“Our true nationality is mankind.”H.G.

ጠቅላይ ሚንስትሩ ተጨማሪ ጀኔራሎችን የመግደል እንቅስቃሴ እንደነበር ተናገሩ፤ “ሰኔ 15 አደገኛ ክስተት ነበር”

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ዛሬ ከሰዓት በሰጡት መግለጫ የሰኔ 15ቱ ግድያ እና ‘መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ’፣ ቀጣዩን ምርጫ እና የሰብዓዊ ምበት አያያዝን በሚመለከት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ተጨማሪ ጀኔራሎችን ለመግደል እንቅስቃሴ ሲደረግ እንደነበር መረጃ አለንም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የሰኔ 15ቱን ሁኔታን አቅልሎ ማየት ልክ አይደለም ያሉ ሲሆን መንግሥታቸው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን በፍጥነት መቆጣጣር ባይችል ኖሮ አስከፊ ነገር ይዞ የሚመጣ አደገኛ ክስተት ነበር ብለዋል።

ጀኔራል ሰዓራ መኮንንን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ ስለሚገኝበት ሁኔታ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ተጠርጣሪው በህይወት እንደሚገኝ እና አንገቱ ላይ ለደረሰበት ጉዳት የህክም እርዳታ እያገኘ ሲሆን በጉዳቱ ምክንያት መናገር ባለመቻሉ ከእርሱ ይገኝ የነበረ መረጃ ማግኘት አለማቻሉን አስረድተዋል።

ይሁን አንጂ ጀኔራሉን በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብ በስልክ ሲገናኛቸው የነበሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን እና ከእነርሱም ብዙ መረጃዎች መሰብሰባቸውን ገልጽዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ተጨማሪ ጀኔራሎችን ለመግደል እንቅስቃሴ ሲደረግ እንደነበር መረጃ አለንም ብለዋል።

መንግሥት የሰኔ 15ቱን ክስተት መሰረት አድርጎ የግለሰቦች እና የመገናና ብዙሃንን ድምጽ ለማፈን ሙከራ አድርጓል የሚል ቅሬታ ይቀርብበታል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሲመልሱ ፤ ይህ እውነት አይደለም መንግሥት የሰዎችን ደምጽ የማፈን ፍላጎት የለውም እንደውም ከዚህ ቀደም በመንግሥት ተዘግተው የነበሩ መገናኛ ብዙሃን እንዲከፈቱ ተደርጓል ብለዋል።

የኢንተርኔት አገልግሎትን በተመለከተ፡

ለጠቅላይ ሚንስትሩ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፤ የጸጥታ ችግር በተከሰተ ቁጥር ለምን የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ይደረጋል? የሚል ይገኝበታል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ እራሳችንን ከበለጸጉት ሃገራት ጋር ማወዳደር የለብንም፤ በበለጸጉ ሃገራት ሰዎች ኢንተርኔትን በመጠቀም ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ ምልዕክት አያስተላልፉም፣ በበለጸጉት ሃገራት ሰዎች ኢንተርኔትን ለበጎ ነው የሚጠቀሙት ያሉ ሲሆን፤ የሰዎችን ህይወት እና ንብረት ከጥቃት ለማትረፍ አስፈላጊ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ ለሳምንት ሳይሆን እስከ ወዲያኛው ኢንተርኔት ሊዘጋ ይችላል ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ፡

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መንግሥት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ቅሬታዎች እየተነሱበት እንደሆነ በመጠቀስ መንግሥታቸው በዚህ ረገድ የነበረው አቋሙ ስለመቀየሩ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ አሁንም ጭለማ ቤት የታሰረ የለም፣ ሰው አይገረፍም፣ ጥፍር አይነቀልም ያሉ ሲሆን በሰብዓዊ መብት አያያዝ ያለን አቋም አልተቀየረም፤ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲስፋፋ ነው ፍላጎታችን ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግነኙነትን በተመለከተ

ከኢትዮጵያ መልካም ግነኙነት ከኤርትራ ጋር መመስረቷን በማስታወስ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የኤርትራ ህዝብ እና መንግሥት ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግሥት ጋር አብሮ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግራዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ሁለቱ ሃገራት ግኑኝነታቸውን አድሰው ወደስራ ሲገቡ ግን በርካታ የባህል እና የኢኮኖሚ መዛባቶች መስተዋላቸውን አልሸሸጉም። ይህ የሁለቱን ሃገራት ግነኙነትም ስርዓት ለማስያዝ እየተሰራ መሆኑን እና ይህም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የሲዳ ዞን የክልል እንሁን ጥያቄን በተመለከተ፡

የትኛውም ህዝብ ፖለቲካዊ መብቱን የመጠየቅ እና የማስከበር መብት አለው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ፤ የክልልነት ጥያቄው ከፖለቲካ መብት በተጨማሪ የሃብት ክፍፍል እና ህጋዊ ሂደቶች ያስፈልጉታል በማለት፤ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ህዝበ ውሳኔው እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የአዴፓ እና የህወሃት የቃላት ጦርነትን በተመለከተ፤

ከሰሞኑን በህወሃትና በአዴፓ መካከል የተፈጠረው የቃላት ጦርነት በፖለቲካ አለም የሚያጋጥም መሆኑን የሚናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ሁለቱ ፓርቲዎች ለህዝብ ጥቅም ሲባል አብራው ሲታገሉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለረጅም ዓመታት ለህዝብ ጥቅም ሲሉ አብረው ታግለዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ፤ በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ግን እንዲህ አይነት ንትርኮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ ብለዋል።

ሁለቱ የኢህዴግ እህት ድርጅቶች ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ መድረክ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ዜና

0Shares
0