“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሃሳብ አመንጪ ምሁራንን የተራበች አገር

መዝገበ ቃላቱ ምሁርን አስተዋይ፣ የተማረ እና ቀለም የጠገበ እያለ ያብራራዋል። ከዚህ አንፃር አሁን ላይ በኢትዮጵያ ምን ያህል ምሁር ሊሰኝ የሚችል አስተዋይ ሰው አለ? በሚለው ላይ ብዙዎች የተለያየ አቋም አላቸው። ምሁር ማን ነው? ብለን ከተነሳንም አከራካሪ ይሆናል።

ዶክተር ሙሉጌታ ደበበ፤ “በመውቀስ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ፤ ራሱን ምሁር ነኝ ብሎ የሚጠራ እና ለኢትዮጵያ የተጨበጠ መፍትሄ የማያመጣ ሰው ምሁር መባል የለበትም። አማራጭ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የውጭ ጉዳይም ሆነ በየመስኩ አሸናፊ ሊሆን የሚችል ሃሳብ ይዞ የማይመጣ ሰው ምሁር ነው ማለት አይቻልም” ይላሉ። ምሁር ማለት ዲግሪ ያለው አይደለም። የተማረ ሁሉ ምሁር አይደለም ይላሉ።

የምሁር መደብ በኢትዮጵያ የለም የሚል እምነት እንዳላቸው የሚናገሩት ደግሞ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ ናቸው። “በየመገናኛ ብዙኃኑ እና በተለያዩ ቦታዎች ላይ ምሁራን ተብለው በተደጋጋሚ ሃሳብ የሚሰጡት ምሁራን ሳይሆኑ ነጋዴዎች ናቸው።” የሚሉት ዶክተር የሺጥላ፤ ሃሳብን አንስተው ማዋጋት ከፊት ሆነው ችግሮችን መምራት እንጂ መፍትሄ ሲያመላክቱ እየተስተዋለ አለመሆኑንም ይናገራሉ። አሁን ምሁራን ተብለው ከፊት መድረኮችን የተቆጣጠሩት እና መሪውን የሚዘውሩት ሌሎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ችግር በመፍታት ፋንታ ጭራሽ ምሁር ተብለው ችግሩን በጣም የሚያወሳስቡበት እንደሆኑ ነው የሚጠቁሙት፡፡

በመውቀስ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ፤ ራሱን ምሁር ነኝ ብሎ የሚጠራ እና ለኢትዮጵያ የተጨበጠ መፍትሄ የማያመጣ ሰው ምሁር መባል የለበትም

“ምሁር ነኝ ባዮቹ ጨዋው ማህበረሰብ ከእነርሱ በአመለካከት የተሻለ ነው።” ካሉ በኋላ፤ ሰዎቹ የተማሩ ናቸው ቢባሉም የማህበረሰቡን ችግር ያልተረዱ፤ እየተፈጠረ ያለውን በጥልቀት ተገንዝበው፣ አጣርተው እና መርምረው መፍትሄ ለማቀበል ፍላጎት እና ቁርጠኝነት የሌላቸው ናቸውም ይሏቸዋል። ዶክተር የሺጥላ፡፡

በየመገናኛ ብዙኃኑ በየሳምንቱ አንዳንዴም በየዕለቱ ሃሳብ ቢሰጡም ዓላማቸው ትርፍ እና ብልፅግና ብቻ በመሆኑ ችግር ፈቺ ሃሳብ ሲያመነጩ እንደማይታዩም ይጠቁማሉ። እነዚህ በየመገናኛ ብዙኃኑ ከአንዱ ወደ ሌላው እየተሽከረከሩ በድፍረት ሃሳብ የሚሰጡ ሰዎች “ያስመስላሉ” እንጂ፤ የማህበረሰቡን ችግር የተረዱ አይደሉም። ተሰብስበው አሉ ለምትሏቸው ችግሮች መፍትሄ አምጡ ቢባሉ መፍትሄ ማቅረብ እንደሚያዳግታቸውም ነው የሚናገሩት፡፡

ዶክተር የሺጥላ ባለፉት 25 ዓመታት የትምህርት መሰረተ ልማት በመስፋፋቱ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ እና ከዚያም በላይ ብዙ የተማሩ ሰዎች ቢኖሩም፤ እነዚያን ሁሉ ምሁራን ማለት አይቻልም። ለዚህ ምክንያቱ በአገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ሁኔታ የፈጠረው ችግር መሆኑን ይጠቁማሉ።

ነገር ግን፤ የተወሰኑ በጣም ትልቅ አበርክቶ ማድረግ የሚችሉ አሉ። እነርሱ ግን ቦታ እንዳላገኙ ዶክተር የሺጥላ ያመለክታሉ። የተዘረጋው ሥርዓት እነርሱን የሚጋብዝ አይደለም። በዚህ ምክንያት በትክክል ምሁራን መባል ያለባቸው አብዛኞቹ አድፍጠው ጊዜያቸውን በመታዘብ የሚያሳልፉ መሆናቸውንም ይናገራሉ።

የተማሩ ምሁራን ገጠር ለገጠር የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት ብለው ብዙ ምርምር የሚያደርጉ ናቸው። መገናኛ ብዙኃኑ ምሁራን ብለው የሚያናግሯቸው የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ በመሆኑ እውነተኛ ምሁር መባል ያለባቸው ሰዎች ሳይታወቁ ሃሳባቸውም አዳማጭ አጥቶ ባክኖ የሚቀርበት ሁኔታ መኖሩንም ያመለክታሉ። በትክክል ጥናት እያካሄዱ ችግር ፈቺ ሃሳብ የሚያፈልቁ ሰዎች ዕድሉን እያገኙ መድረኮችንም እየተጠቀሙባቸው አይደለም።

“እውነተኛ አቅም ያላቸው በምርምር መፍትሄ መጠቆም የሚችሉ ሰዎች ፍራቻ አለባቸው። አሁን ላለው ችግር መፍትሔው ይሄ ነው፤ ብል ‘እጠየቃለሁ፤ አልደመጥም’ የሚል ስጋት አላቸው። ደህንነት አይሰማቸውም። በቤተሰቤና በህይወቴ ላይ ችግር ሊያጋጥመኝ ይችላል። እፈረጃለሁ፤ በደቦ እጠቃለሁ የሚል ስጋትም አለባቸው።” ይላሉ።

ሌላው የባህል ጉዳይ ነው የሚሉት ዶክተር የሺጥላ፤ ምሁራን ሃሳብ ሊሰጡ ሲነሱ ማህበረሰቡ፣ ጎረቤት፤ ጓደኛ እና ቤተሰብም ጭምር አያበረታታቸውም። እናንተ ተቀምጣችሁ ችግሩ ለምን እንዲህ ይጦዛል? ብሎም አይወቅሳቸውም። ነገሩ ተበለሻሽቷል በሚል ሰበብ አርፋችሁ ተቀመጡ የሚል ስለሚበዛ አዲስ ሃሳብ የማመንጨት ብቃት ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ገድበዋል፤ ሆኖም ይህ አያዋጣም ብለዋል።

ሌሎችም ተጓዳኝ ችግሮች እንዳሉባቸው በመጠቆም፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብ ሊያፈልቁ ማህበረሰቡን ቀርፀው በሃሳብ መምራት የሚችሉ ጥቂት ሰዎች መኖራቸው ሊዘነጋ አይገባም። እነዚህን ሰዎች የሚጋብዝ የጋራ መድረክ የለም። አሁን ምሁር እየተባሉ የሚጠሩት መድረክ እያገኙ ያሉት ሰዎች ሃሳብ አፍልቀው ለችግሮች መፍትሄ እያስቀመጡ አስተሳሰብን የሚቀርፁ ሳይሆኑ፤ ሌሎች መሆናቸውን ዶክተር የሺጥላ ደጋግመው ይናገራሉ።

“እውነተኛ አቅም ያላቸው በምርምር መፍትሄ መጠቆም የሚችሉ ሰዎች ፍራቻ አለባቸው። አሁን ላለው ችግር መፍትሔው ይሄ ነው፤ ብል ‘እጠየቃለሁ፤ አልደመጥም’ የሚል ስጋት አላቸው። ደህንነት አይሰማቸውም። በቤተሰቤና በህይወቴ ላይ ችግር ሊያጋጥመኝ ይችላል። እፈረጃለሁ፤ በደቦ እጠቃለሁ የሚል ስጋትም አለባቸው።”

ዶክተር ሙሉጌታ ደበበ በበኩላቸው፤ ምሁር ልባም፤ ተመራምሮ አዲስ ሃሳብ ማመንጨት የሚችል በሚለው ሃሳብ ላይ በመስማማት በኢትዮጵያ ባለው የምሁራን ሚና ላይ ግን ከዶክተር የሺጥላ ትንሽ የተለየ ሃሳብ አላቸው። የኢትዮጵያ ምሁራን ሚና ተብሎ ሲነሳ በጣም ከባድ የነበረው ማዕከላዊነት አሁን በደንብ ያልተማከለ እየሆነ ነው። በትግራይ፣ በአማራ ክልልም ሆነ በደቡብ ያለው ሁኔታ በጣም የተለያየ ነው። በትግራይ መጀመሪያ ምሁራንን አሰባስቦ የማወያየት ሁኔታ አለ። ይህ በኦሮሚያም ይስተዋላል። በጠቅላላ ኦሮሚያ ውስጥ ያለው የተማረ ሰው መንግስትን እንዴት እንርዳ ወደሚለው እየመጣ ነው። የክልሉ መንግስት ይህንን አመቻችቷል። የኦሮሚያ ክልል መንግስት ጠቅላላ በግልም ሆነ በመንግስት ተቋማት ያሉ ምሁራንን በሙሉ ሰብስቦ አወያይቷል። ከማወያየት ባሻገር በክልሉ ውስጥ እንዴት ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ሊመጣ እንደሚችል አደረጃጀት ሰርቶላቸዋል። ጅምር ቢሆንም ይህ በጣም ትልቅ ነገር ነው።

የኦሮሚያ ምሁራን በተለያየ መልኩ እየተቧደኑ ነው። በሙያ የኢኮኖሚ፣ የህዝብ አስተዳደር እና ሌሎችም በሚል ቡድን እየመሰረቱ ነው። በአደረጃጀትም ቡድን በመፍጠር እየተሰራ ነው። ከዚያ በኋላ በሁሉም ክልሎች ካሉ ምሁራን ጋር የጋራ መድረኮችን የመፍጠር ሁኔታ ይኖራል። ምሁሩ እስከአሁን ተቀምጧል። አሁን ግን መግባት እና አገር ማዳን ያስፈልጋል በማለት፤ እንሳተፍ ብሎ እየተነሳ ነው።

በአገሪቷ ላይ ያንዣበበው የፀጥታ ስጋት፤ ሥራ አጥነት፣ ድርቅ እና መፈናቀል አሳሳቢ በመሆኑ በኦሮሚያ አካባቢ በኢትዮጵያ ሰላም እንዴት ይስፈን? ዴሞክራሲ እንዴት ይምጣ? ልማት እንዴት ይረጋገጥ? በሚል በጥሩ መንፈስ እየተሰራ ነው። በፖለቲካው በኩል በአገሪቱ ከመቶ በላይ ፓርቲ አለ። ይህን ሁሉ ለማጥራት ትልቅ ተሳትፎ እየተደረገ ነው። 15 የነበሩት በኦሮሚያ ብቻ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተዋሃዱ ነው። ወደ ሁለትና ሶስት እየመጡ ነው። ይህ የሆነው በምሁራኑ ተሳትፎ ነው። ምሁራኑ በጥናት ላይ ተመስርተው በፓርቲዎቹ ላይ ከባድ ፈተና አቅርበዋል። በፓርቲዎች ላይ ጥናትን ማዕከል ያደረገ በጣም ከባድ ጫና በመፍጠር የበዙት እንዲሰበሰቡ ግፊት በመፍጠር ውጤት እየመጣ ነው።

ሌሎችም ክልሎች እንዲህ ማድረግ አለባቸው። በሶማሊያ ያለው የምሁራን መነሳሳት የተሻለ ይመስላል። ማየት ቢጠይቅም ደቡብና ሌሎች ክልሎች ላይ የምሁራን ተሳትፎ የተቀዛቀዘ ይመስላል። ነገር ግን ሁሉንም በማነሳሳት ክልሎችን ከክልሎች ጋር ማስተሳሰር ይጠይቃል። ለዚህ ትልቅ ሥራ መሰራት አለበት። ሆኖም ግን አሁንም ችግር አለ። አለመደማመጥ ያጋጥማል። ምሁራን ይህን አልፈው ሃሳባቸውን ማስተላለፍ እና አማራጮችን ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው መዘንጋት እንደሌለባቸው ዶክተር ሙሉጌታ ይናገራሉ።

የኦሮሚያ ምሁራን መንግስትን እየደገፉ ናቸው። በትግራይ ክልልም ኢትዮጵያን እንዴት እናድን እያሉ ነው። ሌሎችም ለአገራቸውና ለህዝባቸው መፍትሄዎችን ማመላከት አለባቸው፤ ይላሉ። በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ክፍል የሚሰሩ እና የሚያስተምሩት ዶክተር የሺጥላ የደቡብን ክልል ተሳትፎ አስመልክቶ ሲናገሩ፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት ችግሮችን እያስጠኑ ለዚያም መፍትሄ አምጡ እየተባለ የተሻለ ተስፋ ሰጪ መነሳሳት ነበር። ከዚያ በፊት አልነበረም። ከጥናቱ በኋላም አመራሮች ከሪፖርት ውጪ ብዙም መረጃው አልነበራቸውም። በጥናት ሲመለስ ይህ ነገር “እዚህ ደርሷል ወይ?” ብለው ይባንኑ ነበር። በዚህ አመት ግን በክልሉ ውስጥ በተፈጠረው አጠቃላይ ቀውስ አሁን በጥናት ላይ የተመሰረተ የምሁራን ተሳትፎ አይታይም። ነገር ግን በሌሎችም ክልሎች እንዳለው ፎረሞች አሉ። ሥራ ይሰራል፤ የማማከር ሁኔታም ይኖራል። ይህንን ሌሎችም ሊሰሩት ይችላሉ። ምን ይደረግ በሚል እና በመፍትሄ ላይ በፍፁም መነጋር የለም። አንዳንዴ በሰል ላሉት ሃሳብ አመንጪዎች ብዙ ነገሩ ክፍት አይደለም። ግን አንዳንድ ወጣቶች ሃሳብ ይሰጣሉ። አንዳንዴ እበለጣለሁ በሚል ፍራቻ ምሁራኑ ወደ መድረኩ በመምጣታቸው ሰዎች እንደአማራጭ ያዩዋቸዋል በሚል የምሁራን ሃሳብ የማዳመጥና ለነርሱ መድረክ የማመቻቸት፤ እንዲሁም ለማስጠጋት የመሞከር ሁኔታ የለም ይላሉ።

በአንዳንድ ችግሮች ላይ መገናኛ ብዙሃን ሲጋብዙም ሆነ መድረኮች ሲዘጋጁ፤ በጉዳዩ ላይ በዩኒቨርሲቲው ያጠኑ እና የተመራመሩ ወጣትም ሆነው ነገሮችን የሚረዱ ሃሳብ ማፍለቅ የሚችሉ ሰዎች ማግኘት ያስፈልጋል። “የሳምንት እንግዳ” እየተባለ ተመሳሳይ ሰዎችን ከማቅረብ ይልቅ እነዚህኞቹን ማቅረብ ቢቻል ያደፈጠው ሁሉ ሊነሳ እና ሊያግዝ ይችላል።

መንግስትም በራሱ በተለያዩ መዋቅሮች ሶስተኛ ዲግሪ ስለሰሩ ብቻ መፍትሔ ያመጣሉ ማለት የለበትም። ችግርን የሚረዱ፤ ተመራምረው ማማከር የሚችሉ ሰዎችን በመዋቅር ደረጃ ዘርግቶ ሊቀበላቸው ይገባል። ለምሁራኑ አበርክቶ ቦታ መሰጠት አለበት። ሃሳብ በማፍለቅ ህብረተሰቡን መምራት የሚችሉ ለመንግስትም ገንቢ ሃሳብ ሊያፈልቁ የሚችሉ ሰዎችን መጠቀም ቢጀምር፤ ምሁር በስራው እየተመዘነ እየተለየ ይመጣል። ሰዎች ካሉበት ይወጣሉ ይላሉ።

አገር አደጋ ላይ ከወደቀ ጉዳቱ የጋራ በመሆኑ፤ በእርግጥ ከመንግስት ባሻገር ምሁራን በጉዳዮች ላይ ጥናት አድርገው ለችግሮች መፍትሄ የማመላከት ሃላፊነት አለባቸው። ለመፍትሄው ሁሉም የየራሱን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅበታል። የሲቪክ እና የሙያ ማህበራት ሚና የተሳትፎ አማራጮችን በማዘጋጀት ህብረተሰቡ እንዲያውቅ የማድረግ ሥራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። አሁን ይህን ሲያደርጉ በስፋት አይታዩም። ሃሳባቸው ቢደመጥ የሚደንቅ ለአገር የሚጠቅም ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ፊት በማምጣት አገር እንድትጠቀምበት ለማድረግ ያመቻል። መድረክ ያጡ ሰዎች መድረክ እንዲያገኙ በማገዝ ትውልዱ ማድመጥ ያለበት፤ መመራት ያለበት፤ ተፅዕኖ ሊገባ የሚገባው በማን ውስጥ እንደሆነ መለየት አለበት። ህብረተሰቡ የሚያዳምጠው በትክክል የመፍትሄ ሃሳቦችን እንዲሆን መንግስት፣ የሙያ ማህበራት እና መገናኛ ብዙሃን እውነተኛ ምሁራን መድረክ እንዲያገኙ ማድረግ ይኖርባቸዋል በማለት ዶክተር የሺጥላ ሃሳባቸውን አጠቃልለዋል።

አዲስ ዘመን ሀምሌ 19/2011

ምህረት ሞገስ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?
0Shares
0