አሁን አሁን በኢትዮጵያ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ የጥላቻ ንግግርንና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመቆጣጠር በግለሰብ፣ በተቋማት እና በመንግሥት ደረጃ ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ይስተዋላል።

ጉዳዩ ወጣቶችንም ሳያሳስብ አልቀረም ታዲያ። ለዚህም ነው ቴክቫህ ኢትዮጵያ የተጀመረው። አቅሌሲያ ሲሳይ በመላ ሃገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች መረጃን በዋናነት የሚያገኙት ከማህበራዊ ሚዲያ መሆኑን ትናገራለች።

የኤሌክትሪካል ምህንድስና እና ኮምፒውተር ተማሪ የነበረችው አቅሌሲያ፤ “በዩኒቨርስቲ ውስጥ ሳለን የምናገኘውን መረጃ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ አዳጋች ነበር” ትላለች።

በዚህ ሁሉም የራሱ የሆነ ገፅ ከፍቶ የተለያዩ መረጃዎች በሚያሠራጭበት ዘመን፤ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ዐይናቸውን ለቴሌቪዥን ጆሯቸውን ለሬዲዮ ለመስጠት ጊዜ እንዳልነበራቸው ታስታውሳለች – አቅሌሲያ። ሁሉም ሰው ሞባይሉ ላይ ተጥዶ በማህበራዊ ትስስር መድረኮች በኩል የሚያገኘውን መረጃ ይቃርማል።

እርሷ በዩኒቨርስቲ በነበረችባቸው የመጀመሪያ ዓመታት ፌስቡክ ለእነዚህ ተማሪዎች መረጃን በማቅረብ አልፋና ኦሜጋ ነበር።

በኋላ ግን ቴሌግራም መጥቶ የመረጃ ማቅረቡን መንበር ተቀላቀለ። ያኔ ነው የአቅሌሲያ ጓደኞች ስለቴሌግራም መነጋገር የጀመሩት።

አቅሌሲያም ስለ ቴክቫህ ኢትዮጵያ ሰማች፤ ቤተሰብም ሆነች።

ፀጋአብ ወልዴ ተወልዶ ያደገው ይርጋለም ነው። ሐዋሳ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በጋዜጠኝነትና በተባባሪ አዘጋጅነት መስራቱን ይናገራል። አሁን ደግሞ የቴክቫህ ኢትዮጵያ መስራችና የቤተሰብ አባል ነኝ ብሎ ነው ራሱን የሚያስተዋውቀው።

ቴክቫህ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከ320 ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላት ያሉት እና ቴሌግራም በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር መድረክ ላይ መረጃ የሚያቀብል ገፅ ነው።

ገፁን የሚቀላቀሉት ሁሉ የቤተሰብ አባላት ተብለው እንደሚጠሩ የሚናገረው ፀጋአብ ቴሌግራምን በስልኩ ላይ ጭኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዚህ ገፅ አባል ያደረጋቸው ስልኩ ላይ የሚገኙ ከሃያ እስከ ሠላሳ ሰዎችን ብቻ መሆኑን ያስታውሳል።

እነዚህ ሰዎች በስልኩ ውስጥ ቁጥራቸው የሰፈረ ባልንጀሮቹ ይሁኑ እንጂ የቴሌግራም ተጠቃሚም አልነበሩም።

ቀስ በቀስ ግን አንዱ አንዱን እየሳበ፤ ሌላኛው ለጓደኛው እየተናገረ የገፁ ተከታዮች ቁጥር ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

እነዚህን የቤተሰብ አባላት አንድ የሚያደርጋቸው መረጃ መፈለግ ብቻ ነው? ስንል ጥያቄ ያቀረብንላት የቴክቫህ ቤተሰብ አቅሌሲያ፤ ፈጠን ብላ “…ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊነት ይቅደም የሚለውም አንድ ያደርገናል” ብላለች።

የቴክቫ ገፅ

ቴክቫ የት ተጠነሰሰ?

