በአማራ ክልል ዕውቅና ከተሰጣቸው 93 የግል ኮሌጆች መካከል 39 ችግር ያለባቸው መሆኑን የክልሉ ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡ ኮሌጆቹ የሚሰጡት ትምህርት የሥራ ገበያ ፍላጎት፣ ያላቸውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ሌሎች መመዘኛ መስፈርቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነበር ዕውቅና የተሰጣቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከተፈቀደላቸው አሠራር ውጭ በርቀት የሚያሰለጥኑ፣ ከተፈቀደላቸው የስልጠና የሙያ ዘርፎች ውጭ ስልጠና የሚሰጡ፤ ከተፈቀደው የመግቢያ ነጥብ በታች ተማሪዎችን እየተቀበሉ የሚያሰለጥኑ እና ከተፈቀደው የሰልጣኝ ቁጥር በላይ ከፍተኛ ሰው የሚያሰለጥኑ ኮሌጆች መኖራቸውን የቢሮው ኃላፊ አቶ የሻምበል ከበደ አስታውቀዋል፡፡ በገበያ የማይፈለጉ ሙያዎች ማሰልጠን እና የስልጠና ዕውቅና ሳይኖራቸው አሰልጥነው የምሥክር ወረቀት መስጫ ጊዜያቸው ሲደርስ ወደ ቢሮው የሚሄዱ ኮሌጆች እንዳሉም ተመላክቷል፡፡

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

በዚህም መሠረት ቢሮው ባደረገው ኦዲትና ግምገማ ወረታ ላይ አዲስ ፋና እና ጎንደር ላይ ራዳ ኮሌጆችን አግዷል፡፡ 39 የሚሆኑት ደግሞ ችግር እንዳለባቸው ተለይቷል፡፡ ከ39 ኮሌጆች መካከል የተወሰኑት በእጃቸው ያሉ ሰልጣኞችን እስከሚያስመርቁ ድረስ የጊዜ ቀጠሮ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል፡፡ የከፋ ችግር ያለባቸው ኮሌጆች ደግሞ በማኅበረሰቡ ላይ የከፋ ጫና ሳያደርሱ ሰልጣኞቹ ወደ ሌላ ኮሌጅ እንዲሸጋገሩ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በቀጣይ ከሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን ተጨማሪ ኦዲት በመሥራት ‹‹የተሻለ የሚሠሩ ኮሌጆችን በተለይም ወደ ቴክኖሎጂ ፈጠራ እንዲገቡ መንግሥት እገዛ ያደርጋል›› ብለዋል አቶ የሻምበል፡፡ ኅብረተሰቡን ከተጨማሪ ጉዳት ለመታደግ በኮሌጆች ላይ ጠበቅ ያለ ኦዲት እየተደረገ መሆኑን ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ መቀጠል የሌለባቸው ኮሌጆች ዕውቅናቸው እንዲሰረዝ እስከሚደረግ ድረስም አዳዲስ ኮሌጆች እንዳይከፈቱ ቢሮው ማገዱን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

‹‹ኅብረተሰቡ በተለይ በግል ኮሌጆች ከፍተኛ ወጭ አውጥቶ የሚያስተምረው የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብሎ ቢሆንም ውጤቱ ግን ከዚህ በተቃራኒው እየሆነ ነው›› ብለዋል አቶ የሻምበል ከበደ፡፡ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በግል ኮሌጆች ተመርቀው የሥራ ዕድል ያገኙት ከ62 በመቶ አይበልጡም፡፡ ምንም እንኳን የቴክኒክና ሙያ ‹ስትራቴጂ› ወጣቶችን ሥራ ፈጣሪ ማድረግ ቢሆንም በተገቢው መንገድ ክህሎት ባለማግኘታቸው ምክንያት አብዛኞቹ ሰልጣኞች ወደ ሲቪል ሰርቪስ ተቋም ነው የሚገቡት፡፡

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

እነዚህ ችግሮች በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና አላቸው፡፡ በዚህ ወቅት ግን ኅብረተሰቡ ለችግር ተጋላጭ እንዳይሆን እየተሠራ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡ ፈቃድ የተሰጣቸውን ተቋማት ዝርዝር መረጃ በዞን እና በወረዳ ቴክኒክ እና ሙያ ተቋም ማግኘት እንደሚቻልም አቶ የሻምበል ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 01/2011 ዓ.ም (አብመድ)

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *