የሴራ ፖለቲካ ቁጥራቸው የማይናቅ ሀገራትን ፖለቲከኞች ቆርጥሞ የበላ በሕዝብና በዴሞክራሲ ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው፡፡ ሴራና የሴራ ፖለቲካ ጊዜ ዘመንና ዕድሜው ረዥም መሆኑ ይታመናል። የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ወቅት ጀምሮ የነበረና የኖረ ዛሬም ድረስ የቀጠለ ነው፡፡ ሀገራት በሀገራት፤ መንግሥታት በመንግሥታት፤ የፖ ለቲካ ቡድኖች በፖለቲካ ቡድኖች፤ ግለሰቦች በግለሰቦች ላይ በሴራ እየተነሱ የሴራ ፖለቲካን እያራመዱ ሲጠፋፉ ሲተራረዱ ሲበላሉ ኖረዋል።

የሴራ ዋና ምንጩ ግልጽነት አለመኖር፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ተንኮል፣ ይበልጠኛል ወይንም ይገዳደረኛል ብሎ የሚያስበውን ግለሰብ ቡድን ወይም ድርጅት ጠልፎ የሚጥልበት ተንኮልና ሴራ ነው፡፡ የሴራ ፖለቲካ ከድሮ እስከ ዘንድሮ ከጫንቃችን አልወረደም፡፡ ሀገርና ትውልድ ገዳይ ነው የሴራ ፖለቲካ፡፡ በሀገራችን ከጥንት ጀምሮ በተለያየ መልኩ ሲከሰት ከፍተኛ ኪሳራና ዋጋ ሲያስከፍለን ለመኖሩ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት እንደሚቻል የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ዛሬም ቢሆን የሴራ ፖለቲካ መልኩን እየቀያየረ መከሰቱ አልቀረም፡፡ ሁኔታው ባሰበት እንጂ ለውጥ አልመጣም ሲሉ ምሁራኑ ይሞግታሉ፡፡ የዛሬው ትውልድም ከሴራ ፖለቲካ ተግባር እና ዳፋ አልራቀም፤ ከበሽታውም «አልተላቀቅንም» ሲሉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በቀደመው ትውልድ ወይንም በያኔው ትውልድ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተበላሉበትና የተጠፋፉበት ታሪክ የሴራ ፖለቲካ ልክፍት ነው።

በሴራ ፖለቲካ ምንነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሁለት ታዋቂ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሚሉት አላቸው፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የኤሽያ ጥናት ኃላፊ ዶ/ር ጌታቸው ካሳ የሴራ ፖለቲካ ምንድነው? በሚለው ነጥብ ዙሪያ አነጋግረናቸዋል፡፡

የሴራ ፖለቲካ ምንድን ነው?

የሴራ ፖለቲካን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው ሴራንና ፖለቲካን ነጣጥለው ይመለከቱታል፡፡ የሴራ አስተሳሰብ ማለት ማስረጃ ሳይኖር በደንብ ሳይጠና የተወሰነ ግምታዊ ሀሳብ አምጥተህ መሬት ላይ የሚካሄደውን ነገር በዚያ መግለጽ ማለት ነው። ማሰብ መተንተን ብዙ ያስቸግራል። ሊያምም ይችላል፡፡ ስለዚህ ምንም ሳይጨናነቁ ዝምብሎ እንዲህ ሆኖ እኮ ነው፤ እንዲያ ነው፤ እንዲህ ነበር እኮ፤ እንዲህ ነው በሚል ሴራ ውስጥ ገብቶ ታሪክን የፖለቲካ ሁኔታን በሴራ ላይ ተመስርተህ ፖለቲካን ማስረዳት ማለት ነው። ሴራ ግን ዘለቄታ የሌለው ተኖ የሚጠፋ ነው። ከሴራ ይልቅ በደንብ ነገሮችን መረጃዎችንና ማስረጃዎችን መርምሮ መንቀሳቀሱ የተሻለ ነው ይላሉ ዶ/ር ዳኛቸው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የኤሽያ ጥናት ኃላፊ ዶ/ር ጌታቸው ካሳ በበኩላቸው የሴራ ፖለቲካን እንደሚከተለው ይገልጹታል፡፡ የሴራ ፖለቲካ ማለት ግልጽነት የሌለው ፖለቲካ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ተቀናቃኝ የሆኑ ሁለት የሚገዳደሩ ኃይሎች ካሉ ሀገራዊ በሆነው ነገር ላይ አንዱ ሌላውን የሚጠረጥርበት ማለት ነው።

ምክንያቱም አንዱን ከእኛ ባሕልም አንጻር መውሰድ ይቻላል፡፡ የእኛ ባሕል ምስጢር የሚለው ነገር አለው፡፡ ይሄ ምስጢር ማለት ብዙ ጊዜ ግልጽነት የሌለው ነገር ማለት ነው። ግልጽነት ያለመነጋገሩ ባሕል ስላለ በተለይ ምሁሩ የፖለቲካ ልሂቁና ተማረ የምትለው አካባቢ ችግሩ ነፍስ ዘርቶ ይታያል፡፡

«እኔን ጠልፎ ይጥለኛል» የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ የእምነት ማጣት (ላክ ኦፍ ትረስት)። ምንጊዜም አንድ መንግሥት ሀገርና ሕዝብን ሊመራ የሚችለው ሕዝብ በመንግሥት ወይንም በልሂቃኑ ላይ እምነት ሲኖረው ብቻ ነው። ወይንም ደግሞ መንግሥት በሕዝቡ ላይ እምነት ሲኖረው ነው መምራት እና መመራት የሚቻለው። በዚህ መካከል ያሉት የፖለቲካ ልሂቃን ማድረግ የነበረባቸው እምነትን የሚያመጡ ነገሮችን፤ ሀገር ያላትን ምስል መገንባት የሚታመንበትን ነገር የሚያስተምሩ ዓይነት ሰዎች መሆን ይገባቸዋል፤ ምሁሩ ግን ተመልካች ሆኗል፡፡ ይሄ ሚናው አይደለም፡፡

የሴራ ፖለቲካ በኢትዮጵያ

የሤራ ፖለቲካን በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እንዴት ያዩታል? ለሚለው ጥያቄ ብዙ ሰው ሴራውን ሊለቅ አይፈልግም ይላሉ። ቀጥለውም በኢትዮጵያ ውስጥ ይጎድላል ያሏቸውን ሁለት ነገሮች ይገልጻሉ። አንደኛው ክፍት አእምሮ (ኦፐን ማይንድድነስ) ሲሆን ሁለተኛው በማስረጃ ላይ የሚመሰረት (ኢቪደንሸሪ) የሚሉት ነው፡፡

ክፍት አዕምሮ በሚኖርህ ጊዜ የራስህን ሀሳብ መልሰህ እንድትፈትሽ ይረዳሀል፡፡ «አይ እኔ አንድ ጊዜ ይህን አቋም ይዣለሁ ከዚህ ወዲህ የፈለገው ማስረጃ ቢመጣ አልነቃነቅም» ማለት ትክክል አይሆንም፡፡ ሴራ አንዴ ከገባ በኋላ ያንን ማላቀቅ ከባድ ነው፡፡ የፈለከውን ዓይነት ማስረጃ ለሴረኛው ብታመጣ ሌላ እንደገና ሌላ ሴራ ጎንጉኖ ያንን ያፈርስብሀል እንጂ ክፍት አእምሮ ሆኖ ነገሮችን ማስተካከል አይፈልግም ሲሉ ዶክተር ዳኛቸው ያስረዳሉ፡፡

ሴራ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ገኖ የኖረ ነው ለሚለውም መልስ አላቸው ዶ/ር ዳኛቸው፡፡ ሴራ በገለጻ ደረጃ አንድ ነገር ነው፡፡ ሴራ ደግሞ ከኋላ እየተሻረክ በፊት ለፊት ነገሮችን ከማቅረብ በቡድን እየተቧደንክ ፖለቲካን መግፋት ነው፡፡ ይሄ በጣም አደጋ ነው፡፡ ሴራ የሚያስከትለው መጠፋፋት ነው።

ዶ/ር ዳኛቸው ‹ዘ -ፕሪንስ› በተባለ መጽሐፉ ማክያቬሊ የሴራ ፖለቲካን መሠረት የጣለ ነው የሚባለውን ሀሳብ አይቀበሉትም፡፡ ማክያቬሊ ስለሴራ አይደለም ያወራው፡፡ ማክያቬሊ ፖለቲካና ሞራልን እንለይ ነው የሚለው፡፡ «ሪፐብሊኩን ማጽናት ሪፐብሊኩን መጠበቅ ኃላፊነት አለብህ ፤ የምትዳኘው ሪፐብሊኩን በመጠበቅህ ነው እንጂ ሰው በመግደልህ በማጥፋትህ አይደለም፡፡ ለዚህ ስትል ‹ክርስትያን ሞራሊቲ› ሌላ ያደክበትን ሞራል ሽረህ እንደምንም ብለህ ፖለቲካህን መግፋት አለብህ» ነው የሚለው፡፡

ማክያቬሊ ተናግሮ ጨርሷል ነው የሚሉት ዶክተር ዳኛቸው፡፡ «እኔ እንደነ ሶቅራጥስና ጂሰስ ክራይስት ከጨለማ ወደብርሃን አወጣችኋለሁ አልልም፡፡ እንዴት ግን በጨለማ ውስጥ መኖር እንደምትችሉ አስተምራችኋለሁ ነው ያለው፡፡ ይሄ ዓለም ጨለማ ነው፡፡ ዋሻ ነው» ነው ያለው ክርስቶስ፡፡ ሁሉም ከኋላው ጩቤውን ይዟል። እንዴት መኖር እንደምትችሉ ላስተምራችሁ እንጂ ወደ ብርሃን እወስዳችኋለሁ አልልም ብሏል ሲሉ ስለማክያቬሊ ገልጸዋል፡፡

የሴራ ፖለቲካና …

የኃይል አሰላለፍ

የሴራ ፖለቲካንና አሁን በሀገራችን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታና መፍትሄ አስመልክተው ዶ/ር ዳኛቸው የሚሉት አለ፡፡ መፍትሄ መስጠት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁን የመነጋገሪያ ጊዜ ነው የሚል አቋም አላቸው፡፡

«አማራ ክልል ውስጥ ችግር ተፈጥሯል፡፡ ዝም ብለን ጣት ከምንቀሳሰር ተነጋግረን ከዚህ ችግር ተጠናክረን ወጥተን የክልሉ ሕዝብ ለክልሉ ብሎም ለኢትዮጵያ ማበርከት የሚገባውን ድርሻ እንዲጫወት ማድረግ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ። ይህን ለማድረግ ሁሉም ቤቱን ማስተካከል፤ መወያየት አለበት፡፡ መገፈታተር የለበትም፡፡ በመጀመሪያ መገዳደሉን መተው፡፡

«እኔ የምለው በእንደዚህ ዓይነት አካሄድ መሄድ አለብን ባይ ነኝ፡፡ የአማራ ክልል ሕዝብ በሳል ነው። መሸማገል ፤ መምከርም ያውቅበታል፡፡ የአማራ ባሕል የምክክር ቤት ነው፡፡ እነዚህን እሴቶቻችንን ተጠቅመን ወደ በጎ ነገር መሄድ ነው የሚገባን» ሲሉ ዶክተሩ ይመክራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የሴራ ፖለቲካና ጽንፍ የወጣ የኃይል አሰላለፍ በግልፅ ይታያል፡፡ ለኢትዮጵያ የትኛውም ዓይነት ጽንፈኛ አካሄድ ምንጊዜም አይበጃትም የሚሉት ዶክተር ዳኛቸው ማዕከላዊነት ይበጃል ነው የሚሉት፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ ኢትዮጵያን የሚመለከት ሥራ ስትሰራም ሆነ ስታቅድ ለአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችንም ታሳቢ ማድረግ ይገባል፡፡ የአማራን ጥቅም ብቻ ነው የምጠብቀው በምትልበት ወቅት የሌላውን ጥቅም ታጎድላለህ ይህ ደግሞ ዘላቂ አይሆንም፤ እንዲያውም ለግጭት መንስኤ ይሆናል፡፡

«የአማራውን ጥቅም አስከብራለሁ ስትል የሌላውንም ጥቅም ስታስከብር ነው አላማህን የምታሳካው፡፡ ተነጣጥሎ የሚሄድ አይደለም። የአሉት መሪዎች እየተመካከሩ እኛም እንደ አቅማችን እየመከርናቸው ወደ መልካም መንገድ እንሄዳለን የሚል ተስፋ አለኝ» ብለዋል ዶ/ር ዳኛቸው፡፡