ፀጋአብ በሐዋሳ ኤፍ ኤም 100. 9 ላይ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ የሐዋሳ ድምፅ ላይ ሲሠራ መረጃ አጠናቅሯል፤ አደራጅቷል። ፀጋአብ ዕድሜው ሃያዎቹን ያልዘለለ ወጣት ነው። በርካታ ወዳጆቹ እና የእድሜ አቻዎቹም የሚገኙት በትምህርት ቤት ውስጥ ነው።

ታዲያ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የተነሳ በዩኒቨርስቲዎችም ውስጥ ረብሻ፣ አመፅና ሞት ሁሌም ይሰማል። እነዚህን መረጃዎችን የሚያገኘው ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት መሆኑን ያስታውሳል። ነገር ግን ሁሌም አንድ ክፍተት ይታየዋል።

ይህ ለእርሱም ሆነ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ላሉ ጓደኞቹም የሚደርስ መረጃ፤ የብሔር ታፔላ አንጠልጥሎ፣ ስድብ አዝሎ፣ በቀል አንግቦ እንደሚንቀሳቀስ አስተዋለ።

“በፌስቡክ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ ዜናዎችን አያለሁ። ይህንን ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ወጣቶችም ያዩታል” ይላል።

አቅሌሲያም ይህንኑ ታረጋግጣለች። ተመርቃ ከመውጣቷ በፊት በዩኒቨርስቲ ውስጥ የምትሰማቸው መረጃዎች፣ ተረጋግታ ትምህርቷን እንድትማር የሚያደርጉ ሳይሆኑ ስጋትን የሚያጭሩ፣ መከፋፈልን፣ አለመተማመንን የሚያነግሱ መሆናቸውን አትረሳም።

ጉዳዩ ያሳሰበው ፀጋአብ፤ ከዚህ የማህበራዊ ትስስር መድረክ የመረጃ ቋት ውስጥ ፍሬውን ከገለባ፣ እንክርዳዱን ከፍሬው ለይቶ ለማቅረብ ሁነኛ መፍትሄ ሆኖ ያገኘው ቴሌግራምን ነው።

እናም ሐምሌ 19 ቀን 2009 ዓ.ም ላይ ቴክቫህ ኢትዮጵያ ተመሰረተ።

ቴክቫህ ኢትዮጵያ የገፅ ስያሜ ነው። ቴክቫህ የሂብሩ ቃል ሲሆን ተስፋ ማለት ነው ሲል ያብራራል፤ ተስፋ ኢትዮጵያ ለማለት መፈለጉንም ይናገራል።

ቴክቫህ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እውነተኛ መረጃ ማድረስን ስንቁ አድርጎ ቢይዝም ከዚያ ባሻገር የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይም ወጣቱን ለማሳተፍ እንደሚሰራ ፀጋአብ ይናገራል።

ከዚህ ባለፈም ደግሞ በጥላቻና በሐሰተኛ ንግግሮች ዙሪያ በመነጋገር መማማር እንዲፈጠር የተለያዩ ዘመቻዎችን እንደሚያደርግ አቅሌሲያ ትናገራለች።

ቴክቫህ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኀን የሚያገኛቸውን መረጃዎችን ከማቅረብ ባሻገር ተከታዮቹ ከያሉበት የሚልኳቸውን መረጃዎችንም ያቀርባል።

መረጃዎቹ ከየት መጡ፣ ማን ላከው የሚለውን በማጣራት ኃላፊነት እንዲሰማቸው በሚል ስማቸውን ጠቅሶ ያወጣል። ከተለያዩ መገናኛ ብዙኀን መረጃዎችንም ሲወስድ ያገኘበትን በመጥቀስ የገፁን ተዓማኒነት ለመጠበቅ ይጥራል።

ፀጋ አብ እንደሚለው ለየትኛውም አካል ወገንተኛ ሆኖ አይሰራም።

የቴክቫ የቤተሰብ አባላት በአካባቢ ጽዳት ላይ ተሰማርተውImage copyrightTIKVAH-ETH

ለምን ቴሌግራምን መረጠ?

ኢትዮጵያ ውስጥ ይፋዊ ጥናት ባይኖርም የማህበራዊ ትስስር መድረክ ተጠቃሚዎች ፌስቡክ ቀዳሚ ምርጫቸው ይመስላል፤ ፌስቡክ ይቅርብኝ ያለ ትዊተር መንደር አይታጣም።

ፀጋአብ ግን የመረጠው ቴሌግራምን ነው። ለምን?

ፀጋአብ ፌስ ቡክ ብዙ ተከታዮች እንዳለው አልካደም። ነገር ግን በፌስቡክ ላይ የሚንሸራሸሩ የትኛውም ጉዳዮች ላይ [በጎም ይሁኑ መጥፎ] የሚሰጡ አስተያየቶች መከባበር የተሞላባቸው እና የተለያዩ ወገኖችን ስሜት ያገናዘቡ አይደሉም ይላል።

ሰዎች አስተያየት የመስጠት መብታቸው የተጠበቀ ቢሆንም የጥላቻ ንግግሮች፣ በስፋት የሚታዮበት መድረክ እንደሆነ ለመናገር አላመነታም።

“ፌስ ቡክ ላይ ምንም አይነት ገፅ የለንም” የሚለው ፀጋአብ ገፃችንን ፌስ ቡክ ላይ አድርገነው ቢሆን ኖሮ አንባቢያችን እኛን ብቻ አይቶን ሳይሆን በዙሪያችን የሚርመሰመሱ ሌሎች የመረጃ አቅራቢዎች ጋር ጎራ ብሎ በዚያው መረጃ ሊወሰድ የሚችልበት እድል ሰፊ እንደሚሆን ይናገራል።

በቴሌግራም ላይ አንድ ሰው ፈልጎ የተቀላቀለው ካልሆነ በስተቀር ሌሎች ጉዳዮች ስለማይመጡ ተጠቃሚዎቻቸውን ቢያንስ ከስድብና ከጥላቻ ንግግር ለመጠበቅ እንደሚያስችላቸው በመግለፅ የቴሌግራምን ጠቀሜታ ያስረዳል።

ከዚህ ባሻገርም ቴሌ ግራም እንደ ፌስቡክ አስተያየት በመስጠት ስድብ የመወራወሪያ ዕድል ስለሌለው ራስን ከሐሰተኛ ዜናና ከጥላቻ ንግግር ለመጠበቅ ሁነኛ መላ ሆኖ እንደታየው ይገልጻል።

“በቴሌግራም ቢያንስ የተሻለ መደማመጥ የሚችል፣ የሌላውን ሐሳብ አክብሮ የእርሱን ሐሳብ የሚገልፅ ተጠቃሚ ፈጥረን ወደ ሌላዎቹ የማህበራዊ መድረኮች ወደፊት ልንሄድ እንችላለን፣ አሁን ግን ቴሌ ግራም ብቸኛ አማራጫችን ነው” ብሏል- ፀጋአብ።

ፀጋአብ ቴክቫህ ኢትዮጵያ በተመሠረተበት በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ አንድ ቀን ብቻ መረጃ ለቤተሰብ አባላቱ ሳያደርስ መቅረቱን ያስታውሳል።

ያ- ቀንም ሕመም ገጥሞት እርሱና ሞባይሉ ተራርቀው የነበረበት ነው።

በመላው ሀገሪቱ አልያም በትላልቅ ከተሞች ኢንተርኔት ድርግም ብሎ ሲጠፋ እንኳ እርሱ ዋይፋይ ወደሚያገኝበት ጎራ ብሎ መረጃዎቹን ለቤተሰብ አባላቱ እንደሚያደርስ ይናገራል።

ፀጋአብ መረጃዎቹ ለመቀበልም ሆነ ለማድረስ ሳምሰንግ ኖት 9ንና ሳምሰንግ ኤ70 ስልኮችን ይጠቀማል። የባትሪ እድሜያቸው ረዥም ስለሆነ ነው የመረጥኳቸው ሲል ያክላል።

ቴክቫ ኢትዮጵያ በአማርኛ ብቻ ለምን?

የቴክቫህ የቤተሰብ አባላት በዋናነት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ወጣቶች ናቸው። እነዚህ ወጣቶች ደግሞ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡና የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው።

የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆኑ የቴክቫህ ቤተሰብ አባላት በሀሮማያ ዩኒቨርስቲImage copyrightTIKVAH-ETH

ፀጋአብ ይህ ጉዳይ በሚገባ ያሳስበዋል። ለዚህም በዚህ ዓመት ቴክቫህን በኦሮምኛ ቋንቋ ጀምሮ እየሞከረ እንዳለ ይናገራል። በሌሎች ቋንቋዎችም ለመጀመር እቅድ ይዟል። በማለት ነገሮች ካሰበው ፍጥነት በላይ በመሄዳቸው ሌሎች ተጓዳኝ ተግባራትን ለማከናወን አዳጋች እንደሆነበት ያስታውሳል።

በሁለት ዓመት ውስጥ ከ300ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን እደርሳለሁ ብሎ አለማሰቡን የሚናገረው ፀጋአብ ሌሎች በርካታ ሀሳቦች እንዳሉትም አጫውቶናል።

ፀጋአብ እንደሚለው በርካታ ሰው የሚያውቀው ወቅታዊ መረጃዎችና ዜናዎች የሚቀርቡበትን ቴክቫህ ኢትዮጵያን ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የታመሙ ሰዎች የሚያሳክሙበት፣ የተቸገሩ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያደርጉበት 4ሺህ ተከታዮች ያሉት ቴክቫህ ኤይድ የሚባል ገፅ እንዳላቸው ይናገራል።

ይህ ብቻም ሳይሆን ተማሪዎች ኦሮምኛ፣ትግርኛና ግዕዝን በቀላሉ በስልካቸው መማር እንዲችሉ የሚያገለግል 24ሺህ ተከታዮች ያሉት ቴክቫህ ኢዱ የተሰኘ ገፅም አለው። እርሱ እንደሚለው ይህ ገፅ በበጎ ፍቃደኞች የቤተሰብ አባላት የተደራጀ ነው።

“ወደፊት የቤተሰብ አባላቶቻችንን እያየንና እነርሱ ሊያገለግሉ በሚችሉበት መስክና ቋንቋ መረጃዎችን ለማድረስ መሞከራችን አይቀርም” ይላል -ፀጋአብ።

የቴክቫ ኢትዮጵያ ዘመቻዎች

የቴክቫ የቤተሰብ አባል በችግኝ ተከላ ላይ ተሳትፋImage copyrightTIKVAH-ETH

በተቋማት ውስጥ ያሉ ተማሪዎች በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ጥላቻዎች ተሰብከዋል፤ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ልዩነት እንዲሰፋ የሚሰሩ መልዕክቶች በሰፊው ይሠራጫሉ የሚለው ፀጋአብ በማህበራዊ ትስስር መድረክ ላይ የጥላቻ ንግግርን የሚቃወሙ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ መቆታቸውን ይናገራል።

የቴክቫህ ቤተሰብ አባላት ግን ይህንን የጥላቻ ዘመቻ ተገዳድሮ የሚቆም የሰላም፣ የመቻቻል መልዕክትን ማስተላለፍ እንደሚቻል ለማሳየት መንቀሳቀሳቸውን ይገልጣል።

ባለፈው ዓመት የቴክቫህ የቤተሰብ አባላት በ11 ዩኒቨርስቲዎች በመንቀሳቀስ የጥላቻ ንግግሮችን በተመለከተ ከተቋማቱ ተማሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በዚህ ጉዟቸው ከመቀሌ እስከ አርባ ምንጭ፤ ከወልቂጤ እስከ ደብረብርሀን፤ ከዋቻሞ እስከ ወሎ፤ ከሐሮማያ እስከ ወላይታ ዩኒቨርስቲዎች ድረስ ተጉዘዋል።  ሄዱበት ሁሉ ተማሪዎች እርስ በእርሳቸው እንዲደጋገፉ፣ አንዱ አንዱን እንዲያውቅ የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን ይናገራል።

“በአንዳንድ ተቋማት ይህንን መልዕክት ይዞ መሄድ አስቸጋሪ ቢሆንም እኛ ግን ሀሳባችንን ደግፎ የሚቆም አንድ ሰው እንኳን ቢገኝ በማለት ሄደናል፤ በመሄዳችንም ውጤታማ ሆነናል።” ይላል።

ከተማሪዎቹ ጋር በሚኖር ውይይት በአርባ ምንጭ የሀገር ሽማግሌዎች እንደነበሩ የሚያስታውሰው ፀጋአብ በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ግን በወጣቶች መካከል ብቻ ውይይት መደረጉን፣ በየዩኒቨርስቲዎቹ ባሳለፉትም ሁለት ሁለት ቀን አብዛኛዎቹን ወጪዎች የቴክቫህ ቤተሰብ አባላት መሸፈናቸውን ይናገራል።

ሰው በሰውነቱ እንዲከበር ከዚያም ስለሌሎች ጉዳዩች ለመነጋገር የጥላቻ መልዕክቶችን ማስወገድ ተገቢ መሆኑን የምትናገረዋ አቅሌሲያ በሚቀጥለው ዓመትም ተመሳሳይ መልዕክትን በማንገብ እንደሚጓዙ ነግራናለች።

ቴክቫህ የቴሌግራም ገፅ አሁን ወጪውን የሚሸፍነው ከሚያስተላልፋቸው ማስታወቂያዎች መሆኑን ፀጋአብ ይናገራል።

ቴክቫህ ወደፊት የጥላቻ ንግግሮችን ለማስቀረት፣ ሐሰተኛ ዜናዎችን ለመዋጋት በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የመጓዝ፣ በበጎ አድራጎት በሰፊው ለመሰማራትና ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል የመገናኛ ብዙኀን ለማቋቋም ሀሳብ እንዳለው ፀጋአብ ገልፀፆልናል።

ቢቢሲ አማርኛ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *