“Our true nationality is mankind.”H.G.

በሲዳማ ዞን የደረሰውን አደጋ ፖሊስ ይፋ አደረገ! ጥፋተኞቹ እየተለቀሙ ነው

ሰሞኑን በሲዳማ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እና ከተሞች በተከሰተው ግጭት ሀኪም ቤት ሳይደርሱና በየአካባቢው የተቀበሩትን ሳይጨምር ሃምሳ ሶስት ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች ሃምሳ አራት ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ለጀርመን ድምጽ አረጋገጠ።

በወቅቱ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘም እስካሁን 935 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥራ ማዋሉን የሲዳማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል። የመምሪያው ዋና አዛዥ ምክትል ኮማንደር ዳኛው ደምሴ ዛሬ በተለይ ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት የግጭቱ መነሻ ሐምሌ 11 ቀን 2011ዓ,ም በሐዋሳ ከተማ የሲዳማ ብሔር በክልል የመደራጀት ጥያቄን እናውጃለን የሚሉ ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር መጋጨታቸው ነው።

በመቀጠልም ግጭቱ ሲዳማ ዞን ውስጥ ወደሚገኙት ሁላ፣ ይርጋዓለም፣ ማልጋ፣ ሞሮቾ እና አለታ ወንዶ ወረዳ እና ከተሞች መዛመቱን ተናግረዋል። በተጠቀሱት ከተሞች እና ወረዳዎች ከሞቱት እና ከቆሰሉት ወገኖች በተጠጨማሪ፤ የዱቄት ፋብሪካዎች እና የመዝናኛ ሎጆችን ጨምሮ በሚሊየን ብሮች የሚገመት ንብረት በቡድን ሲንቀሳቀሱ በነበሩት ወጣቶች መውደሙን እና መቃጠሉንም ኮማንደሩ  ዘርዝረዋል።

በወጣቶቾ የተፈጸመው ድርጊት ከሲዳማ ባሕል እና ወግ ያፈነገጠ ብቻ ሳይሆን ከጥያቄው ጋር አይገናኝም ያሉት ምክትል ኮማንደሩ በአሁኑ ወቅትም ድርጊቱ በሲዳማ ማኅበረሰብ እና በየወረዳው በሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች እየተወገዘ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ፋና የሚከተለውን ዘግቧል – በደቡብ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ ከነበረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑን በክልሉ የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ። ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቱ በዛሬው እለት ዝርዝር ተግባራትን እና የአፈጻጸም ሁኔታዎችን ይፋ አድርጓል።

በዚህም በክልሉ በተለይም በሲዳማ ዞን እና አካባቢው ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር በተያያዘ በደረሰው ጉዳት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን አስታውቋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ላይ የመለየትና የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ያለው ኮማንድ ፖስቱ፥ ህብረተሰቡም ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ የመስጠትና ንብረቶችን የማስመለስ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ከህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘም ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሶ፥ የፍተሻ ኬላዎችን አልፈው በግለሰቦች እጅ የሚገኙ መሳሪያዎች ተይዘዋልም ነው ያለው።

ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቱ ከ12 ቀናት በፊት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር መከሰቱን ተከትሎ መቋቋሙ የተገለጸ ሲሆን፥ ክልሉ ወደ ቀደመ ሰላሙ እስከሚመለስ ድረስ እንደሚሰራ ተጠቅሷል።

ሁኔታዎች አሁን ላይ መሻሻል ማሳየታቸውን እና ሁኔታው በዚህ ከቀጠለና ህብረተሰቡም ተባባሪነቱን ካሳየ የኮማንድ ፖስቱ የቆይታ ጊዜ ረጅም እንደማይሆን ተገልጿል።

መደበኛ ህጎችን መጣስ (ያልተፈቀዱ ሰልፎችን ማድረግ፣ በዜጎች ላይ ሰብዓዊ ጥቃት መፈጸም፣ የተለየ እና የሰላም ማደፍረስ እንቅስቃሴ ማሳየትና ማድረግ በኮማንድ ፖስቱ ተከልክለዋል።

ከዚህ ባለፈም በሃዋሳ ከተማ ክልከላው እስከሚነሳ ድረስ ሞተር ብስክሌት ማሽከርከር አይቻልምም ነው ያለው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሞተር ብስክሌታቸው የተያዘባቸው ግለሰቦች ባለቤትነታቸውን አሳውቀው መውሰድ ይችላሉም ነው ያለው ኮማንድ ፖስቱ።

በቀጣይም ከሃዋሳ ውጭ ባሉ ሌሎች ከተሞች ከሞተር ብስክሌት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለፀጥታ ችግር ሊሆኑ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ከተስተዋሉ ክልከላ እንደሚደረግም ተነስቷል።

ከላይ ከተጠቀሱት ውጭ በኮማንድ ፖስቱ የሰዓት እላፊም ሆነ የተለየ ክልከላ አልተደረገም ያለው ኮማንድ ፖስቱ፥ ወደፊት ከዚህ ጋር ተያይዞ የተለዩ አካባቢዎች ካሉ ይፋ ይደረጋልም ብሏል።

አሁን ላይ በክልሉ ሁሉም መንገዶች ክፍት መሆናቸውን ጠቅሶ፥ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ላሳየው ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል።

በቀጣይም ሰላምና ፀጥታን ከማስፈን አኳያ እስከ ታች ድረስ ህዝባዊ ውይይት እንደሚደረግም አንስቷል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ኦሮሞ ኦሮሞን አድፍጦ እየገደለ ነው፤ ኦነግ ሸኔ ለስራ የሚጓዙ አምስት ኦሮሞዎችን ገደለ
0Shares
0