የምሁራንና የወጣቱ የቤት ሥራ

ዶ/ር ጌታቸው ካሳ ሁኔታውን ሰፋ አድርገው አብራርተዋል፡፡ ጽንፍ የያዘው ሌላው ምሁር ደግሞ መገንጠል ነው የሚሰብከው። በአፍሪካ ቀንድ በሙሉ ከሄድክ የጎሳውን ታሪክ የማጉላት ታሪክ እንጂ ሀገርን እንዴት አድርገን እንፈጥራለን የሚለው ላይ በምሁሩ መካከል ስምምነት አልነበረም፡፡ ስለዚህ ርዕዮተ ዓለምም ብትለው አርቲፊሻል ጉዳይ ነው፡፡ ከጎሳ አስተሳሰብ አልወጣም፤ አልመጠቀም፡፡

ዓለም ዓቀፋዊ የሆነ (ግሎባል) አስተሳሰብ፤ ከባቢያዊ የሆነ ሁኔታ ሀገራዊ አንድነትን የሚያስብ አልነበረም፡፡ የጻፈው ሁሉ ጽንፍ የወጣ ነው፡፡ ምሁሩ ወይ የአማራውን ወይ የኦሮሞውን ወይ የትግሬውን ታሪክ ነው የሚያወራው። የመገንጠል ታሪክ ነው የሚያ ወራው፡፡ መገነጣጠል፡፡ ጽሑፎቹን ሁሉ ማየት ትችላላህ።

«በጋራ የሚያቆመን ነገር ላይ ሳይሆን በሚለያየን ነገር ላይ ነው ሲጽፉ ሲሰሩ የኖሩት። ሀገርን እንዴት አድርገን እንፍጠራት የሚለው ላይ ምሁሩም መካከል ስምምነት አልነበረም። የለም። ምሁሩ በአብዛኛው አንድነትን የሚያመጣ ነገር ላይ አልጻፈም፡፡ አልሰበከም። ይህቺ ሀገር ለሁላችንም ትበቃለች በሚል አይደለም የሰሩት ሲሉ» ዶ/ሩ ይወቅሳሉ፡፡

ወጣቱን ትውልድ በተመለከተ ዶ/ር ዳኛቸው የሚሉት አላቸው፡፡ ወጣትነት በጣም አስቸጋሪ ዘመን ነው፡፡ ወጣቱ ምክር ማዳመጥ አለበት፤ መጠየቁን የፖለቲካ ንቃቱን ይቀንስ አይባልም። ነገር ግን በጣም ረጋ ማለት አለበት። መረጋጋት አለበት። ሽማግሌዎች የሚሉትን መስማት፤ ልንሳሳት እንችላለን ብሎም እንዲያስብ ነው የሚፈለገው፡፡ መሳሳት አለ፤ ይኖራል የሚል ብሂል ማሳደግ አለበት እንጂ «እኔ ልክ ነኝ ፤ያለቀ ነገር ነው» የሚለው ትክክል አይደለም፡፡ከዚህ መውጣት አለበት፡፡

ለምሁራን ብቻ

ምሁራን ለሁሉም የጋራ በሆኑ ነገሮች ላይ መስራት ነበር የሚገባቸው፡፡ አሁን ግን የሚታየው ውድድር ነው፡ ፡ምስጢር ይበዛል፤ግ ልጽነት የለም። መጠላለፍ አለ፡፡ ስለዚህ እርስ በእርስ፤ በቡድንም ውስጥ ያለመተማመን አለ። ይሄ መሠረቱ ምንድነው ካልን በሕዝብና በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል ያለው ወጥ ያልሆነ አስተሳሰብ ወይም ፍትሀዊ የሆነ አስተሳሰብ የለም ብሎ ለመናገር ብዙ ማሳያዎች አሉ ይላሉ ዶክተር ጌታቸው፡፡

ማሸነፍ ያለብህ ግልጽ በሆነ አጀንዳ ላይ ተከራክረህ ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ምሁር የዜሮ ድምር ውጤት ውስጥ ስላለ ብዙ ጊዜ የፖለቲካ አወቃቀሩም የዜሮ ድምር ፖለቲካ ይሆናል፡፡ እስከመጨረሻው ሄደህ አጥፍተኸው ነው ሥልጣን የምትወስደው፡፡ ይሄ በሕዝቡ፤ በጎሳዎችም ሆነ በየደረጃው ባለው ፖለቲካና ፖለቲከኞች ውስጥ ጎልቶ ይታያል ይላሉ ዶ/ር ጌታቸው፡፡

አብዛኛው የፖለቲካ አመራሩ በመጠፋፋት ነው የሚያምነው፡፡ አንዱ ሌላውን በመጣል እንጂ በማሳመን የጋራ ግብ ኖሮአቸው ላለመስማማት መስማማት ስለሌለ ነው ፖለቲካዊ ሴራ ሁልጊዜም የሚኖረው፡፡ የግልጽነት አለመኖርና ማጣት ነው የሴራ ፖለቲካ በትክክል ይህን የመሰለ ገጽታ እንዲኖረው ያስቻለው፡፡ ለሴራ መኖር የሴረኞች መኖር አንዱ ምክንያት ነው፡፡

እንደ ዶ/ር ጌታቸው ማብራሪያ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ከቀድሞ ዘመናት ጀምሮ ምሁሩና ተማሪው ስርነቀል አብዮት ለማምጣት ታግሏል፡፡ በሴራ ፖለቲካ ተጠላልፎ መክኖ መቅረቱን በተመለከተ ዶ/ሩ የራሳቸውን አተያይ ይገልጻሉ፡፡ የአፍሪካ ቀንድ በተለይ ምሁራንን በአጠቃላይ ከወሰድክ ከትርክት አልወጡም፡፡ የማያባራ መሠረት የሌለው ትርክት፡፡

አፈታሪክን ይሄ ነገር ትክክለኛ ታሪክ ላይሆን ይችላል ብለው እሱን አጥርተው አላጠሩም። ጥላቻ አለ፡፡ (ፕሬጂዱሲስ) አንዱ ለሌላው ያለውን አመለካከት ጽንፋዊ የሆነውን ይሄ ጠላቴ ነው ፤ይሄኛው እንደዚህ ነው፤ ዶሚኔት አድርጎኛል የሚባለው ትርክት ስላለ ምሁሩ ከዚህ ትርክት አልወጣም፤ ዛሬም ተቀፍድዶ እንደተያዘ ነው ይላሉ ዶክተር ጌታቸው፡፡

ርዕዮተዓለሙ ልባስ ዓይነት ነገር ነው። መሸፈኛ፡፡ ያለውን ትክክለኛ አቋም ከዚህ በላይ ልቆ ያሰበበት ጊዜ የለም፡፡ አንዱ ሌላውን በማጥፋት የሥልጣንና የራሱን የጥቅም የሚያስከብር ቡድን ማምጣት ላይ ስለነበረ ሴራው ያ ችግር አለ፡፡ አሁንም መጠየቅ የሚገባው ትልቁ ነገር ምንድነው ምሁሩ ከጎሳ አስተሳሰብ አልወጣም፡፡ የ1960ዎቹም ትውልድ ሀገራዊ አንድነት የሚለው ጽንፍ ይዞ የሄደው የኢትዮጵያ አንድነት ወይ ሞት የሚለውም አስተሳሰብና ቡድን አለ፡፡

ይሄም አግባብ አይደለም የሚሉት ዶ/ር ጌታቸው እሱን ደግሞ እንዴት አድርጎ እንደሚ ያመጣ ያስረዳበት ጊዜ የለም፡፡ እንዴት አድርገን ነውአንድነታችንን የምናመጣው በሚለው ላይ አልተ ሰራበትም፡፡ ከታች ከባሕላችን ጀም ረን ሁሉንም የማቀፉን ሌላውን የማግለሉን ነገር በማቆም እንዴት ነው ሀገራዊ አንድነት የም ናመጣው በሚለው አስተሳሰብና የሀገር ግንባታ ላይ ምንም ጥሩ ነገር አልነበረውም ሲሉ ዶ/ር ጌታቸው ያስረዳሉ፡፡

መፍትሄው ምንድነው?

«በእኛ ዘመን እኛ ልንሳሳት እንችላለን ብለን ስላላልን ጥፋት ደርሷል፡፡ አሁን ያለው ወጣት የእኛን የ1960ዎቹን ያንን እንዳይደግም ነው የምለው፡፡ ቀኖናዊ ነበርን፡፡ ዶግማቲክ ነበርን። መሀላችን ልንሳሳት እንችላለን ይሄን ነገር እስቲ እንፈትሸው አላልንም ነበር፤ በዚህም ብዙ ጥፋት መጣ፡፡ መግባባት፡፡ መደማመጥ። የራስን ሀሳብ ደግሞ ደጋግሞ መፈተሽ ተገቢ ነው» ሲሉ ዶክተር ዳኛቸው ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ዶ/ር ጌታቸው የሚሉት አላቸው፡፡ አሁን ካለው በላይ የሚሄድ የሚሻገር የገዘፈ ሀገራዊ ራእይ ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው ምሁሩ ከኋላቀር የአስተሳሰብ ባርነት ነፃ መውጣት አለበት፡፡ ፖለቲካውን የሚያርቀው (ማረቅ) የሚችለው የሚገባውም እኮ እሱ ነበር፡፡ በፊት የነበረውን እስከአሁን ያለውንና የነበረውን ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታና ቀውስ በመፍጠር ረገድ ምሁሩ ነው አስተዋጽኦ ያደረገው፡፡

ምሁሩ ኅብረተሰቡን ለመቅረጽ አልበቃም። ምሁሩ ከኅብረተሰቡ በአስተሳሰብ ቀድሞ ልቆ መጥቆ አልሄደም፡፡ ልቆም ሄደ ካልከው የያዘው መለያ ርዕዮተዓለም ግዙፍና ሀገርን ወደትልቅነት የሚያሻግር አይደለም፡፡ ከትንንሽ አስተሳሰብ አልወጣም፡፡ ስለዚህ ሀገራዊ ፖለቲካችንን ለማረቅ ከተፈለገ የፖለቲካ ልሂቁና ተማረ የሚባለው ኃይል ሰፋ አድርጎ የሚያስብና ሕዝቡን የሚያቀራርብ ከዚያ በላይ መማር ያለበት እስከአሁን የሄድንበት አንዱ ሌላውን አቅፎ የኖረበትን ፖለቲካ ማምጣት አለበት። ሁለተኛው በውይይት ማመን ነው። በውይይት የማመኑ ነገር ታች ስንወርድ ኅብረተሰቡ አካባቢ አለ፡፡

«በእኛ ሀገር ስትወስደው አንዱ እንዴት አድርጎ የአንዱን ሀሳብ እንደሚጥል እንጂ የሚያሰላው ከእሱ ውስጥ የሚጠቅሙ ሀሳቦች ስላሉ ለጊዜው ባንስማማ እንኳን ተስማምተን እንሂድ የሚል የላቀ አስተሳሰብ የለውም ምሁሩ፡፡ አሁን እንዳልኩህ አንዱ ስለ ሌላው ለማብራራት ከዚያ በላይ ሄዶ ያንን ለመገመት የሚያስችለውን ለማድረግ በጽሑፍ በጥናት ምርምር አድርጌ በሚል ሳይሆን ከዚያ በላይ የሚሄድና አንዱ ለሌላው ያለውን ጥርጣሬ ጥላቻ አንዱ በሌላው ላይ ያለውን የጠላትነት መንፈስ ማለዘብ መቻል ነበረበት፤ ይህ አልሆነም፤ አልለዘበም፡፡ ልዩነቱን ነው ሲያጎላ ሲያገዝፍ የመጣው፡፡ የኖረው፡፡

የሚጠናው ጥናት ውድቀት ላይ እና ለምን ኅብረተሰቡ ተለያየ የሚል ላይ ነው እንጂ የሚቀራረብበት ነገር አለ ወይ? የሚለው ላይ አንድም አልተሰራም ሲሉ ዶክተር ጌታቸው ይወቅሳሉ፡፡ ይሄ ችግር ሁሉ ሊፈታ ይገባል። የሴራ ፖለቲካ ለሀገርና ለሕዝብ ውድቀት እንጂ ትሩፋት የለውም ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011

ወንድወሰን መኮንን

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *