May 9, 2021

ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

በአማራና በሶማሊ ሕዝብ መካከል የተዘራው የፈጠራ ትርክት ማቅ ለብሶ ተቀበረ!!

በአማራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረውና በፈጠራ ሲሰራጭ የነበረው አፍራሽ ቅስቀሳ በሶማሌና በአማራ ክልል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማቅ ለብሶ መቀበሩን ዝጅቱን የተከታተሉ ገለጹ። ለፖለቲካ ትርፍ ሳይሆን የፈጠራ ትርክት በመሆኑ አማራው ላይ የተነዛውን የሃስት ዘመቻ እንደማይቀበሉት፣ እሳቸው በሚመሩት ክልል ሁሉም ብሄረሰብ በስላም መኖር ካልቻሉ ስርዓቱ አፓርታይድ መሆኑንን ያመለክቱት አቶ ሙስጣፋን ተከትለው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ላቀ አያሌው የሚከተለውን ተናግረዋ።

‹‹የአማራ ሕዝብ ከአገር ላነሰ ዓላማ ሠርቶ እንደማያውቀው ሁሉ ዛሬም ወርደን ከአገር ላነሰ ትንሽ ሥራ የማንሰለፍ መሆናችንን ለእናንተ የምሥራቅ ፀሐዮች ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፡፡›› ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ላቀ አያሌው

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 14/2011 ዓ.ም (አብመድ) በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሐመድ ዑመር የተመራው የሱማሌ ክልል ልዑክ ዛሬ በባሕር ዳር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ውይይት አካሂዷል፡፡

በሕዝብ ለሕዝብ ውይይቱ ላይ የ‹እንኳን ደኅና መጣችሁ› መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው ‹‹ለሱማሌ ክልል ሕዝብ የአማራ ክልል ክልላችሁ መሆኑን ብናውቅም በሕዝባችን ባሕልና ትውፊት መሠረት ትልቅ እንግዶቻችን በመሆናችሁ ትህትና በለመደው ወገባችን ጎንበስ ብለን፤ ቄጠማችንን ጎዝጉዘን ‹‹በጋአ ነበድ ኩቲማዴን›› (እንኳን በደህና መጣችሁልን) ስንል በደስታ ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹‹አገር ማለት ሰው ነው!› እንደሚባለው ሁሉ አገር ማለት የምታሳድጋቸው ልጆቿ የሚፈጥሯትና በፍቅርና በመተሳሰብ ገንብተው የሚኖሩባት ይህቺ ምድር ናትና፤ አገር! በድጋሜ በፍቅር እና በመተሳሰብ ወደገንባችኋት አገራችሁ እንኳን በደህና መጣችሁ›› ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡ 
‹‹ኢትዮጵያ የስልጣኔን ፈር የቀደደች የቀደምት ባለታሪክና ባለዝና ብዙ ጀግኖችን የፈጠረች የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌትና የአፍሪካውያን ኩራት የነበረች አገር ነበረች›› ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህችን ባለታሪክ አገር ወደ ቀድሞ ዝናዋና ክብሯ በመመለሰ የከፍታዋን ዘመን ዳግም ለማምጣት ዕድሉ ‹‹በእኛ በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እጅ ነው›› አሉ፡፡

መሪዎች መለያዬትን ሳይሆን አንድነትን ሲሰብኩ፣ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን ሲዘሩ፣ ‹ቋንቋው ምንድነው?› ማለታቸውን ትተው ኢትዮጵያዊ መሆኑን መለኪያቸውና መስፈርታቸው ሲያደርጉ፤ እንዲሁም ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የቆየውን አንድነትና ታሪክ ለቀሪው ዘመን የሚጠቅመውን በመለዬት ለወጣቶች በአግባቡ ማስተላለፍ ሲችሉ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ነው የተዛቡ ትርክቶች የሚታረሙትም ሀገር የሚገነባውም ብለዋል አቶ ላቀ በንግግራቸው፡፡ የዛሬው የአማራና የሱማሌ ክልል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለኢትዮጵያ አብሮነትና መተሳሰብ ፍይዳው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ 
የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት ዘመናትን ያለፈ እና በብዙ ታሪካዊ ምክንያቶች የታተመ መሆኑን ያወሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ላቀ የዛሬው ግንኙነትም ያንን ታሪካዊ ግንኙነት ማደስ እንጂ እንደ አዲስ መጀመር አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ሁለቱ ወንድም ሕዝቦች የየራሳቸው ባሕል፣ ትውፊት እና እሴት ቢኖራቸውም የበርካታ ሺህ ዓመታት የአብሮነት ታሪክን የሚጋሩ እና አንድነታቸውና ዕጣ ፋንታቸው በጋራ የተጋመደ ነው›› ያሉት አቶ ላቀ ‹‹ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አገራዊ አንድነታችንን አደጋ ላይ የጣለ ፖለቲካዊ ብልሽት በገጠመን ወቅት ሁለቱ ሕዝቦች እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን የለውጥ ኃይሎች ሁሉ አገራዊ ፖለቲካዊ ብልሽታችን መታረም ይኖርበታል ብለው የታገሉ ሕዝቦች ናቸው›› ብለዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ከተፈጠሩት የቅርብ ዓመታት የፖለቲካ ብልሽቶች ውስጥ አንዱ የአማራ ብሔር እንደ በዳይ እና ጨቋኝ እንዲሁም እላፊ ተጠቃሚ ተደርጎ የተዛባ ትርክት በመንዛት ሕዝባችን ሲነገድበት ኖሯል›› ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህ የተዛባ ትርክት እንዲታረም ትግል በተደረገበት ወቅት ሁኔታውን በውል ተገንዝቦ ‹‹ትርክቱ እንዲታረም እና እንዲስተካከል ከጎናችን በመሰለፍ አጋርነቱን የገለፀውን የሱማሌ ክልል የለውጥ አመራርና ሕዝብ ልናመሠግን እንፈልጋለን›› ነው ያሉት፡፡

‹‹የአገር ወዳዱ የሱማሌ ክልል ሕዝብ የለውጥ መሪ ክቡር አቶ ሙስጠፋ ሙሐመድ ዑመር የሀገረ-መንግሥት ግንባታችን የገጠመውን የተሳሳተ የታሪክ ትርክት ስብራት ማከም የቻሉ መሪ ናቸው›› ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ላቀ ‹‹ጅግጅጋ የሚኖር ሱማሌ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብት የማይኖረው ከሆነ የመንግሥታችን ሥርዓት አፓርታይድ ነው ማለት ነው፤ ሌላ ምንም ስም መስጠት አያስፈልግም›› በማለት የአብሮነት ሐኪም፣ የአንድነት መሐንዲስ መሆናቸውን አሳይተዋል›› ነው ያሉት፡፡

‹‹በእርግጥም አገርንና ሕዝብን ከልብ የሚወዱት አቶ ሙስጦፋ ከቃልም በላይ የተግባር ሰው ናቸው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ባለፈው ክረምት በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች የተፈጠረውን መፈናቀል በማውገዝ በክልላቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ 100 ሚሊዮን ብር በመመደብ ያቋቋሙ፣ የተጎዳን ያከሙ፤ ሥነ ልቦናውን ያጀገኑ መሪ መሆናቸውን ታሪክ በደማቁ ያቀልመዋል›› ነው ያሉት፡፡

‹ትናንት› አሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ላቀ ‹‹ትናንት የሱማሌ ክልል የሀገር መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በካሊ ሸለቆ ተደብቆ ዕጣ ፋንታችሁ እንደ ጨርቅ መበጣጠስና መበተን ስለሆነ ከእኛ ጋር ተቀላቀሉ ያሏቸውን እንግሊዛውያንን ‹እስኪ የእናንተ ቆዳ ከእኛ ጋር የት ተመሳስሎ ነው ከኢትዮጵያ ተለይታችሁ ከእኛ ጋር ተቀላቀሉ የምትሉን?› ብለው ሴራቸውን እንዳከሸፉት ሁሉ ለአገር አንድነት በጋራ መቆምና የኢትዮጵያዊነት ስሜት በክቡር አቶ ሙስጠፋ ብቻ ሳይሆን በሚመሩት ሕዝብም በተግባር የሚገለጽ ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹የአማራ ሕዝብ ባለፉት ዓመታት እንደተነዛበት የተሳሳተ ትርክት ሳይሆን የአማራ ሕዝብ አገሩንና ወገኑን ከራሱ በላይ አብልጦ የሚወድ፣ ታማኝና አደራ ጠባቂ፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ ሟች፣ ሥነ መንግሥትን አምኖ የሚቀበልና ሕግ አክባሪ፣ እንግዳ ተቀባይና ያለውን ተካፍሎ የሚበላ፣ ብዝኃነትን ጌጥ አድርጎ የሚመለከትና ፈጣሪውን አጥብቆ የሚያከብር ሃይማኖተኛ ሕዝብ ነው›› ያሉት አቶ ላቀ ዛሬም የሕዝባችን ጭንቀት እኩልነት እና ፍትሐዊነት የሰፈነባት ሀገር እንዴት እንገንባ እንጂ ከቶውንም ሌላ የጓዳ ፍላጎት የለውም ነው ያሉት፡፡

በዚህ አጋጣሚ አሉ ክቡር ርዕሰ መስተዳድር ላቀ ‹‹በዚህ አጋጣሚ ለእናንተ የመሥራቅ ፀሐዮች የምናረጋግጥላችሁ አንድ እውነት ቢኖር የአማራ ሕዝብ አያት ቅድመ አያቶቻችን ያስረከቡንን ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ጠንካራና የበለፀገች ሆና ለትውልድ እንድትዘልቅ ለማድረግ እንሠራለን እንጂ ከዚህ ላነሰ ዓላማ መቼውንም ሠርተን እንደማናውቅ ሁሉ ዛሬም ነገም አንሠራም›› ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ለብሔረ-አገር ግንባታ የማይተካ ሚና መጫወት የሚችሉ እንደ በለስ፣ ተከዜ፣ አንገረብ፣ ከሰም፣ ጀማና ሌሎች የተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤት መሆኑን ያወሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንደ ፀጋዎቹ ሳይሆን በስሙ ሲነገድበት፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት ረመጥ የሚራገፍበት እና ውለው ያደሩ ፖለቲካዊ ጥያቄዎቹ ያለተመለሱ፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን መሠረታዊና መዋቅራዊ ችግሮች ነቅሶ አውጥቶ ለብሔረ-አገር ግንባታ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር እየታገለ ያለ ሕዝብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው አማራ ማስ ሚዲያ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ዶክተር አብራሃም በላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ!
0Shares
0
Read previous post:
የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ሕግ ላይ ለመወያየት የተጠራው ሕዝባዊ ውይይት ተበተነ፤ረቂቁ በምክር ቤቱ ድረ ገጽ ላይ ነበር

‹‹ውይይቱን ያዘጋጀው የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቅድመ ዝግጅት አላደረገም›› በሚል  ከተወያዮች በተነሳ...

Close