ የመግባት ሰፊ ስራ ሰርቷል። ወዳጅ አገራትና ታማኝ የሰራዊት አመራሮች ሴራውን እንዳከሸፉት የገለጹት የመረጃው ሰዎች ” ውጥኑ ውስን የብሄር ድርጅቶችን እንዲያካትት ተደርጎ የተሰራ ነበር” ሲሉ ገልጸዋል። የብሄር ድርጅት ያሏቸውን አልዘረዘሩም።

ከመከላከያ ሰራዊት ኤታማዦርሹም ጀነራል ሰአረ ግድያ ጋር ጉዳይ ግንኙነት ይኖረው እንደሆነ ለተጠየቁት ዝምታን የመረጡት የዛጎል ምንጮች፣ ሰሞኑንን የመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከፍተኛ መኮንኖች በውስጣቸው ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለና ለሕገመንግስቱ ታማኝ ሆነው እንደሚሰሩ በተደጋጋሚ ያስታውቁት በምክንያት መሆኑንን ግን አልሸሸጉም።

የአሜሪካ የጦር መኮንኖች በስልጠና ስም ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ለዚሁ ዓላማ ይሁን አይሁን ምላሽ ያልሰጡት የዜናው ሰዎች፣ ህዝብ ” እረኛውን ግደል፣ መንጋው ይበተናል” የሚል መርህ ያዘለውን አገሪቱን የመበተን ሴራ በማስተዋል ቢመረምር እንደሚሻል ግን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባህር ዳር የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ ድንገተኛ መግለጫ ሲሠጡ አዲስ አበባ ዙሪያ ሁሉንም ተቆጣጥረናል ችግር የለም ማለታቸው ይታወሳል። እሳቸው ዝርዝሩን ባይናገሩም የድሮው አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው የድህንነት ቢሮ አዲስ አበባ ላይ የታቀደውን ሴራ ሲያቀነባበር እጃቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁ መታኮስ መርጠው መመታታቸውን ውስጥ አዋቂዎቹ እንደማሳያ ገልጸዋል።

Related stories   ኢሰመኮ ኢሰመኮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ቡድን አሰማራ፤ የእስረኞች አያያዝ ላይ ምስክርነቱን ይፋ አደረገ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *