ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ 1 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ለቤት ልማት መዘጋጀቱን ታከለ ኡማ አስታወቁ

የመዲናዋ ነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ለቤት ልማት የሚውል 1 ሺህ 500 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የአስተዳደሩን የ2011 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
 
ምክትል ከንቲባው በሪፖርታቸውም ባለፈው አንድ ዓመት በከተማ አስተዳደሩ ከካቢኔ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ድረስ 47 ሺህ ሰራተኞችን ያቀፈ የመዋቅር ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
 
በወረዳዎች የሚታዩ የአግልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ 5 ወረዳዎች ዘመናዊ እና ቀልጣፍ አገልግሎት እንዲሰጡ በዘመናዊ መንገድ መገንባታቸውንም አንስተዋል።
 
የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመቀነስ ባለፈው ዓመት በቀን 44 ሺህ ሜትር ኪዩብ ማምረት የሚችል የውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
 
በከተማዋ የሚታየውን የመኖርያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ ከ3 ሺህ በላይ የቀበሌ ቤቶች ለአቅመ ደካሞች መተላለፋቸው ተገልጿል።
 
ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራን በተመለከተ የከተማ አስተዳደሩ የ2 ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ ከ163 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስራ ፈላጊዎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።
 
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም 35 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን የገለጹት ኢንጂነር ታከለ፥ ገቢው ከባለፈው ጋር ሲነፃፀር በ5 ነጥብ4 ቢሊየን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።
 
በሌላ በኩል 13 ሺህ በላይ የሚሆኑ ህገወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፥ በተመጣጣኝ ዋጋ ለከተማው ነዋሪ የሚያቀርብ ግዙፍ የዳቦ ማምረቻ ኢንቨስትመንት ድጋፍ ተደርጎለት ወደ ስራ ገብቷል።
 
በአምስቱም የአዲስ አበባ መውጪያና መግቢያ በሮች ላይ አርሶ አደሮች ምርታቸውን የሚያስቀምጡበትና ለገበያ የሚያቀርቡበት ማዕከላትን ለመገንባት ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑ ተመላክቷል።
 
የከተማዋ አስተዳደር ባካሄደው ሰፊ ንቅናቄ ከ10 ሺ በላይ ወጣቶችን ከጎዳና ላይ ማንሳት መቻሉን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ደብተር እና ለ600 ሺህ ተማሪዎች የደንብ ልብስ በነፃ ለማቅረብ እንዲሁም ለ300 ሺህ ህፃናት የምገባ ፕሮግራም የማስጀመር ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ ተገልጿል።
 
የከተማዋ ነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ አዲስ የቤት ልማት መርሃ ግብር ለመጀመር 1 ሺህ 500 ሄክታር መሬት የተዘጋጀ ሲሆን፥ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍም ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው ተብሏል።
 
በቀጣዩ ዓመት ለ250 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ይሰራል ያሉት ምክትል ከንቲባው፥መልማት ያልቻሉ ሰፋፊ መሬቶችን በመንግስትም ይሁን በግለሰቦች ተይዘው የቆዩ ሁሉ በጥናት ወደ መሬት ባንክ እንዲመለሱና ለተሻለ ልማት እንዲውሉ ይደረጋሉ ብለዋል።
 
በአዲስ አበባ የሆቴል ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እና ከተማዋን ግዙፍ የኮንፈረንስና የልዩ ልዩ ሁነቶች ማስተናገጃ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ግዙፍ ኮንቬንሽን የሚከፈት መሆኑንም ጠቁመዋል።
 
በከተማዋ የሚስተዋለውን ስር የሰደደ የውሃ ችግር ለመፍታት የከርሠ ምድርና የገፀ ምድር ውሃ መገኛ ምንጮችን በማልማት የንፁህ ውሀ አቅርቦት ችግር መፍታ ቅድሚያ ተሰጥቶ የሚሰራበት ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
 
ምክር ቤቱ ለሶስት ቀናት በሚያካሂደው መደበኛ ጉባኤው የአስተዳድሩን የ2012 ረቂቅ በጀት ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
 
ከዚህ ባለፈም የተለያዩ ሹመቶችን የሚያፀድቅ መሆኑ ተገልጿል።
 
እንዲሁም ምክር ቤቱ የከተማዋን ፍርድ ቤቶች የ2011 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በማዳመጥ የሚያፀድቅ መሆኑን ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።
ፋና –
Related stories   አውሮፓ ህብረት እየተሽኮረመመ ታዛቢ ሊልክ ነው