“Our true nationality is mankind.”H.G.

“ሞኝ በምን ይረታል፣ ቢሉት እምቢ ብሎ” የእምቢታ ፖለቲካ የት ያደርሰን ይሆን ?

Image may contain: Mushe Semuከገዢው ፓርቲና ከ”ተቀናቃኝ” ሃይል ጋር የሚካሄደው የሁለትዮሽ ትግል አሁንም ከነባራዊ እውነታዎችና ከተሞክሯችን የማይማር፣ መርህ የሌለው፣ በመታሰር፣ በመፈታት፣ በስደት፣ በመሽቆጥቆጥና በጭፍን ድጋፍ ወይም በጭፍን ጥላቻ የሚመራ ከርዕዮተ ዓለም፣ ከድርድር፣ ከምክንያታዊነትና ከሂደት ይልቅ የከረረ የብሔር ወገንተኝነትና “ከኔ በላይ ላሳር” የሚል አግላይነት በሚፈጥረው ጥላቻና የሃሰት ግለሰባዊ ከፍታ ላይ የተንጠለጠለ ሆኖ እንደሚቀጥል ምልክቶች እየታዮ ነው።
የተቃውሞ ሃይሉም ከስርዓቱ ጋር የፈጠረውን ፍቅር እየጨረሰ ስለመጣ ካደፈጠበት ወጥቶ ወደ ተለመደው የብሶትና የእሮሮ፤ የአሳዳጅና የተሳዳጅ ግብግብ እየተመለሰ ነው። መርህ የሌለው ፍቅርም ሆነ ጥላቻ መጨረሻው ይህ እንደሆነ ግልጽ ነበር። 
አዲሶቹ የስልጣን አደላዳዮችና የፖለቲካ ዘዋሪዎችም የግጭቶችን መንስኤ በቅጡ መርምረው ወደ ድርድር ጠረጴዛ ከመምጣት ይልቅ በኛ ተራ እንዴት ከሚል ስሌትና ተነካን፣ ተደፈርን ከሚል እልህ በመነሳት በጅምላ ማሰሩን፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማክሸፉንና ማሰናከሉን፣ የነሱ ያልሆነና ያልመሰላቸውን ማሸማቀቁን፣ ጋዜጠኛ ማሰሩንና ማሳደዱን ተያይዘውታል። የለመድናቸው ፌክመንተሪዎች ተቀናቃኝን ለእስር ለማመቻቸት፣ ለማሳደድና ለመፈረጅ በሚጠቅም መልኩ በቅርቡ እንደሚጧጧፍ መናገር ትንቢተኝነት እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ። ይህ ማለት ደግሞ እንደገና ወደ መጣንበትና ታግለን ወደ አንበረከክነው የዜሮ ድምር ፖለቲካ እየዘቀጥን እንደሆነ ማሳያ ነው። 
የተቃውሞ ሃይሉም አጀንዳዎቹን በመፈተሽና አንጥሮ በማውጣት፣ ቅራኔን በአግባቡ በመያዝ፣ በሃሳብና በመርህ ላይ ተመስርቶ በሚያካሄደው ትግል ልክ አማራጭ ሃሳብ ነጥሮ እንዲወጣ በማድረግ የሕዝብን ጥቅም በተሻለ ደረጃ እንዳሻሻልና እንዲከበር ማድረግ ወሳኙና ብቸኛው መፍትሔ መሆኑ ሊገለጥላቸው አልቻለም። 
ከዚህ ይልቅ በቀላሉ ሊታረቁ የማይችሉ የመንግስት አደረጃጀትን፣ የብሔር ብሔረሰብ መብትን፣ ስር ነቀል ትርምስ ሊደቅኑ የሚችሉ ሕገ መንግስትዊ ጥያቄዎችን በማጫር፣ አማራጭ ሳያቀርቡ የማይታረቁ ልዩነታችን ብቻ ማዕከል አድርገው የማይጨበጥና የማይዳሰስ ጠላት አበጅተው በእውር ድንብር ፖለቲካ ዙርያ እየተሰባሰቡ ነው። 
ከጠበበ የብሔር ወገንተኝነት፣ ከወቅታዊ አሸናፊነት፣ ከትምክህትና ጥበት፣ ከጭፍን ጥላቻና ውግዘት ጠብ የሚል ነገር አለመኖሩን ለመረዳት ሁሉም ኃይሎች አቅም አጥሯቸዋል። በስንፈሰና ዳዋ ተውጠዋል። በድራማውና በማስመሰሉ ተረተዋል። መራራ ቢመስልም ከደረስንበት አስከፊ የስጋትና የጭንቀት ዘመን መሻገር የሚቻለው ችግሩን በመሸሽና በማድበስበስ፣ በመሞሸርና በመቀሸር ወይም ችግሮችን አውሎ በማሳደር እንዳልሆነ በመጀመርያ መተማመን አለብን። ለውጥ የሂደት፣ የድርድርና የውይይት እንጂ በሃይል ሚዛን ላይ ተመስርቶና በመልመጥመጥ ሆኖ አንደማያውቅ መረዳት መቻል አለብን። 
በተለይ እጅግ የሚያሳፍረው ጉዳይ፣ ትግሉና መስዋእትነቱን ለስደት ማመልከቻነት የተቀሙበት ኃይሎች፣ ስደትን የመጎናጸፍ ግባቸውን ማሳካታቸው ሊበቃ ሲገባ፣ በስደት ዓለም ሆነው ታጠቁ፣ ሰንቁ፣ ተዋጉ የሚለው አዋኪ ልፈፋቸውን አጠናክረው ከመቀጠላቸውም በላይ አድማጭ ማግኝታቸው ነው። በዚህ መንገድ የሚገኝ አንጻራዊ የፖለቲካ ትርፍ ቢኖር እንኳን ቀኖ ሲውል አድሮ በመካረር ሁለንተናዊ ድቀት ማስከተሉ አይቀርም። 
ሰሚ ያጣውና የተሻለው አማራጭ ግን በድርድር፣ በምክንያት፣ በክብ ጠረጴዛ መታገል መሆኑ ዛሬም የዳገት ጉዞ የሆነባቸውና የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው ማለት የለመዱት፣ ከትናንት መላቀቅ ያልቻሉ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን መቆናጠጥ ብቻ በራሱ ግብ የሚመስላቸው ቡድኖች በሃሳብ ልዕልና ላይ ማንሰራራት እንዳቃታቸው እየታየ ነው። 
የጀግና ቤቱ እስር ቤት አይደለም። የጀግና ቤቱ እልህ አስጨራሽና አድካሚ የሆነ ድርድር፣ ኃሳብን የሚፋጭበት መድረክ ነው። ከሃሳብ ፍጭት ውስጥ ሁሉም የሚያተርፍበት ብልጭታ እንዲሚፈነጥቅ ጥርጥር የለኝም። መሽቆጥቆጡም ሆነ መስፈንጠሩ ደም ለመቃባትና ለመተላለቅ በር ከፋች ከመሆን ውጭ ጠቃሚ መዳረሻ የለውም። 
መንበር ስለጨበጡና ከፍ ከፍ ስላሉ ትግሉ የተናጠናቀቀ ለሚመስላቸው ትግሉ ገና መጀመሩን እንዲገነዘቡ አሳስባለሁ ። የለውጥ ንፋስ ተስፋ ያጫረበትና ነገን በመናፈቀ ዛሬን ውሎ ያደረ ዜጋ፣ ተዳፍኖ የሚብላላ አጀንዳ በየቤቱ እንደሌለው ማሰብ የዋህነት ነዉ። 
ገና የሃይል አሰላለፍ አልጠራም። ገና አታጋይ መፈክር ሚዛን አልያዘም። ብዥታው እልፍ ነው። በአንድ ዓይነት መፈክር ስር ሁለት የተቃውሞ ሰልፍ እያየን ነው። በእምቢተኝነትም ሆነ ወደ እምቃ ባዘነበለ መርህ ኢትዮጵያን ለመመራት መከጀል ፖለቲካው ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ግልጽ ሳይታለም የተፈታ ስለሆነ ነገ ለመከራ እንዳንዳረግ፣ ዛሬ በጠረጴዛ ዙርያ እንደገና “ሀ” ብለን ተሰይመን እንወያይ።

አቶ ሞሼ ሰሙ ፌስ ቡክ

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0