“Our true nationality is mankind.”H.G.

በደቡብ ክልል ሕዝብ ለፍርድ እንዲቀርቡ ያላቸው ከፈተኛ ባለስልጣናት ከስልጣንና ከድርጅት ታገዱ፤ ለፍርድ ይቀርባሉ

የሃዋሳን የክልልነት ጥያቄ በመንተራስ መንግስት፣ የክልሉ ፓርቲ፣ ምርጫ ቦርድ በየደረጃው ያሳለፉትን የአተገባበር ሂደት በመቃወም ለከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት መጠየቅ አለባቸው በሚል ህዝብ ድምጹን ያሰማባቸው ባለ ስልጣናትና የድርጅት አመራሮች መታገዳቸውን ዲህዴን ይፋ አደረገ።

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ እንዳለው በክልሉ ችግር በተፈጠረባቸና ህዝብ ስጋት ላይ በወደቀባቸው አካባቢዎች በሙሉ በፍጥነት የአመራር ስርዓቱን ለማስተካከል የፖለቲካ ተጠያቂነቱን መራጋገጥ ጀምሯል። በዚሁ መሰረት ደኢህዴን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የሲዳማ እና የሀድያ ዞን ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከኃላፊነት አደገ። በከፋ ዞን የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችም የህግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትሉ አሳስቧል። ፋና መግለጫውን ተንተረሶ የሚከተለውን አስነብቧል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ነው ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎቹ ከስራ መታገዳቸውን ያስታወቀው።

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በመግለጫው በክልሉ የሚነሱትን የክልልነት ጥያቄ የሚመለስበት አግባብ ላይ ግልጽ አቅጣጫ በድርጅቱ ጉባዔ መቀመጡን አስታውሶ፥ ይሁን እንጂ ከድርጅት አቅጣጫና ከመንግስት ውሳኔ በተቃራኒ የተፈጸሙ ኢ ህገ መንግስታዊ ድርጊት እና ይህንን ተከትሎ በሲዳማ ዞን በሰው ህይወት፣ አካል እና ስነ ልቦናዊ እንዲሁም በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እጅግ አሳዛኝ እና ኢ ሰብአዊ በመሆኑ በጽኑ አውግዟል።

የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ዜጎች መጽናናትን የተመኘው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፥ በጥቃቱ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራ በአስቸኳይ እንዲሰራም ወስኗል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በጥፋቱ የተሳተፉ እንዲሁም ያስተባበሩ እና የመሩ አካላትን ከህዝቡ ጋር በመተባበርና በመለየት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመሩት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ለፍጻሜ እንዲደርሱ በጥብቅ እንደሚሰራም አስታውቋል።

በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ የስርዓት አልበኝነት አዝማሚያዎች በክልሉ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ያደረጉ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆሙና የህግ የበላይነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቋም መወሰዱን በመግለጫው ተመልክቷል።

በዚህም የተነሳ በአካባቢው የሚታዩ የስርዓት አልበኝነት በህዝብ ጥያቄ ሽፋን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ የክልሉን ህዝቦች ደህንነት ስጋት ላይ የጣሉ በመሆናቸው በመደበኛው የፀጥታ ስራ መቆጣጠር ወደማያስችልበት ደረጃ በመድረሱ የፀጥታው ስራ በፌደራል ኮማንድ ፖስት እንዲመራ መደረጉንም አስታውቋል።

በክልሉ የሚከሰቱ ችግሮች በዋናነት ከአመራር ስርዓቱ ጋር የተያያዙ መሆኑን አስቀድሞ መገምገሙን በማስታወስ አሁንም ለተፈጠረው ችግር የአመራር ሚና የጎላ መሆኑን ተመልክቷል።

በቀጣይም ይህንን ለማረም ከድርጁ ስራ አስፈጻሚ እና ማእከላዊ ኮሚቴ ጀምሮ እስከታችኛው የአመራር እርከን ድረስ ፈትሾ እርምት በመውሰድ ውጤቱን ለአባላቱና ለህዝቡ እንደሚያሳውቅ ውሳኔ አሳልፏል።

አሁን ችግሩ በተከሰተባቸው እና ህዝቡን ስጋት ውስጥ ያስገቡ አንቅስቀሴዎች ጎልተው እየተዩ መሆናቸውን በገመገመባቸው አካባቢዎች ካለፈው ጉድለቶች ትምህርት በመውሰድ በፍጥነት የአመራር ስርዓቱን ለማስተካከል የፖለቲካ ተጠያቂነቱን መራጋገጥ መጀመሩን አስታውቋል።

በዚህ መሰረት ሰሞኑን በሀዋሳ ከተማና እና በሲዳማ ዞን የገጠር አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት የራሳቸው ሚና ነበራቸው በሚል የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር እና የሲዳማ ዞን የፊት አመራሮችን ከመንግስትና ከድርጅት ሀላፊነት ያገደ መሆኑን አስታውቋል።

የሃድያ ዞንም የህዝቡ ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ የተደረገውን እንቅስቃሴ በመገምገም በተመሳሳይ ሁኔታ የዞኑን የመንግስት አመራር ከሃላፊነት ማገዱን ደኢህዴን አስታውቋል።

በተጨማሪም በወላይታ ዞን አካባቢ ከመርህ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ያሳሰበው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፥ በከፋ ዞንም የተካሄዱትን እንቅስቀሴዎች የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ናቸው ሲል አሳስቧል።

የክልሉ ህዝቦች ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ከህግና ስርዓት ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እና ድርጊቶችን በመከላከልና በማጋለጥ ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ የደኢህዴን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪ አቅርቧል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ
0Shares
0